ሪፖርት | መከላከያ እና ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

ረፋድ 04፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የ11ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደረጉት መከላከያ እና ስሑል ሽረ 2-2 ተለያይተዋል።

መከላከያ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረታበት የአስረኛ ሳምንቱ ጨዋታ አበበ ጥላሁን ፣ በኃይሉ ግርማ እና ፍቃዱ ዓለሙን አሳርፎ በምትካቸው ሽመልስ ተገኝ ፣ ዳዊት ማሞ እና ምንይሉ ወንድሙን አሰልፏል። ከደቡብ ፖሊስ ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበሩት ሽረዎች ደግሞ ሰንደይ ሮቲሚን እና ኪዳን አሰፋን በሀፍቶም ቢሰጠኝ እና አሸናፊ እንዳለ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው እንደጀመረ ነበር ግብ ያስተናገደው። ከአብዱሰላም አማን የተነሳውን ኳስ አሸናፊ እንዳለ ከቀኝ መስመር ወደ መከላከያ የግብ ክልል ሲልከው በይድነቃቸው ኪዳኔ እና ምንተስኖት ከበደ መካከል የነበረውን አለመግባባት በመጠቀም ልደቱ ለማ ሽረን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል። በጊዜ ግብ ማስተናገዳቸው ያደናገጣቸው የሚመስሉት መከላከያዎች በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ተጭነው ቢጫወቱም ተረጋግተው በተደራጀ መንገድ ለማጥቃት ጊዜ ወስዶባቸዋል። በነዚህ ደቂቃዎችን ፍፁም ገብረማርያም ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደ ላይ የተነሳበት እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቅጣት ምት ያደረጓቸው ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።

እንግዶቹ ሽረዎች ግቧን ካገኙ በኋላ ወደ ፊት አጥቂዎቻቸው ኳሶችን በቶሎ ለማድረስ ጥረት አድርገዋል። በተለይም ከግራ መስመር ይነሳ የነበረው ግብ አስቆጣሪው ልደቱ ከኢብራሒማ ፎፋና ጋር በመሆን ከመከላከያ የኋላ ክፍል ጀርባ ለመግባት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። 20ኛው ደቂቃ ላይ ተጫዋቹ ያገኛቸው ሁለት አጋጣሚዎችም ወደ ግብነት የመቀየር ዕድል ነበራቸው።ልደቱ በቅድሚያ ፎፋና ከቀኝ መስመር ያሻማለትን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ኳሷ የግቡን አግዳሚ ታካ ስትወጣ ከሰከንዶች በኋላ ከይድነቃቸው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ የላከውም ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ከነዚህ ሙከራዎች በኋላ ሽረሮች በብዛት በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን የመረጡ ሲሆን አልፎ አልፎ ግን ከነአሸናፊ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር።

ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ሽረ የሜዳ አጋማሽ ለመግባት ክፍተቶችን ሲፈልጉ የነበሩት መከላከያዎች ተጋጣሚያቸው ከራሱ ሜዳ እንዳይወጣ ቢያደርጉም ወደ ሳጥኑ ውስጥ መግባት ግን ከብዷቸው ነበር። ምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ታዬ ከሳጥን ውጪ ከሚያደርጓቸው ሙከራዎች በተጨማሪ ቡድኑ በረጅሙ ወደ ፊት የሚልካቸው ኳሶች የተመጠኑ ሳይሆኑ እየቀሩ ይባክኑ ነበር። 32ኛው ደቂቃ ላይ ግን ምንይሉ በቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የላካትን ኳስ በሽረ ተከላካዮች መሀል ይገኝ የነበረው ፍፁም ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ምንይሉ 45ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሜ ከግራ በኩል ወደ ሳጥን ገብቶ ለዳዊት ማሞ የሰጠውም ኳስ ሁለተኛ ግብ ሆነ ተብሎ ቢጠበቅም የዳዊት ሙከራ በግቡ አናት ወጥቷል። በዚሁም ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፍቃዱ ዓለሙን በዳዊት ማሞ ቀይረው የገቡት መከላከያዎች ከባድ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ። 47ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ታፈሰ ሰረካ ከምንይሉ ተቀብሎ ከሞከረው ኳስ ሀፍቶም ከራሱ ተጫዋች ኳስ በእጁ በመቀበሉ ለመከላከያ ሁለተኛ ቅጣት ምት አስገኝቷል። ሆኖም በተመሳሳይ ሁኔታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛ ቅጣት ምት አግኝተው የነበሩት ባለሜዳዎቹ ይህንንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። እንደመጀመሪያ ሁሉ በራሳቸው ሜዳ ላይ ይታዩ የነበሩት ሽረዎችም በድንገተኛ ረጃጅም ኳሶች አደገመፍጠር እንደሚችሉ ያሳዩባቸውን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ወደ ሙከራነት የተቀየሩ አልነበሩም።

መከላከያዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 55ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ከምንይሉ በደረሰው ኳስ ከቅርብ ርቀት ያደረገውን ሙከራ ሀፍቶም ለጥቂት አድኖበታል። ሆኖም የፊት አጥቂው ከደቂቃዎች በኋላ ያገኘውን ዕድል ተጠቅሞበታል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያደረገው ሙከራ ሲደረብ ነበር ፍፁም ደርሶ ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር የቻለው። መከላከያዎች በዚህ ግብ ቀዳሚ ከሆኑ በኋላ የጨዋታው መንፈስ ተቀይሯል። ኪዳኔ ረሰፋን ቀይረው በማስገባት በቀኝ በኩል ለመግባት ይጥሩ የነበሩት ሽረዎች ለማጥቃት በጦሩ ሜዳ ላይ የሚታዩባቸው ደቂቃዎች ሲበራከቱ በአንፃሩ ወደ ኋላ ሸሸት ያሉት መከላከያዎች ደግሞ ጥሩ የመልሶ አጋጣሚዎች ሲፈጠርላቸው ታይቷል። በተለይም 66ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ከመሀል የጣለውን ኳስ ተጠቅሞ ምንይሉ ግልፅ የግብ ዕድል ያገኘበት ሙከራ ተጠቃሽ ቢሆንም ኢላማውን መጠበቅ ግን አልቻለም።

የማጥቃት ኃይላቸውን በሙሉ ለመጠቀም ሲሞክሩ ይታዩ የነበረሩት ሽረዎች ሙከራዎችን በብዛት ማድረግ ባይችሉም 72ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጦሩ ሳጥን በገቡበት ጊዜ ግን ተሳክቶላቸዋል። ከተከላካዮች ጋር ሲታገል የነበረው ፎፋና የጨረፈለትን ኳስ አክርሮ መትቶ ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው ደግሞ ተቀይሮ የገባው ኪዳኔ አሰፋ ነበር። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የጨዋታው ግለት ከፍ ብሎ ሁለቱም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የደረሱባቸው እንቅስቃሴዎች የታዩባቸው ነበር። የፉክክሩ ሳቢ መሆን እንዳለ ሆኖ ግን ሙከራዎች በብዛት አልታዩም። ታፈሰ ሰረካ 86ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ያደረገው ሙከራ እና ጭማሪ ደቂቃ ላይ አዲሱ ተስፋዬ ከማዕዘን ምት በተሻገረ ኳስ ያደረገው የግንባር ሙከራ ብቻ የተሻሉ ነበሩ። ከአዲሱ መከራ በኋላም የጨዋታው ውጤት ሳይቀየር 2-2 ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *