የግል አስተያየት | ዮሐንስ ሳህሌ አምና እና ዘንድሮ…

አስተያየት በዘርዓይ ኢያሱ

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እና ድሬዳዋ ከተማ የመለየታቸው ነገር እርግጥ መሆኑን ሰሞኑን ከተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎች ሰምተናል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ አምስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ካከናወነ በኋላ ቡድኑን ለመልቀቅ የወሰነበት ምክንያት ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው በፋሲል ከነማ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ከደጋፊው ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው ነው ተብሏል፡፡
ይህ አንዱ ምክንያት ሆኖ ሳለ እኔ ታክቲካዊ ጉዳዮች አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድኑን የለቀቀበት ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ 

አሰልጣኙ በ2010 የውድድር ዓመት መቐለ 70 እንደርታን ይዘው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ መርዳቱ ይታወሳል፡፡ በጊዜው መቐለ ለሊጉ አዲስ እንደመሆኑ ቡድኑን በሊጉ እንዲቆይ ከማስቻሉም ባሻገር አራተኛ ሆኖ በመጨረስ ስኬታማ ግዜ ሳልፈዋል፡፡ ይህን ሲያሳካ ደግሞ የራሱ የሆነ የጨዋታ ምርጫ ነበረው፡፡

4-4-2

አሰልጣኝ ዮሐንስ መቐለ በ2010 የውድድር ዓመት 4ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ 4-4-2 ዝርግ የሚባለው ፎርሜሽንን ሲጠቀም አስተውያለሁ። በዮሐንስ ተመራጭ የሆነው 4-4-2 ፍላት (flat) የሚባለው ይህ ፎርሜሽን ለተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡ በዚህ የጨዋታ ቅርፅ አራቱ ተካላካዮችና በአራቱ አማካዮች መካከል ያለው ክፍተት በጣም ጠባብ ሆኖ የተጋጣሚ ቡድን ኳስ እንደፈለገ ማንሸራሸር እንዳይችል እና የጎል እድሎችን እንዳይፈጥር የሚገታ ነው፡፡

ለዚህ ጥሩ ማሳያ ልናደርግ የምንችለው በ2010 የገባበትንና ያስቆጠረውን የጎል መጠን ነው፡፡ መቐለ በ30 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የገባበት 16 ጎሎች ሲሆን ከሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር ቀጥሎ ዝቅተኛ ግብ የተቆጠረበት ቡድን ነው፡፡ይህ ማለት በአማካይ በአንድ ጨዋታ አንድ ጎል እንኳን የማይገባበት ቡድን ነው ማለት ነው፡፡ 

ይህ አሃዝ የሚነግረን የቡድኑ የመከላከል መዋቅር በጣም ጠንካራና ተጋጣሚ ቡድኖች በቀላሉ ሊሰብሩት የማይችሉት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የማጥቃት ስልቱ ደግሞ መልሶ ማጥቃት ሆኖ ብዙ ጎሎችን ለማስቆጠር ምቹ አለመሆኑን በ30 ጨዋታዎች 26 ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩ እንደማሳያ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡

ይህ የግብ መጠን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ከወረደው ከአርባምንጭ ከተማ ቀጥሎ ዝቅተኛ ግብ ያስቆጠረ ቡድን ያደርገዋል፡፡

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት በ4-4-2 የዮሃንስ የማጥቃት ስልቱ መልሶ ማጥቃት ነው፡፡ ነገር ግን በፈጣን እንቅስቃሴና በብዙ ቅብብሎሽ የታገዘው መልሶ ማጥቃት ሳይሆን ከተከላካዮች አልያም ከግብ ጠባቂው በቀጥታ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በሚጣሉ ኳሶች (fast break counter attack) ማጥቃት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ስልት እያንዳንዱ ተጨዋች የየራሱ የስራ ድርሻ ቢኖረውም ከምንም በላይ ግን የአማኑኤል ገብረሚካኤል፣ የፍሊፕ አቮኖ እና አቻፖንግ አሞስ ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

በመልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው…

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዮሐንስ የማጥቃት ስልት መልሶ ማጥቃት ሆኖ በአብዛኛው ከተከላካዮች አልያም ከግብ ጠባቂው በቀጥታ ለአጥቂዎቹ በሚጣሉ ኳሶች የግብ እድሎች የሚፈጥር ነው፡፡ ይህን ስትራቴጂ ( ስልት)  ውጤታማ ለማድረግ ረጅም ኳስ የመጫወት እና ጨዋታውን በቶሎ መረዳት የሚችሉ ተጨዋቾችን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ 

በዚህ ረገድ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ባለፈው የውድድር ዓመት ሶስት ተጨዋቾችን ማለትም ስልቱን መፈፀም የቻሉትን ግብ ጠባቂውን ፍሊፕ አቮኖ፤ ተከላካዩን አቻፖንግ አሞስንና አጥቂውን አማኑኤል ገብረ ሚካኤልን መያዙ የ2010 የውድድር ዓመት ስኬታማ እንዲሆን አግዞታል፡፡ 

ምክንያቱም ፍሊፕ አቮኖ እና አቼምፖንግ አሞስ የተሳኩ ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂው አማኑኤል ገብረ ሚካኤል በማድረስ በኩል ውጤታማ ነበሩ፡፡ አጥቂው አማኑኤልም ደግሞ ፍጥነቱን በመጠቀም ወደ ጎል በአብዛኛው በረጅም የሚጣሉለትን ኳሶች ወደ ግብ በመቀየር የማጥቃት ስልቱ ውጤታማ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅ አበርክቷል፡፡ 

የሁለቱ አማካዮች ሚና…

በዚህ ፎርሜሽን ዐመለ ሚልኪያስ/ሐብታሙ ተከስተ እና ሚካኤል ደስታ በመሃል አማካይነት ይሰማራሉ፡፡ ታዲያ የሁለቱ የመሃል አማካዮች ሚና የተጋጣሚ ቡድን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዳይወስድ ማድረግና ለመሃል ተከላካዮቹ ሽፋን መስጠት ነው፡፡ በአመዛኙ የመከላከሉን ስራ ሲሰሩ በማጥቃት ውስጥ የሚኖራቸው ሚና በእጅጉ ውስን ነው፡፡

ይብዛም ይነስ እነዚህ ተጨዋቾች አቅማቸው በፈቀደ መጠን በአሰልጣኙ የተሰጣቸውን ግዳጅ ተወጥተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የመስመር አማካዮቹ ደግሞ እየተፈራረቁ በመስመር በኩል ማጥቃት ላይ በመሳተፍ አጥቂዎችን ያግዛሉ ነበር፡፡ የዚህ ድምር ውጤት ዮሃንስን ውጤታማ አድርገውታል፡፡ 

ዘንድሮስ?

አሰልጣኙ ዘንድሮ ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት እየመራ አምስት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ እስከ አሁን ሶስት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን በመጀመሪያው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ 2ለ1 መሸነፉ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጨዋታ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እንደ አምናው ሁሉ 4-4-2 ፎርሜሽንን ሲጠቀም ተመልክተናል፡፡

ባለፈው የውድድር አመት በዚሁ ፎርሜሽን ስኬታማ ግዜ እንደማሳለፉ ዘንድሮም 4-4-2 መጠቀሙ ትክክል መሆኑ አያከራክርም፡፡ ግን ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ በአምናው የመከላከልና የማጥቃ ስልት ለመጫወት የማያስችሉ እንከኖች እንዳሉበት ያየንበት ተመልክተናል፡፡

ዮሐንስ መቐለንበዋና አሰልጣኝነት እየመራ ይጫወት የነበረውን የመልሶ ማጥቃት ጨዋታ ለመጫወት እንደ ፍሊፕ አቮኖና አቻፖንግ አሞስን እንደ አጥቂው አማኑኤልን ወይም እንደ እነሱ ያሉ ለስልቱ ምቹ ተጨዋቾችን ያጣ ይመስለኛል፡፡ 

ይህ ማለት ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዎቻቸው በትክክል የሚያደርሱ ተከላከዮችና አጥቂዎች እንዲሁም ግብ ጠባቂ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ድሬዳዋ ከተማ እንዲህ አይነት ተጨዋቾች እንደሌሉት ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር አይተናል፡፡

በወቅቱ 4-4-2 ፎርሜሽን ይዞ የገባ ሲሆን ስልቱን ለማስፈፀም የሚችሉ ተጨዋቾች ባለመኖራቸው ነገሮች ባሰበው መንገድ ሊሄዱለት አልቻሉም፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው አጋማሽ አጥቂውን ሐብታሙ ወልዴን በማስወጣት በእሱ ምትክ በመስመር አማካይነት ይጫወት የነበረው ኃይሌ አሸቱን ወደ ፊት አጥቂነት ቀይሮታል፡፡ አሰልጣኙ ይህንን ያደረገው ኃይሌ እሸቱ በመስመር በኩል የነበረው መከላካል ደካማ ስለሆነበት ሲሆን ገናናውን ቀይሮ በማስገባት በቀኝ መስመር በኩል የነበረውን ክፍተት ለማጠናከር ሞክሯል፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሃይሌ እሸቱን አስወጥቶ የግራ መስመር ተከላካዩን ወሰኑ ማእዜን አስገባ፡፡ የዚህን ግዜ ፎርሜሽኑ ወደ 5-4-1 ተቀየረ፡፡

ከ4-4-2 ወደ 5-4-1

ድሬደዋ ከተማ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠሩን ተከትሎ ውጤቱን ለማስጠበቅ ከ4-4-2 ፎርሜሽን ወደ 5-4-1 ቀይሮታል፡፡ ይህ በሆነ በአጭር ግዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠሩ በድጋሚ ወደ 4-4-2 ፎርሜሽን ለመመለስ ተገዷል፡፡ የዚህን ግዜ በመስመር አጥቂነት ይጫወት የነበረው ራምኬል ሎክ በፊት አጥቂነት እንዲጫወት ተደርጎ ወሰኑ ማዜ ደግሞ ከግራ መስመር ተከላካይነት ወደ ግራ መስመር አማካይነት አሸጋሽጎታል፡፡

አሰልጣኙ ይህንን ሁሉ ለውጥ ማድረግ የፈለገው ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ይመስል ነበር፡፡ ነገር ግን የታክቲኩን ትርጓሜ እውን ማድረግ የሚችሉ ተጨዋች በቡድኑ ውስጥ ባለመኖራቸው የተፈለገው ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ድሬዳዋ በዮሐንስ ግዜ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ ሲሆን የጨዋታ መዋቅሩም ሊስተካከል የሚችል ስላልመሰለው ቡድኑን ለመልቀቁ አንደኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

ማጠቃለያ

ስለዚህ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከድሬዳዋ ጋር የነበረውን የአጭር ጊዜ ቆይታ ያጠናቀቀው ከደጋፊው ተቃውሞ ባሻገር የታክቲክ ጉዳይ እንዳለበት መገመት ይኖርብናል፡፡ 


*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡

*ለጸኃፊው ያለዎትን አስተያየት በዚህ ኢሜይል አድራሻ መላክ ይችላሉ | zeray.eyassu@gmail.com


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *