ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳስ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ

በ12ኛው ሳምንት የሊጉ ሦስተኛ ቀን ውሎ ጅማ ላይ አባ ጅፋር ድቻን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ጅማ አባ ጅፋር ነገ በሜዳው ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል። እስካሁን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ሜዳው ላይ ለማድረግ የታደለው አባ ጅፋር አዳማ ላይ ድል ከቀናው ወዲህ ሌላ ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። ቡድኑ ምንም እንኳን  14ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ቢገደድም አምስት ተስተካካይ ጨዋታዎቹ እንዳሉ ሆነው ነገ ሁለት ደረጃዎችን ማሻሻል የሚችልበት ዕድል አለ። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ብቻ ያገኙት ወላይታ ድቻዎች ጎንደር ላይ ከደረሰባቸው የ1-0 ሽንፈት በኋላ ነው ወደ ጅማ የሚያመሩት። ድቻዎች ያላቸው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢሆንም 11ኛ ደረጃ ላይ መገኘታቸው ከነገው ጨዋታ ውጤት ይዘው እንዲመለሱ የሚያስገድዳቸው ነው። 

ጅማ አባ ጅፋር ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ከጉዳት ያልተነለሰለት ሲሆን ልምምድ የጀመረው ዐወት ገብረሚካኤልም ለነገው ጨዋታ አይደርስም። ከዚህ ውጪ የቡድኑ አምንበል እና የግራ መስመር ተከላካይ ኤልያስ አታሮም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ታውቋል። በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ኃይማኖት ወርቁ ፣ ያሬድ ብርሀኑ ፣ ተክሉ ታፈሰ እና ፀጋዬ አበራ ከጉዳት ቢመለሱም ሙሉ በሙሉ  ባለማገገማቸው  የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን  የአራት ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት እሸቱ መናም ከቡድኑ ስብስብ ውጪ ነው፡፡

ከአፍሪካ መድረክ ሽንፈቱ በቶሎ ማገገም የሚጠበቅበት ጅማ አባ ጅፋር ነገ ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገ የጨዋታ ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል። በዛው ልክ ሳምንት ነጥብ ለመጋራት ተቃርቦ በነበረው ወላይታ ድቻ በኩል ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይጠበቃል። የጅማ አባ ጅፋር ዋና የማጥቃት አማራጭ የሆኑት የመስመር አጥቂዎች የወላይታ ድቻን የኋላ መስመር አስከፍቶ ለመግባት በአማካዮቹ ድጋፍ ከሚያገኘው የድቻ የኋላ ክፍል ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ጨዋታውን ቻምፒዮኖቹ ሜዳቸው ላይ እንደማድረጋቸውም የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነም ከመስመር አጥቂዎቻቸው ባለፈ የማጥቃት ባህሪ ካላቸው አማካይዮቻቸውም የግብ ዕድሎችን ሊያገኙ ይችላሉ። ሁለት የፊት አጥቂዎችን መጠቀም ለጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ግን ወደ ፊት የሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ዋነኛ የግብ ዕድል መፍጠሪያ መንገዳቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– አባ ጅፋር ወደ ሊጉ መጥቶ ሻምፒዮን በሆነበት የ2010 የውድድር ዓመት ሜዳው ላይ ወላይታ ድቻን 2-1 ማሸነፍ ሲችል ሶዶ ላይ የተገናኙበት ጨዋታ ደግሞ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ሜዳው ላይ ባደረገው ብቸኛ ጨዋታ ከወልዋሎ ዓ/ዩ ጋር ያለ ግብ ተለያይቷል። ቡድኑ በስድስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር የቻለው በሁለቱ ላይ ብቻ ነው። 

– ከሜዳቸው ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻሉት ወላይታ ድቻዎች በሁለት አጋጣሚዎች ነጥብ ሲጋሩ አራት ጊዜ በሽንፈት ተመልሰዋል። 

ዳኛ

– ጨዋታው በ2010 የውድድር ዓመት 24ኛው ሳምንት ላይ አርባምንጭ ከተማ እና ወልዲያ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ የሚመራው ይሆናል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)                       

ዳንኤል አጄዬ

ያሬድ ዘውድነህ – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ

ኄኖክ ገምቴሳ – ይሁን እንዳሻው – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ –ኤርሚያስ ኃይሉ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

ታሪክ ጌትነት

እዮብ ዓለማየሁ – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ –  ኄኖክ አርፌጮ

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ፍፁም ተፈሪ 

አንዱዓለም ንጉሴ – ባዬ ገዛኸኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *