የ11ኛ ሳምንት የነገ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

ዛሬ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ነገ በጎንደር እና አዲስ አበባ ረፋድ 04፡00 ላይ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል። በሁለቱ ጨዋታዎች ዙሪያም ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

ከሦስት ቀናት በፊት በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም ደደቢትን አስተናግዶ ድል ማድረግ የቻለው ፋሲል ከነማ ነገ ደግሞ ወላይታ ድቻን በሜዳው ይገጥማል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ፋሲል ሊጉን የመምራት ተስፋውን አስጠብቆ ከዛሬዎቹ ጨዋታዎች በኋላ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ነገ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻልም ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አራት ማጥበብ ይችላል። በተቃራኒው ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ላይ ተቃውሞ እስከማስነሳት የደረሰ የአቋም መዋዠቅ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ሳምንት ወልዋሎን አስተናግዶ በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቀው። የመጨረሻ ድሉን ደቡብ ፖሊስ ላይ ካስመዘገበ በኋላ ሦስት ነጥብ ካሳካ አንድ ወር ያለፈው ድቻ አስር ነጥብ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከጎንደር በድል ከተመለሰ ወደ ሰንጠረዡ ወገብ በመጠጋት ለአሰልጣኙም እፎይታ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

በደደቢቱ ጨዋታ ጉዳት ከገጠማዎቸው የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች መካከል ሙጁብ ቃሲም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን የሱራፌል ዳኛቸው መግባት አለመግባትም ግን አለየለትም። ከዚህ ውጪ ፋሲል አስማማው አሁንም ከጉዳት ያላገገመ ቢሆንም ሽመክት ጉግሳ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ይመለሳል። በወላይታ ድቻ በኩል የረጅም ጊዜ ጉዳት ገጥሞት ያገገመው ኃይማኖት ወርቁ አሁንም ለጨዋታው ብቁ ባለመሆኑ የማይደርስ ሲሆን ያሬድ ብርሀኑ ፣ ተክሉ ታፈሰ እና ፀጋዬ አበራም በጉዳት ወደ ጎንደር ያላመሩ ተጫዋቾች ናቸው። በተጨማሪም የአራት ጨዋታ ቅጣት የተላለፈበት እሸቱ መና በቅጣት የማይሰለፍ ይሆናል፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች አራት ጊዜ ተገናኝተው ሁለት ሁለት ጊዜ መሸናነፍ ችለዋል። የአቻ ውጤት ባልተመዘገበባቸው ጨዋታዎቻቸውም ድቻ 5 ጎል ሲያስቆጥር ፋሲል 4 ጊዜ ግብ ቀንቶታል።

– ፋሲል ከነማ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን ሲያሳካ ምንም ሽንፈት አላገኘውም።

– አምስት ጊዜ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የደረጉት ወላይታ ድቻዎች በሦስቱ ሲሸነፉ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ዳኛ

– ከአስሩ ሳምንታት ውስጥ በሁለቱ በመራቸው ጨዋታዎች አስራ አንድ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ያሳየው ተካልኝ ለማ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ዮሴፍ ዳሙዬ – ሐብታሙ ተከስተ – ኤፍሬም አለሙ

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ – አብዱራህማን ሙባረክ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

ተክሉ ታፈሰ – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ፍፁም ተፈሪ – እዮብ ዓለማየሁ

አንዱዓለም ንጉሴ

መከላከያ ከ ስሐል ሽረ

በከተራ በዓል ምክንያት እንደ ጎንደሩ ጨዋታ ሁሉ የሰዓት ማስተካከያ የተደረገበት የመከላከያ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ 04፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይጀምራል። ሜዳው ላይ ባደረጋቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች አስር ግቦች የተቆጠሩበት መከላከያ ያሉት ተስተካካይ ጨዋታዎች እንዳሉ ሆነው አሁን ላይ ለወራጅ ቀጠናው ቀርቧል። መረጋጋት የማይታይበት የቡድኑ አቋም እንዲስተካከልም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። ለሊጉ እንግዳ የሆኑት ስሑል ሽረዎች የሚገኙበት ሁኔታም ከተጋጣሚያቸው እምብዛም የተሻለ አይደለም። ቡድኑ እስካሁን ከዘጠኝ ጨዋታዎች በሦስቱ ብቻ አንድ አንድ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ድሉን ለማግኘትም ገና በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

መከላከያ አቤል ማሞን እና ምንይሉ ወንድሙን ከጉዳት ዓለምነህ ግርማን ደግሞ ከቅጣት መልስ የሚያገኝ ሲሆን ዳዊት እስጢፋኖስ ግን ከጉዳት ባለማገገሙ ለነገው ጨዋታ አይደርስም። በስሑል ሽረ በኩል ደግሞ ሰዒድ ሀሰን ብቻ ከጉዳት ሲመለስ ሸዊት ዮሃንስ ፣ ሰለሞን ገብረመድህን፣ መብራህቶም ፍስሃ እና ንስሃ ታፈሰ አሁንም እንዳላገገሙ ታውቋል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ጨዋታው ለቡድኖቹ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነታቸው ይሆናል።

– ዘንድሮ የአዲስ አበባ ስታድየም የሆነው የማይመስለው መከላከያ ከአራት ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፏል። ወላይታ ድቻን 3-1 የረታበት ጨዋታም ብቸኛው ድሉ ነው።

– በሦስት አጋጣሚዎች ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎች ያደረጉት ስሑል ሽረዎች በሁሉም ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ከነዚህ መካከል ሁለቱ በአዲስ አበባ ስታድየም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የተሸነፉባቸው ናቸው።

ዳኛ

– ጨዋታው ለአሸብር ሰቦቃ የዓመቱ አራተኛ ጨዋታ ይሆናል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች 13 የቢጫ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምትም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

በኃይሉ ግርማ

ሳሙኤል ታዬ – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ፍሬው ሰለሞን

ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ

ሳሙኤል ተስፋዬ – ኄኖክ ካሳሁን

ኢብራሒማ ፎፋና – ጅላሎ ሻፊ – ልደቱ ለማ

ሚድ ፎፋና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *