ሪፖርት | ደደቢት እና አዳማ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

ዛሬ በተደረገው ብቸኛ የ11ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት እና አዳማ ከተማ አቻ ተለያይተዋል።

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በሳምንት አጋማሽ በፋሲል ከተሸነፉበት ስብስብ በሙሉጌታ ብርሃነ፣ አብርሀም ታምራት እና በመጨረሻ ሰዓት ጉዳት ያጋጠመው አቤል እንዳለ በአሌክሳንደር ዐወት፣ ኩማ ደምሴ እንዳለ ከበደ ሲተኩ እንግዶቹ አዳማዎች በበኩላቸው ባለፈው ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈው ስብስባቸው በሱራፌል ዳንኤል እና ከነዓን ማርክነህ ምትክ ሱሌይማን ሰሚድ እና ዐመለ ሚልክያስ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኳስን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ያልተሳኩ ጥረቶች የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያ ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ከአዳማ ከተማዎች የተሻለ ወደ ግብ ሲደርሱ በጨዋታው ግብ ለማስቆጠርም ብዙ ግዜ አልፈጀባቸውም። በግቡ አቅራብያ የተገኘውን ቅጣት ምት እንዳለ ከበደ መትቶ ሮበርት ኦዶንካራ ሲተፋው ከግቡ ፊት ለፊት የነበረው ዳዊት ወርቁ በማስቆጠር ሰማያዊዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።


ጨዋታው ከተጀመረ አንስቶ መረጋጋት ያቃተው የአዳማ ተከላካይ መስመር ምንም እንኳ ከተጋጣሚ አጥቂዎች ከባድ ፈተና ባይገጥመውም በተለይም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እጅግ ተጋልጦ እና ረጃጅም ኳሶችን ለመከላከል ተቸግሮ ታይቷል። እንዲያም ሆኖ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በርካታ የጠሩ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በበረከት ደስታ እና ቡልቻ ሹራ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። በተለይም የቡልቻ ሹራ ድንቅ ሙከራ ዳዊት ወርቁ ደርሶ ባያድናት አዳማን አቻ የምታደርግ ሙከራ ነበረች።

በደደቢት የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች የተጨናነቀውን የመሐል ክፍል አልፈው በሜዳው ቁመት በመጠቀም ወደ ግብ መቅረብ የተሳናቸው አዳማዎች የማጥቃት እንቅስቅሴያቸውን ወደ መስመር ካደረጉ በኋላ የተሻለ በመንቀሳቀስ አቻ የምታደርጋቸው ኳስ አስቆጥረዋል። አዲስ ህንፃ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ የተሻማሽለት ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ ከፍ አደርጎ መትቶ በማስቆጠር አዳማ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።

ደደቢቶች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ ወደ ፊት ገፍተው እና የአዳማ ተከላካዮች ከጀርባቸው የሚተውት ክፍተት ለመጠቀም በረጃጅም በሚጥሏቸው ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ በርከት ያሉ ዕድሎችም ፈጥረዋል። ዳዊት ወርቁ ከርቀት መቷት ለጥቂት የወጣችው እና በዓለምአንተ ካሳ ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር አዳማ ሳጥን ውስጥ የተፈጠረችው መለከራዎችም ይጠቀሳሉ። በአንፃሩ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተዳከሙት አዳማዎች በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ አማካኝነት መርተው ወደ ዕረፍት የሚያመሩበት ዕድል አግኝተው ነበር።


በረከት ደስታ በድንቅ ሁኔታ አሻምቶት በግቡ አፋፍ ላይ የነበረው ዳዋ ሆቴሳ ባመከነው ወርቃማ ዕድል የጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በርካታ ሙከራዎች ያልታዩበት እና በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተጠና የማጥቃት አጨዋወት ያልታየበት ነበር። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ወደ ግብ የቀረቡት አዳማዎች ከመጀመርያው ሙከራ ብዙም ሳይቆዩ በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ከቅጣት ምት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ረሺድ ማትውሲ በድንቅ ብቃት ወደ ውጭ አውጥቷታል።

ዘግይተው ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ደደቢቶችም ተደጋጋሚ ግዜ ከርቀት ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም መድሃኔ ብርሃኔ እና ተቀይሮ የገባው አብዱልዓዚዝ ዳውድ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በመጨረሻዎቸ ደቂቃዎች ረጃጅም ኳሶች ምርጫቸው ያደረጉት ደደቢቶች በአሌክሳንደር ዓወት እና አለምባንተ ካሳ ሙከራዎች ሲያደርጉ እንግዶቹ አዳማዎች በበኩላቸው በረከት ደስታ የተከላካዮች ትኩረት ማጣት ተጠቅሞ ሁለተኛው አጋማሽ ከተፈጠሩት ዕድሎች የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎ ነበር።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎ ደደቢቶች በተከታታይ ሁለት የሜዳ ጨዋታቸው አራት ነጥብ ሲያመዘግቡ አዳማዎች በበኩላቸው  ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *