ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ

መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ የሚገናኙበትን የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ እንደሚከትለው ዳሰነዋል።

ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም በመከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የሚካሄደው የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ 11፡00 ላይ ይጀምራል። ወደ ወራጅ ቀጠናው አፋፍ የተነሸራተተው መከላከያ የመጨረሻ ድሉን ወላይታ ድቻ ላይ ካስመዘገበ አምስት የጨዋታ ሳምንታት አልፈዋል። ሳምንትም ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በሲዳማ የ2-0 ሽንፈት ደርሶበት የተመለሰ ሲሆን ከዚያ አስቀድሞ ሜዳው ላይ ከሽረ ባደረገው ጨዋታም የመምራት ዕድል ቢያገኝም ነጥብ ለመጋራት ተገዶ ነበር። ከዛሬ ጨዋታዎች በፊት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ሊጉን ከመምራት ካዳነቀፏቸው ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ደቡብ ፖሊስን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል። በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየትም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ሲያስፈልጋቸው ለመከላከያም ከአደጋው ዞን ለመራቅ ወሳኝ ፍልሚያ ያደርጋል።

መከላከያ ዳዊት እስጢፋኖስን ከጉዳት እንዲሁም የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተጥሎበት የነበረው ተመስገን ገብረኪዳንን ከቅጣት መልስ የሚያገኝ ሲሆን ሽመልስ ተገኝ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛል። ከዚህ ውጪ ከጉዳቱ እያገገመ የሚገኘው አቤል ማሞ ወደ ጨዋታ መመለስ ግን እርግጥ አልሆነም። በሀዋሳ ከተማ በኩል ብሩክ በየነ ፣ ዳንኤል ደርቤ እና ደስታ ዮሃንስ  በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልመጡ ሲሆን ገብረመስቀል ዱባለ ከጉዳት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን እና አዲስዓለም ተስፋዬ ደግሞ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የሚመለሱ ይሆናል፡፡

መከላከያ የተመስገን እና ዳዊትን መመለስ ተከትሎ በማጥቃት ሂደቱ ላይ መሻሻል እንደሚያሳይ ይጠበቃል። አጋጣሚው ተጋጣሚው አማካይ ክፍል ላይ የሚጠቀማቸው ተጫዋቾች ቁጥር መበራከትን ለመቋቋም የሚያስችለውን ጉልበት ለማግኘት የሚያግዘው ቢሆንም ቡድኑ ወደ መሀል አጥብቦ የሚያጠቃ በመሆኑ የመስመር ተከላካዮቹን እገዛ መፈለጉ የማይቀር ነው። ከዚህ ውጪ በተከላካይ መስመሩ ላይ የሚታይበትን አለመረጋጋት ካላስተካከለ ግን የሀዋሳ ፈጣን አጥቂዎች ሰለባ መሆኑ የማይቀር ነው። ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል ፈጣን ጥቃቶች ላይ ተመስርተው ወደ ጨዋታው እንደሚገቡ የሚጠበቁት ሀዋሳ ከተማዎች እስራኤል እሸቱ እና አዳነ ግርማ ከፊት በሚፈጥሩት ጫና ክፍተቶችን የማግኘት ዕድላቸው የሰፋ ነው። በተለይም ሰባት የሊግ ግቦች ላይ የደረሰው የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ታፈሰ ሰለሞን ከአጥቂዎቹ እንቅስቃሴ የሚገኙ ክፍተቶችን በመጠቀም እና የመስመር ተመላላሾቹን ወደ ተጋጣሚ የመከልከል ዞን የሚያስገቡ ኳሶችን በመማደራጀት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 26 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 11 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ 7 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ 28 ፣ መከላከያ 24 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– ሀዋሳ ላይ የተካሄደው የአምናው የመጨረሻ ግንኘነታቸው በመከላከያ 4-0 የተጠናቀቀ ነበር።

– አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አምስት ጨዋታዎችን ያከናወኑት መከላከያዎች አንድ ጊዜ አሸንፈው አንዴ ደግሞ አቻ ሲለያዩ በሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል።

– አራት ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጪ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ይዘው ሲመለሱ አንድም ድል አላስመዘገቡም።

ዳኛ

– እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ዳኝቶ 24 የማስጠንቀቂያ አንድ የቀይ ካርድ የመዘዘው ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ታፈሰ ሰረካ  –  ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ዓለምነህ ግርማ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ

ተመስገን ገብረኪዳን

ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-1-2) 

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መሣይ ጳውሎስ

አክሊሉ ተፈራ –ኄኖክ ድልቢ– ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ያኦ ኦሊቨር

ታፈሰ ሰለሞን

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *