ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ደደቢት

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የደደቢትን የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ መቀመጫውን ወደ መቐለ ካዞረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የሚመጣው ደደቢትን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ነገ 11፡ 00 ላይ ይጀምራል። ከዛሬ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አምስተኛ ደረጃ የተንሸራተቱት ጊዮርጊሶች ከመሪው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ለማጥበብ የሚረዳቸውን ጨዋታ ነው የሚያደርጉት። ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኋላ መምጣታቸው ደግሞ በጥሩ የአዕምሮ ደረጃ ላይ እንዲገኙ እንደሚረዳቸው ይታመናል። ሳምንት አዳማ ከተማን አስተናግዶ አቻ የወጣው ደደቢት አራተኛ ነጥቡን ማሳካት ችሎ ነበር። ሆኖም ውጤቱ ከ16ኛ ደረጃው ከፍ የሚያደርገው አልሆነም።  ደደቢት በነገው ጨዋታ ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ጨዋታዎች መነቃቃትን የሚፈጥረለት ውጤትንም የሚያሳካ ይሆናል። 

በድሬዳዋው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት ገጥሟቸው የነበሩት ጌታነህ ከበደ እና አቡበከር ሳኒ ለነገው ጨዋታ ብቁ ሲሆኑ አቤል ያለውም ከጉዳት መልስ ቡድኑን እንደሚያገለግል ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የቆየው ምንተስኖት አዳነ ቢያገግምም ነገ የመግባቱ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑ ሲሰማ መሀሪ መናን ጨምሮ አብዱልከሪም መሀመድ እና አሜ መሀመድ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ አይካተቱም። በደደቢት በኩል ግን በቅጣትም እና በጉዳት ማይሰለፍ ተጫዋች የሌለ ሲሆን  ባለፈው ሳምንት በጉዳት ያልነበሩት አቤል እንዳለ እና ሙሉጌታ ብርሃነም ተመልሰዋል።

በጨዋታው የመስመር ተመላላሾቹን በሰፊው በማጥቃት ላይ የሚያሳትፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በራሱ ሜዳ ላይ መቆየትን ምርጫው የሚያደርግ ደደቢት ይጠበቃሉ። የቅዱስ ጊዮርጊስ መሀል ሜዳ ላይ ሊወሰድበት ከሚችለው የቁጥር ብልጫ አንፃር አብዛኛው የቡድኑ ጥቃቶች ከመስመር የመነሳት ዕድል ይኖራቸዋል። ለሁለቱ የፊት አጥቂዎች ዕድል የሚፈጥሩ ተሻጋሪ ኳሶች የደደቢት የኋላ ክፍል ላይ የሚፈጥሩት ጫናን ተከትሎ እንግዶቹ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ በጨዋታው ተጠባቂ ሲሆን ደደቢቶች የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ካገኙ ከጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ጀርባ ሊኖር የሚችለውን ሰፊ ክፈተት የመጠቀም አጋጣሚ ሊፈጠርላቸው ይችላል። በዚህ ሂደትም ውስጥ የቡድኑ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች የሚቀሟቸውን ኳሶች በተመጠነ መልኩ ወደ ፊት የማድረስ ኃላፊነት የጠበቅባቸዋል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 18 ጊዜ ተገናኝተዋል።  ቅዱስ ጊዮርጊስ በ12 ጊዜ ድል ቅድሚያውን ሲወስድ ደደቢት ሶስት ጊዜ አሸንፎ ቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ 31 እንዲሁም ደደቢት 17 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል። 

– ደደቢት በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ ዋንጫ ባነሳበት የ2005 የውድድር ዘመን 3-1 ባሸነፈበት ወቅት ነው።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ስድስት ጨዋታዎችን አድርጎ ሦስት ጊዜ ድል ሲቀናው ሁለቴ አቻ ተለያይቶ አንዴ ነጥብ ተጋርቷል።

– ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የሚመጣው ደደቢት እስካሀን ከመቐለ ውጪ በወጣባቸው አራት ከተሞች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሮ ከሁሉም በሽንፈት ተመልሷል።   

ዳኛ

– አምስተኛ እና ስምንተኛው ሳምንት ላይ ሁለት ጨዋታዎችን ዳኝቶ ስድስት የቢጫ ካርዶችን የመዝዘው ባህሩ ተካ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

ሳላለዲን በርጌቾ  – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አቡበከር ሳኒ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

ሳላሀዲን ሰዒድ – ጌታነህ ከበደ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

አብርሀም ታምራት – የአብስራ ተስፋዬ

ዳግማዊ ዓባይ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ

አኩዌር ቻሞ

                  

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *