የግል አስተያየት | የጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዘመኑ የእስካሁን ጉዞ…

አስተያየት በቴዎድሮስ ታደሰ

በ2010 ከከፍተኛ ሊጉ ባደገበት ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን መሆን የቻለው ጅማ አባ ጅፋር በዘንድሮው የውድድር ዓመት በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገውን ተሳትፎ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሀሳኒያ አጋዲር ተሸንፎ ቋጭቷል። አባ ጅፋር የአምና ቻምፒዮንነት የሚለውን ስያሜ ይዞ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ወሳኝ ተጫዋቾቹን አጥቶ፣ አሰልጣኙን እና አመራሮቹን በአዲስ ተክቶ በመሆኑ ለብዙሀኑ የስጋት ምንጭ የነበረ ቢሆንም ይህ አካሄዱ ከአምናው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ተከትሎ በዚህ ዓመት ላይቸገር እንደሚችልም ተገምቶ ነበር።

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን 13 የነጥብ ጨዋታዎችን አከናውኖ በሶስቱ ሲያሸንፍ አራት አቻ ተለያየቶ በስድስት ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል። 10 ሲያስቆጥር 16 ጎሎችን አስተናግዷል። (አምና በሙሉ ዓመት ከተቆጠረበት ጎል በአንድ ይበልጣል)። ቡድኑ በዓመቱ መጀመርያ ላይ እንደመገኘቱ እና ደረጃቸው ከፍ ካሉ የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ጋር አራት ጨዋታ እንደማድረጉ ከወዲሁ እነዚህን የቁጥር ማሳያዎች ከአምናው ጋር በማነፃፀር የቡድኑን ወቅታዊ ሁኔታ መገምገም አስቸጋሪ ቢሆንም በሜዳ ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ፣ ከሜዳ ውጪ ያሉ አለመረጋጋቶች እና የቅድመ ዝግጅት ጉድለቶች ጅማን ከባድ የውድድር ዓመት ጅማሮ እንዲያደርግ፣ ቀጣዩ ጊዜም የበለጠ ፈታኝ እንዲሆን የሚያደርገው ነው።

የአጨዋወት ዘይቤ

ባሳለፍነው ዓመት በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ስር በነበረበት ወቅት ይጠቀም የነበረው የአጨዋወት ዘይቤ ቀጥተኛ የማጥቃት ስልት ላይ የተመሰረተ ሆኖ በአመዛኙ በቀኝ መስመር የሚሻገሩ ኳሶች ዋነኛ የማጥቃት አማራጩ ነበር። በመከላከሉ በኩል በዓመቱ ጥሩ የተከላካይ ጥምረት ከነበራቸው ክለቦች ውስጥ ግባር ቀደሙ ነበር። የአማካይ ክፍሉ ለተከላካይ ክፍሉ በሚሰጠው ሽፍን እና ወደ ማጥቃት በሚያደርው ሽግግር ፍጥነት የገብረመድኅን ቡድን ውጤታማ ነበር። ቡድኑም በአንዳንድ የታክቲክ ለውጦች ምክንያት ካልሆነ በቀር  በ4-4-2 አሰላለፍን ይጠቀም ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ሁለት የተለያየ ጠንካራ ጎን የነበራቸው የተመስገን እና ኦኪኪ የሰመረ ጥምረት ቡድኑ ከፊት ስል እንዲሆን ረድቶታል። እንደ ሁለቱ አጥቂዎች ሁሉ መሀል ላይም ይሁን እና አሚኑ የተጣጣመ ቅንጅት መፍጠራቸው ዓመቱን ሙሉ በሚያስብል መልኩ የማይለዋወጥ የመጀመሪያ አሰላለፍ የተጠቀመው አባ ጅፋርን የቡድን ውህደት ከፍ አድርጎት ነበር። የውህደቱ ከፍታም በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት ፣ መሀል ላይ በቶሎ ኳስ የሚያስጥል እና ተጋጣሚው የኋላ ክፍሉን ከማደራጀቱ በፊት በፍጥነት ገብቶ ግብ የሚያስቆጥር ነበር።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ግን ቡድኑ ይህ ነው የሚባል የጨዋታ ፍልስፍናም ሆነ አተገባበር አይታይበትም። አልፎ አለፎ መስዑድ መሐመድ ከጉዳት ነፃ ሆኖ በአሰላለፍ ውስጥ ከተካተተ ኳስን በመቆጣጠር የተጋጣሚ ተከላካዮችን አስከፍተው በመግባት ለማስቆጠር ይሞክራሉ። መስዑድ ወደ ሜዳ ባልገባባቸው ጨዋታዎች ደግሞ ኄኖክ ገምቴሳን አልያም ንጋቱ ገብረሥላሴን በሚጠቀሙበት ወቅት በአመዛኙ ወደ ኋላ በመሳብ ውጤታማ ያልሆኑ ቅብብሎችን ሲከውኑ ሦስቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ዲዲየ ለብሬ ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አስቻለው ግርማ በግል የሚያደርጓቸው እቅስቃሴዎች ብቻ የጥቃት ምንጮቹ ሲሆኑ ይስተዋላሉ።

ቡድኑ በአብዛኛው በ4-3-3 ቢጠቀምም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ከቡድኑ በመነጠላቸው (ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ባለመሆናቸው) ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች ወደ ኋላ በመሳብ የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-5-1 ሲቀይሩት ይታያል። በዚህ ጊዜ በሌላ የአጨዋወት ስልት ከርቀት የሚጣሉ ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀም ቡድኑ ቅርፅ አልባ ሲሆን እና የተጫዋቾቹን ጉልበት ለብክነት እንዲሁም ለጉዳት ሲዳርግ ይታያል።

ደካማ ቅድመ ዝግጅት 

ቡድኑ ከሀሳኒያ አጋዲሩ ጨዋታ በፊት ባሉ 13 ቀናት ውስጥ በፕሪምየር ሊጉ አራት ጨዋታዎች ማድረጉን ተከትሎ ከምክትል አሰልጣኙ ዩሱፍ ዓሊ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሲሰማ የቆየው ተደጋጋሚ ቃል ” የጨዋታ መደራረብ ” የሚል ምሬት የተቀላቀለበት አስተያየት ነበር። በእርግጥ በኢትዮጵያ እግርኳስ ደረጃ ቡድኑ “የጨዋታ መደራረብ” ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በርካታ ጨዋታዎችን በጥቂት የጊዜ ልዩነቶች ለማድረግ ተገዷል። ሆኖም ቡድኑ የአምና ቻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ በአፍሪካ ውድድር እንደሚሳተፍ እየታወቀ በስብስብ በመጠናከር፣ በአዕምሮ በመዘጋጀት እና ተስማሚ የልምምድ መርሐ ግብር እና የጨዋታ እቅዶችን በማዘጋጅት ለተደራራቢ ጨዋታዎች ራሱን ማዘጋጀት ነበረበት። ዘንድሮ ካፍ የፎርማት ለውጥ በማድረጉ ከዚህ ቀደም ከነበረው በእያንዳንዱ ዙሮች እና የደርሶ መልስ መካከል የሚኖረው የጊዜ ክፍተት ቀንሷል። ይህን የጊዜ መጣበብ አስቀድሞ መረዳትም የክለቡ ስራ ሊሆን ይገባ ነበር።

ቡድኑ ከጨዋታ መደራረብ በተጨማሪ “የአምና ቻምፒዮን” የሚል ስም ይዞ ጨዋታዎችን ማድረጉ ለማሸነፍ የሚፈለግ ለተጋጣሚዎች የመነሳሳት ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው። ቡድኑ የተሟላ ቢሆን እንኳን የአምናን ክብር ይዞ መቀጠል ቀላል አይሆንለትም። ከተጋጣሚዎች አስቸጋሪ ሆኖ መቅረብ በተጨማሪ የትኩረት ማዕከል መሆን እና በደጋፊዎቹ ዘንድ ቢያንስ እንደ አምናው እንኳን ባይሆን እስከመጨረሻው እንዲፎካከር መጠበቅ ጫና ውስጥ እንደሚከተው አስቀድሞ በመረዳት ቡድኑ በአዕምሮ በሚገባ እንዲዘጋጅ መደረግ ነበረበት።

ስብስብ

ባለፈው የውድድር ዓመት ከሁሉም ክለቦች በላቀ ሁኔታ ጅማ አባ ጅፋር ከ15 በላይ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም አመዛኞቹ ተጫዋቾች ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ዋንጫውን እንዲያነሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከአምበሉ ኤልያስ አታሮ እና አጥቂው ተመስገን ገብረኪዳን ውጪ ያሉት ተጫዋቾች (አሰልጣኙን ጨምሮ) በአጠቃላይ በአዲስ መልክ ክለቡን መቀላቀላቸውን ስንመለከት ዘንድሮም ቡድኑ ተመሳሳይ መንገድ በመከተል ውጤታማ ጉዞ ለማድረግ ማለሙ ዋጋ ያስከፈለው ይመስላል። አብዛኛዎቹ ወሳኝ ተጫዋቾች በአዲስ ሲተኩ አሰልጣኝ ገብረመድኅንም በዘማርያም ተተክለዋል።

ክለቡ በክረምቱ በርካታ ተጫዋቾችን በመልቀቁ በምትኩ ውጤታማነቱን የሚያስቀጥሉ ተጫዋቾችን መልምሎ ከማምጣት ይልቅ ጥድፊያ በተሞላበት መልኩ እጅግ በርካታ ተጫዋቾችን አስፈርሟል። በጉዳት ላይ የነበሩ፣ በቡድኑ እና ሊጉ የጥራት ደረጃ ላይ የማይገኙ አዳዲስ ተጫዋቾች ገና በዝግጅት ወቅት መሰናበታቸውም የክለቡ የጥድፊያ ስራን የሚያሳይ ነበር። የውድድር ዓመቱ ከተጀመረ በኋላም እስካሁን በጉዳት እና አቋም ምክንያት አንድም ጨዋታ ማድረግ ያልቻሉ ተጫዋቾች መኖራቸው ስብስቡ ያልተሟላ እና አማራጮች የጠበቡበት እንዲሆን አድርጎታል። በሀሳኒያ አጋዲሩ የመልስ ጨዋታ በቡድኑ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩት አራት ተጫዋቾች ብቻ መሆናቸውም የዘንድሮውን ቡድን አወቃቀር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከተው ነው።

በጉዳት እና በአቋም ምክንያት ቡድኑን ማገልገል ካልቻሉ ተጫዋቾች ውጪ ያለው የቡድን ስብስብን በግርድፉ ስንመለከተው በልምድ ረገድ ከአምናው የተሻለ ቢሆንም በወቅታዊ ብቃትም ሆነ ተነሳሽነት ረገድ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የወረደ ነው። አምና ከከፍተኛ ሊግ የመጡ እንዲሁም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙ እና በሊጉ የመጫወት ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረው ቡድን ከፍተኛ ተነሳሽነት የነበረው ሲሆን የዘንድሮው ደግሞ በተቃራኒው ረጅም ዓመት በመጫወት የሚመጣ የተነሳሽነት ማነስ የሚታይበት ነው።

ዘ-ማርያም ወልደጊዮርጊስ

አሰልጣኙ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ወልዲያ ከተማ በነበሩበት ወቅት በሚያዝያ ወር በፌዴሬሽኑ የአንድ ዓመት ቅጣት ተላልፎባቸው ከቡድኑ ጋር መለያየታቸው ይታወሳል። ገብረመድኅንን ያጣው ጅማ አባ ጅፋር ቅጣታቸውን ያላገባደዱት ዘማርያምን በአሰልጣኝነት ሲቀጥር ከፊቱ ከሚጠብቀው ከባድ የውድድር ዘመን አንፃር ሪስክ መውሰዱ ጥርጥር የለውም። በፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ቡድናቸውን በአሰልጣኞች መቀመጫ ላይ ተቀምጠው መምራት ተጽዕኖ መፍጠሩ የማይቀር ነው። ከዚህ በተጨማሪም አሰልጣኙ ደሞዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ስራ እስከማቆም በመድረስ በሙሉ ልባቸው ስራቸው ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓቸዋል።

አስተዳደራዊ ክፍተቶች 

በአብዛኛዎቹ የሀገራችን ክለቦች ላይ እንደሚስተዋለው ከሜዳ ውጭ ያሉ አስተዳደራዊ ስራዎች ትኩረት ሲሰጣቸው አንመለከትም። ቡድኖች እቅዳቸው እና ግባቸው አይታወቅም። በአንድ የውድድር ዓመት ምን ለማሳካት እንደሚወዳደሩ እና በምን ያህል በጀት ውድድሮችን እንደሚያካሂዱ የሚያሳዩ አቅጣጫዎች የላቸውም። ከነዚም መካከል አምና ቻምፒዮን የሆነውን ጅማ አባጅፋር እንደማሳያነት ብንወስድ በቡድኑ አመራሮች በኩል ለሚቀጥለው የውድድር ዘመን ሀገርን ወክሎ በአፍሪካ መድረክ እንደሚሳተፍ እየታወቀ አሰልጣኙን ጨምሮ በርከት ያሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾችን ማቆየት አለመቻላቸው፣ በለቀቁባቸው ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ምትክ የሚጠብቃቸውን ውድድሮች ታሳቢ ያደረጉ የተጫዋቾች ምልመላ አለመደረጉ ዋንኛው ድክመት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ተደጋጋሚ አስተዳደራዊ ድክመቶችን ሲያሳይ ተስትውሏል። የደሞዝ ክፍያ መዘግየት፣ አል አህሊን ለመግጠም ወደ ግብፅ ለማምራት በተዘጋጀበት ሰዓት በጉዞ ትኬት አለመመቻቸት ጨዋታው በሚደረግበት ዕለት አሌክሳንድሪያ መድረሳቸው እና ወደ አጋዲር በተጓደለ የልዑክ ቡድን መጓዛቸውን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

እነዚህ ክፍተቶች እና ሌሎች ችግሮች በቡድኑ አመራሮች በጊዜ እልባት ካልተሰጣቸው ምናልባትም አምና ለቻምፒዮንነት የተጫወተው ቡድን ዘንድሮ የውጤት ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ያሰጋል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ጥር ወር ላይ በ15 ቀናት ውስጥ አራት ጨዋታዎችን ሲያከናውን የካቲት ወር ላይ ደግሞ በ18 ቀናት ውስጥ 5 ጨዋታዎችን ያደርጋል። የአንደኛው ዙር አልቆ ቡድኖች እረፍት ላይ ሲገኙ እንኳን ጅማ አባጅፋር በጨዋታ ላይ የሚጠመድ መሆኑ እንዲሁም ተጋጣሚዎቹ ከመደበኛ መርሐ ግብር ውጪ የጨዋታ ጫና የሌለባቸው መሆኑ ሲታሰብ ቀጣዩን ጊዜ ከባድ ያደርገዋል።

ከላይ የተጠቀሱት የቅድመ ዝግጅት ድክመቶች ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍለው እንደመቆየቱ አሁንም ከፊቱ በሚጠብቁት ቀሪ ጨዋታዎች የተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘት ራሱን በቅጡ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። የቡድን ስብስቡን በአግባቡ መጠቀም፤ የቡድኑን ትኩረት የሚበታትኑ አስተዳደራዊ ችግሮችን መቅረፍ እንዲሁም የተጫዋቾችን እና የቡድኑን አቋምና ተነሳሽነት ማሻሻል ቀጣዩ የቤት ስራ ሊሆን ይገባል።


*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *