የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 1-3 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ለ35 ደቂቃዎች መቋረጥ ገጥሞት የነበረው የደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” ያገኘናቸውን ዕድሎች ጫና ፈጥረን በመጫወታችን ወደ ግብ ቀይረናቸዋል” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው 

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። በጣም ተጭነን ነበር የተጫወትነው። ምክንያቱም ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ተሸንፈን ሁለት አቻ ወጥተናል። ከዛ ነገር ደግሞ ለመውጣት አጥቅተን ለመጫወት ነው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ደቂቃ ድረስ የሞከርነው። ያም ተሳክቶልናል። ቡድናችን ተደጋጋሚ ጎሎች ጋር ይደርስ ነበር፡፡ ከተጠቀምናቸው ያልተጠቀምናቸው ኳሶች ይበልጣሉ። ይሄ ደግሞ አንዳንዴ ይከሰታል። የፊት አጥቂያችን አዲስ ኳሶች ሲበላሹበት የነበረው በጉጉት ይመስለኛል። ከዛ ውጪ በጣም ያስደሰተኝ መሐመድ ወደ ነበረበት ብቃቱ መመለሱ ነው። ለቡናችን የሱ ጥሩ መሆን አቅም ሆኖናል፡፡ ማሸነፍ ብዙ ነገርህን ያነሳሳል እስከ አሁን በተለያዩ ምክንያቶች ነጥብ እንደጣልን ይሰማናል። ነጥብም ስንጥልም ብዙ ያገኘናቸውን ዕድሎች ማምከናችን ነበር ችግሩ። ዛሬ ግን ያ የለም ፤ ያገኘናቸውን ዕድሎች ጫና ፈጥረን በመጫወታችን ወደ ግብ ቀይረናቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተነሳሽነታችንን ጨምሮታል።”

ስለ ልዩነት ፈጣሪው ዳዊት ተፈራ

“ዳዊት በየጨዋታው የሚያሳየው እንቅስቃሴ ልዩ ነው። ብዙ ጊዜ እሱን የምንጠቀመው የኛ ቡድን አጨዋወት ልክ እንደሱ ስለሆነ ነው። ይሄ ግን ቲክቲኩ ይወስነዋል። አንዳንዴ በታክቲኩ ሊቀመጥ ይችላል። ለምሳሌ በመቐለ ጨዋታ አልተጫወተም። እንደዚህ አጥቅተን ለመጫወት ስናስብ ደግሞ ዳዊት አንደኛ ምርጫችን ነው። አንደየተጋጣሚዎቻችን ሁኔታ ተጫዋቾችን እንጠቀምባቸዋለን ዳዊት የሚያሳየው ብቃት ግን አበረታች ነው።”

” አስለቃሽ ጭሱ ከጨዋታ ውጪ እንድንሆን አድርጎናል ” ዘላለም ሽፈራው –  ደቡብ ፖሊስ

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው ደርቢ ከመሆኑ አንፃር ውጥረት እንደሚኖረው ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ጨዋታው ሲጀመር  ጥሩ ነበር እስኪቋረጥ ድረስም መልካም አጀማመር ነበረን። በደጋፊው ዘንድም ስንመለከት የነበረው ጥሩ ነገር ነው፡፡ አስለቃሽ ጭስ ከተተኮሰ እና ከተቋረጠ በኃላ ተጫዋቾቼ ወርደዋል። ጨዋታው በስረዓት እየተካሄደ ነው ፤ ለምን ግን እንደዚህ እንደሆነ አላወኩም። ተመልካቹም በሥነ ስርዓት እየደገፈ ነበር ፤ እዚህ ያለውን እንዳየነው ውጪ ፤ የነበረውን ባናውቅም።  ነገር ግን ጨዋታው ተቋርጦ ህዝብም ሜዳ ውስጥ ገብቷል። በአጠቃላይ የኛ ልጆች በስነ ልቦና ወርደው ነበር። ይሄ ደግሞ የሚጠበቅ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በስነ ልቦና ቢወርዱም የሚገርም አይደለም። ለምን እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደሚደረግ አልገባኝም ለኔ ይሄ ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ አስለቃሽ ጭሱ ከጨዋታ ውጪ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ”

ስለ ውጤት ማጣት

“ቡድኑ ወራጅ ቀጠና ላይ መሆኑ የሚገርም ነገር የለውም። ዝግጅት የጀመረው ዘግይቶ ከመሆኑ በጨማሪ በሊጉ ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸውን ተጫዋቾች ነው ያሰባሰብነው። ቡድኑ ውጤት አጣ ተብሎ እኛ አካባቢ ባሉ ሚዲያዎች የሚዘገቡ ነገሮች በዕውቀት ቢሆኑ ጥሩ ነው። እኛ ምን እናድርግ? የተሻለ አጥቂ ለማምጣት ብር መክፈል አለብን.. ካልከፈልክ አታገኝም። እኛ ደግሞ የአጥቂ ችግር አለብን። በምንችለው አቅም ስናስፈርም ደግሞ ሚዲያው የጨረሱ ተጫዋቾች አመጡ ይላል። እስካሁን በአሳማኝ ሁኔታ አይደለም ስንሸነፍ የነበረው፤ ምናልባት ዛሬ ሲዳማ ብቻ ነው በልጦ ያሸነፈን።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *