ሪፖርት | ለረጅም ደቂቃዎች ተቋርጦ በቀጠለው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ደቡብ ፖሊስን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ለ35 ደቂቃዎች ተቋርጦ የነበረው የደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በሲዳማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ደቡብ ፖሊስ ወደ ሽረ አምርቶ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ዘሪሁን አንሼቦን በዘላለም ኢሳያስ ፣ አበባው ቡታቆን ከረጅም ጊዜ ጉዳት በተመለሰው ብርሀኑ በቀለ ፣ አዲስዓለም ደበበን በኤርሚያስ በላይ ፣ መስፍን ኪዳኔን በኄኖክ አየለ እንዲሁም ብሩክ አየለን በብሩክ ኤልያስ ተክቶ ጨዋታውን ጀምሯል። ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ብቻ በማድረግ ተመስገን ገብረፃዲቅ እና ግርማ በቀለን በመሀመድ ናስር እና ወንድሜነህ ዓይናለም ተክተዋል።

ጨዋታው ሲጀምር ተመጣጣኝ ቢመስልም የሲዳማ ቡናዎች አስፈሪ የማጥቃት ኃይል የታየበት ነበር፡፡ ደቡብ ፖሊሶች በአመዛኙ ከኤርሚያስ በላይ እና ዘላለም ኢሳያስ ከጥልቅ አማካይ ክፍላቸው ረጃጅም ኳሶችን ወደ ብሩክ ኤልያስ በመጣል ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ጨራሽ የሚባል አጥቂ አለመኖር ለሲዳማ የተከላካይ ክፍል በቀላሉ እጅ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። በደጋፊዎቻቸው ታግዘው በጨዋታው ያገኙትን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም ከቢጫ ለባሾች የተሻሉት ሲዳማ ቡናዎች በመሀመድ ናስር ፣ አዲስ ግደይ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ አማካኝነት በአማካይ ክፍሉ ጥሩ ጥምረት ከነበራቸው ዳዊት ተፈራ እና ወንድሜነህ አይናለም ታግዘው ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች ሲያገኙ ተስተውሏል፡፡

ጨዋታው ገና ከመሀል ሜዳ እንደተጀመረ ዮሴፍ ዮሃንስ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ከዳዊት ተፈራ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ እንደምንም ያዳነበት የመጀመሪያው ሙከራ ነበር። ሆኖም ጨዋታው 7ኛው ደቂቃ ላይ ለመቋረጥ ተገዷል። ከስታድየሙ ውጪ መግቢያ በር ላይ እጅግ በርካታ ደጋፊዎች ወደ ቅጥር ግቢው ለመግባት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት የፀጥታ አካላት የአስለቃሽ ጭስ በመተኮሳቸው ነበር ጨዋታው የተቋረጠው። በስታድየሙ ውስጥ የተገኙ በርካታ ደጋፊዎችም ወደ መጫወቻ ሜዳው ውስጥ በመግባት ከጭሱ ለማምለጥ በባደረጉት ጥረት ጉዳት አስተናግደዋል።  ሆኖም የሲዳማ ቡና የደጋፊዎች ማህበር አባላት ባሳዩት መልካም የማግባባት ስራ ጨዋታው ከ35 ያህል ደቂቃዎች መቋረጥ በኃላ በድጋሚ ሊቀጥል ችሏል፡፡

ሲዳማዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ዕድሎችን ለመፍጠር አሰላለፋቸውን ከ4-3-3 ወደ 3-4-3 በመቀየር መሀል ላይ በዮሴፍ ፣ ወንድሜነህ እና ዳዊት በሚገኙ ዕድሎች በሚገባ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለመጫን ሞክረዋል። ፖሊሶች ደግሞ የግራ እና ቀኙን የሜዳ ክፍል ለጥጠው ለመጫወት እና በሚያገኙት የመልሶ ማጥቃት ዕድል ተጠቅመው በቀጥተኛ  ኳሶች ኄኖክ አየለን ለመጠቀም ያለመ አጨዋወትን ተግብረዋል።

በተሻለ ሁኔታ በርከት ያሉ ጥቃቶችን ሲፈፅሙ ከነበሩት ሲዳማ ቡናዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ የዋለው ዳዊት ተፈራ በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ወንድሜነህ ዓይናለም በግሩም አጨራረስ የቀድሞው ክለቡ ላይ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ወንድሜነህ ግቧን ካስቆጠረ በኃላ ደስታውንም ሳይገልፅ ቀርቷል፡፡ በደቡብ ፖሊስ ግራ መስመር ከጉዳት በተመለሰው ብርሀኑ በቀለ በኩል በተደጋጋሚ ሲዳማዎች ሰብረው ሲገቡ ቢታይም ፖሊሶች አበባው ቡታቆን በመቀየር በመጠኑ እፎይታን ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ከዳዊት እግር በሚነሱ ኳሶች የጎንዮሽ ቅብብሎችን እያደረጉ ወደ ሳጥን በመግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የታዩት ሲዳማዎች በሌላ አጋጣሚ ዮናታን ፍሰሀ ከማዕዘን ምት አሻግሮት መሀመድ ናስር በግንባሩ ከገጨው ኳስ ከባድ ሙከራ አድርገዋል።

በደቡብ ፖሊሶች በኩል በአጋማሹ መገባደጃ ላይ በተደረገ አደገኛ ሙከራ አበባው ቡታቆ በግራ በኩል ከግቡ ትይዩ ለሚገኘው ብሩክ ኤልያስ ሰጥቶት ብሩክ አገባው ሲባል በተከላካዩቹ ጥረት በቀላሉ አምክኗታል፡፡ ሆኖም 44ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከወንድሜነህ ዓይናለም ያገኛት ኳስ ወደ ውስጥ ገፍቶ በመግባት በቀድሞው ክለቡ ላይ አስቆጥሮ የሲዳማን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ በብቸኝነት ከፊት ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው ኄኖክ አየለ ለደቡብ ፖሊስ ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 2-1 መሪነት ተገባዷል።

ከእረፍት መልስ ደቡብ ፖሊሶች ቀዝቀዝ ብሎ የታየውን የተሻ ግዛውን በልዑል ደረጀ ከተኩ በኃላ የሲዳማ ቡናን የቀኝ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲያስጨንቁ ኄኖክ አየለም ከሌላኛው አጥቂ በኃይሉ ወገኔ በተሻለ የቡድኑን ጥቃት መዳረሻ ሆኖ ታይቷል። ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው በተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድን ከአማካይ ክፍሉ ወደ መስመር በሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔ ከማዕዘን አሻምቶት ደስታ ጊቻሞ በግንባር የገጫት ኳስ ደቡብ ፖሊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ ለመሻላቸው ማስረጃ ሆናለች፡፡


በአንፃሩ የሲዳማዎቹ አዲስ ፣ ወንድሜነህ እና ዳዊት በተደጋጋሚ ከርቀት አክርረው የሚመቷቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ኳሶች የዳዊት አሰፋ ብቃት ባይታከልባቸው ኖሮ የግብ ልዩነቱን የማስፋት ጉልበት ነበራቸው። ነገር ግን 63ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የደቡብ ፖሊስ የግብ ክልል በአስደናቂ እንቅስቃሴ ወደ ውስጥ እየገፋ የገባው ሀብታሙ ገዛኸኝ ተሳክቶለት ለራሱ ሁለተኛ ለክለቡ ደግሞ ሦስተኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ሲዳማዎች በዮናታን ፍሰሀ አማካኝነትም ሌላ አጋጣሚን አግኘተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ 

በ78ኛው ደቂቃ የደቡብ ፖሊሱ አጥቂ ኄኖክ አየለ ከፍቅሩ ወዴሳ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ፍቅሩ ያወጣበት ኳስ ምናልባት ቡድኑን ወደ ጨዋታው ልትመልስ ተቃርባ ነበር፡፡ ሆኖም ደቡብ ፖሊሶች ኄኖክ አየለ በግሉ ከሚያገኘው አጋጣሚ ውጪ ሌላ የጠራ ዕድል መፍጠር ተስኗቸው ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *