ሪፖርት | የባህር ዳር እና ፋሲል ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ቀን ውሎ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሁለት ከተሞች ክለቦችን ያገናኘው የባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ፍልሚያ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ወደ መቐለ ተጉዘው በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ ግርማ ዲሳሳን በማራኪ ወርቁ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ ተጋባዦቹ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ወላይታ ድቻን ካሸነፉበት ጨዋታ በዬሴፍ ዳሙዬ፣ ኤፍሬም ዓለሙ እና ኢዙ አዙካ ምትክ በሱራፌል ዳኛቸው፣ ኤዲ ቤንጃሚን እና ሰለሞን ሐብቴ አሰልፈው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የባህር ዳር ከተማ የደጋፊዎች ማህበር ለፋሲሎች በአምበላቸው ደረጄ መንግስቱ አማካኝነት ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን ስጦታውን የፋሲል ከነማው አምበል ያሬድ ባየ ተረክቧል። ሁለት መልክ በነበረው ጨዋታም በመጀመሪያ አጋማሽ ዐፄዎቹ ተሽለው ሲንቀሳቀሱ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ የጣናው ሞገዶቹ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል።

እንደ ስታዲየሙ ድባብ ሁሉ ሞቅ ብሎ የጀመረው ጨዋታው በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የፋሲል ከነማ ብልጫ ታይቶበታል። ሁለቱም ቡድኖች መስመር ላይ ያደርጉት የነበረው ፍትጊያ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የወሰደ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች ግን የመስመር አጥቂዎቻቸውን ቦታ (አብዱራህማን እና ሽመክት) በየተወሰኑ ደቂቃዎች በመቀያየር ብልጫ በመውሰድ ተንቀሳቅሰዋል። ፋሲሎች በእነዚህ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የወሰዱትን የበላይነት በጎል ለማሳመር የሚያስችል በ6ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የክለቡ ደጋፊዎች በስታዲየሙ ልደቱን ያከበሩለት ያሬድ ባየ የፍፁም ቅጣት ምቱን አምክኖ ገና በጊዜ መሪ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በደቂቃ ልዩነት ፋሲሎች በሱራፌል ዳኛቸው የቅጣት ምት ሌላ ግብ ሊያስቆጥሩበት የሚችሉበት አጋጣሚ ፈጥረው ሐሪስተን ሄሱ አውጥቶባቸዋል። ሙከራ መሰንዘራቸውን ያላቆሙት የውበቱ አባተ ተጨዋቾች በ10ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ለሰለሞን ሐብቴ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅመው አሁንም መሪ ለመሆን ቢጥሩን ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች በ15ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ለጃኮ አራፋት ባመቻቸለት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ያሬድ ባየ ወደ ውጪ አውጥቶባቸዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ማራኪ ወርቁ ወደ ግብ ከርቀት የሞከረው ኳስ ተጨራርፎ ጃኮ እግር ስር ሲደርስ ኳሱን ጃኮ ወደ ግብ በቀጥታ ቢመታትም ኳሱ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ከመባል የዘለለ ትርጉም ሳትሰጥ መክናለች።

የፋሲል የአጥቂ መስመር ተጨዋቾች ቦታ እየተቀያየሩ የባህር ዳርን የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ትኩረት በመበተን የግብ ሙከራዎችን በተደጋጋሚ ለማድረግ ቢችሉም ፍሬ ማፍራት ግን አልቻሉም። በ18 እና በ24ኛው ደቂቃ ባህር ዳሮች ከቆመ ኳስ በወሰኑ ዓሊ እና በደረጄ መንግስቱ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገው ሚኬል ሳማኪ አድኖባቸዋል። የፋሲል የመስመር ተጨዋቾች የባህር ዳር የመስመር አጥቂዎች እና ተከላካዮች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ተገድበው እንዲቆዩ በማድረግ ሲሰነዘርባቸው የነበረውን ጫናዎች በመጠኑ ማብረድ ችለዋል።

ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ቀጥተኛ አጨዋወትን በመከተል ረጃጅም ኳሶችን ለጃኮ አራፋት በመላክ የተጫወቱት ባህር ዳሮች ከ4-3-3 የተጨዋች አደራደር ወደ 4-5-1 ለውጥ በማድረግ በተለይ ወሰኑ እና ማራኪ ሁለተኛ ኳሶችን እንዲጠቀሙ በማሰብ ሙከራዎችን ለማድረግ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ይህንን አጨዋወት በሚገባ የተቆጣጠሩት ዐፄዎቹ ግብ ሳያስተናድዱ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄን መርጠው የተጫወቱት ፋሲል ከነማዎች ከአጥቂ መስመር እስከ ተከላካይ መስመር ያለውን ርቀት ወደ ኋላ በማፈግፈግ ያጠበቡት ሲሆን ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉትን ሽግግር በመጠኑ በመቀነስ ተጫውተዋል። ባህር ዳሮች በበኩላቸው በመሐል ሜዳ ላይ ያበዙትን የተጨዋች ብልጫ በመቀነስ የመሃል እና የመስመር አጥቂ ተጨዋቾችን በማስገባት ተጭነው ተጫውተዋል።

በ53ኛው ደቂቃ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት የባህር ዳሮችን መረብ ለመድፈር ቢጥርም ሃሪሰን አውጥቶበታል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ሃሪሰን ሄሱ በረጅሙ ለጃኮ አራፋት የመታውን ኳስ ጃኮ በግምባሩ ጨርፎ ተቀይሮ ለገባው ግርማ ዲሳሳይ ያቀበለው ሲሆን ግርማ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ኳሱን አምክኖታል። ይህንን አስደንጋጭ ሙከራ ያደረገው ግርማ በ67ኛው ደቂቃ ከመስመር ሌላ ኳስ ከወሰኑ ዓሊ ተሻምቶለት በግምባሩ ሙከራ ቢያደርግመወ ኳሱ የግቡን ቋሚ በመግጨት ወደ ውጪ ወጥቷል።

በጨዋታው ብልጫ እየተወሰደባቸው የመጣው ፋሲሎች የግብ ማግባት ሙከራቸውን ከቆሙ ኳሶች በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በዚህም እንቅስቃሴ በ78ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ አክርሮ መቶት ሃሪሰን አድኖታል። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይም ሁለቱም ቡድኖች አቻ ለመውጣት የሚፈልጉ በሚመስል መልኩ ጠንከር ብለው ወደ ጎል ሳይጓዙ ጨዋታቸውን ያለ ግብ አጠናቀዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *