ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዷል

13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ መካሄድ ሲጀምር አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ጅማ አባጅፋርን ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀድሞው ተጫዋቻቸው አስቻለው ግርማ ግብ በሜዳቸው የ 1-0 ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ አጋማሽ በመቐለ 70 አንደርታ ሽንፈትን ካስተናገደው የቡድን ስብስብ ውስጥ ዳንኤል ደምሴ እና ወንድይፍራው ጌታሁንን በማስወጣት፤ የኃላሸት ፍቃዱንና ተካልኝ ደጀኔን በማስገባት ጨዋታውን ሲጀምሩ በአንጻሩ እንግዶቹ ጅማ አባጅፋሮች ባሳለፍነው ሐሙስ በሜዳው የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያውን ድል በሜዳ ካሳካው ቡድን ውስጥ ቢስማርክ አፒያ እና ኤርሚያስ ኃይሉን አስወጥተው በዲዲዬ ለብሪ እና ማማዱ ሲዲቤን ተክተው ወደ ጨዋታው ቀርበዋል። በዛሬው ጨዋታ በጅማ አባጅፋር በኩል በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከኢትዮጵያ ቡና ጅማን የተቀላቀሉት መስዑድ መሐመድ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና አስቻለው ግርማ የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒ ገጥመዋል፡፡

እጅግ ደካማ የነበረ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ በርከት ያሉ አካላዊ ጉሽሚያዎች የተስተዋሉበት ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ቡናው ተመስገን ካስትሮ እንዲሁም በጅማ በኩል ዐወት ገብረሚካኤል ባጋጠማቸው ጉዳት በወንድይፍራው ጌታሁን እና ኄኖክ ገምተሳ ተቀይረው ለመውጣት ተገደዋል፡፡

ሁለቱ የኢትዮጵያ ቡና የመስመር አጥቂዎች ኢያሱ ታሕሩ እና አቡበከር ናስር በጥልቀት ወደ ኋላ በመሳብ የተከላካይ መስመሩን በቂ ሽፋን በመስጠታቸው ቡናዎች የጅማ ሁነኛ የጥቃት ምንጭ የሆነውን የመስመር እንቅስቃሴ በመገደቡ በኩል ስኬታማ ነበሩ። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቡና ሶስት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ከጨዋታው የተነጠሉ ነበሩ። በዚህም የተነሳ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ለመድረስ ተቸግረው ተስተውሏል። በ6ኛው ደቂቃ መስዑድ መሀመድ ከአስቻለው ግርማ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ከቡና ሳጥን ውጪ በቀጥታ መቶ ወደ ውጭ የወጣበት እንዲሁም በ11ኛው ደቂቃ ቡናዎች በኩል ደግሞ ሳምሶን ከመሀል ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ በግንባሩ ገጭቶ ዳንኤል አጄይ የያዘበት ኳስ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግብ ጠባሺ እና ከመሐል ተከላካዮች በቀጥታ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ቡና ረጃጅም ኳሶችን በቀላሉ ሁለቱ የጅማ ከተማ የመሀል ተከላካዮች በተለይም አዳማ ሲሶኮ በቀላሉ ሲመክኑ ተስተውሏል፡፡

በ63ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል የነጠቁትን ኳስ ኄኖክ ጥቂት እርምጃዎች ከገፋ በኋላ ያመቻቸውን ኳስ ዲዲዬ ለብሪ ከቀኝ መስመር ሲያሻግረው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አስቻለው ግርማ በተረጋጋ ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል። አስቻለው ግርማ ደስታውን ከመግለፅ በመቆጠብ ለቀድሞ ክለቡ ደጋፊዎች ያለውን ክብር ገልጿል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ጅማዎች ንጋቱ ገብረሥላሴን በማስገባት ወደ ኃላ አፈግፍገው መጫወትን ምርጫቸው ሲያደርጉ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች የመስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድን አስወጥተው አጥቂው ፍፁም ጥላሁንን በማስገባት ይበልጥ የፊት መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾችን ቁጥር በማብዛት በረጃጅሙ በሚላኩ ኳሶች ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አልነበረም፡፡

ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል አልቢትር ለሜ ንጉሴ ተቸግረው ባመሹበት ጨዋታ ከረዳቶቻቸው ጋር ባለመናበብ በርካታ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ሲወስኑና በመቀጠልም ሲያስተካክሉ ተስተውሏል፡፡

ጨዋታው በጅማዎች የ1ለ0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪነታቸውን በቅዱስ ጊዮርጊስ ሲነጠቁ በአንጻሩ ተከታታይ ሁለተኛ ድላቸውን ያስመዘገቡትና አምስት ቀሪ ጨዋታዎች ያላቸው ጅማ አባጅፋሮች ወደ ስምንተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *