ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ሲዳማ ቡና

ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና ነገ በሚያደርጉት የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ዙሪያ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

የሀዋሳውን ሰው ሰራሽ ሜዳ የሚጠቀሙት ደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና ነገ በ11ኛው ሳምንት እርስ በርስ ይገናኛሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ እና ታች የተቀመጡት ሁለቱ ክለቦች አስረኛውን ሳምንት በአቻ ውጤት ነበር ያለፉት። ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገዱት ሲዳማዎች በመሀመድ ናስር ጎል ከሽንፈት ሲድኑ ደቡብ ፖሊስም በሽረ ከተመራ በኋላ በኄኖክ አየለ ግብ አማካይነት ጨዋታውን 1-1 ማጠናቀቅ ችሎ ነበር። ከስምንተኛው ሳምንት በኋላ ወደ አሸናፊነት መመለስ የተሳናቸው ሲዳማዎች ከሦስተኛ ወደ ስምንተኝነት ወርደዋል። ዳግም ወደ ዋንጫው ፉክክር ለመመለስም ነገ ማሸነፍ ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ጨዋታው የሊግ ቆይታው ካሁኑ ማጠራጠር ለጀመረው ደቡብ ፖሊስም ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድል ይሰጠዋል።

የደቡብ ፖሊሶቹ ኤርሚያስ በላይ ፣ ቢኒያም አድማሱ እና ሙሉዓለም ረጋሳ ከጉዳት ተመልሰው ለነገው ጨዋታ መድረሳቸው እግርጥ ሲሆን ወደ ልምምድ የተመለሱት ብርሀኑ በቀለ እና በረከት ይስሀቅ ግን የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ መሳይ አያኖ ፣ ዮሴፍ ዮሃንስ እና ዳግም በቀለ በጉዳት እንዲሁም ግርማ በቀለ በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።

ወደ ኋላ አፈግፍጎ የሚከላከል ቡድን ሲገጥማቸው ከተሻጋሪ ኳሶች ውጪ ሌሎች አማራጮችን የመፈለግ ችግር የታየባቸው ሲዳማዎች ነገም ተመሳሳይ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። ደቡብ ፖሊስ ከጨዋታው ነጥብ ለማግኘት ጥንቃቄን ለመምረጥ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ከሚገኙ ዕድሎች ወደ ፊት አጥቂው የሚጥላቸው ኳሶች መኖራቸው ግን አይቀርም። ሆኖም የሲዳማን የመስመር አጥቂዎች እንቅስቃሴ አፍኖ ማስቀረት ለቡድኑ ትልቁ ፈተና ይሆናል። ሲዳማ ቡናዎች ከፈጣሪ አማካያቸው ዳዊት ተፈራ በሚነሱ ኳሶች በሁለቱ መስመሮች ወደ ውስጥ ለመግባት መጣር እንዲሁም የተጋጣሚያቸው የኋላ መስመር ከግቡ የሚርቅበት አጋጣሚ ካለ በፍጥነት ሰብረው ከመግባት ዕድሎች የመፍጠር ዕቅድ ይኖራቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሲዳማ ቡና ወደ ሊጉ በመጣበት እና ደቡብ ፖሊስ በወረደበት የ2002 የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ አንዱን ሲያሸንፍ ሁለተኛውን በአቻ ውጤት ጨርሰዋል። ሲዳማ ሁለት ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አንድ ግቦችን አስቆጥረዋል።

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን ሀዋሳ ላይ እያንዳንዳቸው አምስት ጨዋታዎችን አድርገዋል። በውጤቱም ደቡብ ፖሊስ አንዱን አሸንፎ በሌሎቹ ሽንፈት ሲያስተናግድ ሲዳማ በተቃራኒው በዚሁ ሜዳ ሦስቱን በድል አጠናቆ ሁለቴ ነጥብ ተጋርቷል። ነጥብ የጣለባቸው ጨዋታዎች ግን በመጨረሻ ያደረጋቸው ነበሩ።

ዳኛ

– ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመምጣት ሁለት ጨዋታዎችን ዳኝቶ አምስት የቢጫ ካርዶች እና አንድ ቀይ ካርድ የመዘዘው ኢሳያስ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ዳዊት አሰፋ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ

አዲስአለም ደበበ – ኤርሚያስ በላይ – ዘላለም ኢሳያስ

ብሩክ ኤልያስ – በኃይሉ ወገኔ – ኄኖክ አየለ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – አበባየሁ ዮሃንስ – ወንድሜነህ ዓይናለም

ፀጋዬ ባልቻ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – አዲስ ግደይ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *