ሪፖርት | ፋሲል እና አዳማ ያለግብ ተለያይተዋል

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአማራ ደርቢን ታድመው ከባህር ዳር ሲመለሱ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ህይወታቸውን ላጡ የዐፄዎቹ  ደጋፊዎች የአዳማ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ባነር ይዘዉ ስታድየም በመገኘት ሀዘናቸውን ገልፀዋል። ጨዋታዉም አደጋው ለገጠማቸው የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር የጀመረው።

ፋሲሎች ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ሐብታሙ ተከስተን በመጣባቸው ሙሉ እንዲሁን አብዱራህማን ሙባረክን በዓለምብርሀን ይግዛው በመተካት ወደ  ሲገቡ አዳማዎች ወልዋሎን በረቱበት ጨዋታ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው ቡልቻ ሹራን ከህመም በተመለሰው ከነዓን ማርክነህን ብቻ በመቀየር ጨዋታውን ጀምረዋል።

የመጀመሪያዉ አጋማሽ ግጭት የበዛበት እና ፈጣን ጨዋታ የተስተዋለበት ነበር። ገና በ3ኛው ደቂቃ ላይ መጣባቸው ሙሉ ከመሀል ለአምሳሉ ጥላሁን ባቀበለዉን ኳስ አፄዎቹ ወደ ግብ የደረሱ ሲሆን አምሳሉ ከሳጥን ዉጪ ሞክሮ ሮበርት በቀላሉ አድኖበታል። የባለሜዳዎቹ ፋሲሎች የማጥቃት ሂደት የሽመክት ጉግሳን  እንቅስቃሴ ተከትሎ ወደ ግራ ያዘነበለ ሲሆን 10ኛው ደቃቂ ላይ ሽመክት ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝዉን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸዉ አሻምቶት አምሳሉ ጥላሁን ቢሞክርም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ጨዋታው 12 ደቂቃ ሲደርስ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ተነስተዉ የህሊና ፀሎት ያደረጉ ሲሆን በስታድየሙ ሙሉ የታደሙት የአፄዎቹ ደጋፊዎች ደግሞ 15ኛው ደቂቃ ላይ ተነስተዉ በማጨብጨብ ህይወታቸው ላለፉ ደጋፊዎች ያላቸዉን አክብሮት ገልፀዋል።

ወደኋላ ማፈግፈግን የመረጡት የአዳማ ከነማ የተከላካይ ክፍልን ሰብሮ መግባት ያቃታቸው አፄዎቹ 15ኛ ደቂቃ ላይ ከርቀት በኤዲ ቤንጃሚን እና በሽመክት ጉግሣ ተከታታይ ሙከራ ቢያደረጉም ሮበርትን ማለፍ አልቻሉም። በድጋሜ 19ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብ አክርሮ የመታዉን ኳስ ሮበርት በመትፋቱ የተገኝውን አጋጣሚ ሽመክት ጉግሳ ሳይጠቀምበት የቀረዉ የመጀመሪያው አጋማሽ የሚያስቆጭ  ሙከራ ነበር። የቀድሞ ክለቡን የገጠመው ሱራፌል ዳኛቸው 27ኛው ደቂቃ ላይ ከሰለሞን ሀብቴ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጥጠቅሞ እንዲሁም 29ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ተከላካዮች በማለፍ  ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ሁለቱም በሮበርት ጥረት ድነዋል። 32ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ በግራ መስመር ላይ ሽመክት ጉግሳ እና አምሳሉ ጥላሁን አንድ ሁለት ተቀባብለዉ ወደ ሳጥን ይዘዉት የገቡትን ኳስ አምሳሉ አክርሮ ቢመታም የግቡን ቋሚ ተጠግቶ የወጣበት ኳስ ሌላዉ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር ።

በእንግዳው ቡድን አዳማ ከተማ በኩል ወደኋላ አፈግፋገው ወደ መከላከል ያመዘነ ጨዋታ ሲጫወቱ ተስተዉሏል። በረከት ደስታ 18ኛው እና 20ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ወደግብ የሞከራቸዉ እና ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዛቸዉ ኳሶች የሚጠቀሱ የቡድኑ ሙከራዎች ሲሆኑ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ባልተጠበቀ ሁኔታ ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት ወደግብ አክርሮ የመታዉን ኳስም ሳማኬ አድኖበታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ግጭት ከመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ የበዛበት እንዲሁም ዳኛዉ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲከብደዉ የተስተዋለበትም ነበር ፤ በተደጋጋሚ ተጫዋቾች ሲከቡት እና ለዉሳኔም ሲቸገር ተስተዉሏል። በጨዋታው ሙሉ ለሙሉ በፋሲል ከነማ ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማዎች ረጃጅም ኳሶችን ከተከላካይ መስመራቸው ለዳዋ ሆቴሳ ለማሻገር ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም። በሙከራ ደረጃ ምኞት ደበበ 52ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂውን መዉጣት ዓይቶ ከርቀት አክርሮ የመታዉ እና ሳማኬ ያዳነበት ተጠቃሽ ነበር። በመልሶ ማጥቃት የተገኝዉን ኳስ ደግሞ ዳዋ ሆቴሳ 85ኛ ደቂቃ ላይ ከርቀት ቢሞክረዉም በግቡ አግዳሚ ተጠግቶ ወጥቶበታል። በድጋሜ 87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባዉ ሱራፌል ዳንኤል ወደግብ የመታዉን ኳስ ግብ ጠባቂው ሳማኬ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያዳነበትም የአዳማዎች ጠንካራ ሙከራ ነበር።

በፋሲል በኩል የአዳማ ከተማን የተከላካይ መስመር ሰብረዉ ለመግባት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ተስተዉሏል። 46ኛ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸዉ ከመሀል ወደ ቀኝ መስመር ለሰይድ ሀሰን ያሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክረዉም በጨዋታ ድንቅ ብቃት ላይ የነበረዉ ሮበርት ኡዶንካራ አድኖበታል። ወደ ፊት ሰብረዉ መግባት የተቸገሩት አፄዎቹ 58ኛ ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው ያቀበለዉን ኳስ መጣባቸዉ ሙሉ ከሳጥን ዉጪ ወደግብ አክርሮ ቢመታዉም ግብ ጠባቂ አድኖበታል። በጨዋታው ለአዳማ ተከላካዮች እጅግ ፈታኝ የሆነባቸዉ ሱራፌል ዳኛቸዉ 64ኛው ደቂቃ ላይ እራሱ ላይ የተሰራ ጥፋት የተገኝዉን የቅጣት ምት ወደ ግብ አሻምቶት ሽመክት ጉግሳ በጭንቅላት ቢገጨዉም የግብ አግዳሚ የመለሰበት በሁለተኛው አጋማሽ የታየ ጥሩ ሙከራ ነበር።  የተሻለ ተጭነዉ ለመጫዎት የማጥቃት እንቅስቃሴውን ለማጠናከር ሠለሞን ሐብቴን በማስወጣት ኢዙ አዙካን ያስገቡት ፋሲል ከነማዎች 79ኛ ደቂቃ ላይ ከኢዙ አዙካ የተሻገረለትን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸዉ ሳይጠቀምበት የቀረዉ ሌላዉ የሚጠቀስ ሙከራ ነዉ ። 

ጨዋታው ያለምንም ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ20 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከሜዳ ዉጪ አንድ ነጥብ ይዞ የተመለሰዉ አዳማ ከነማ በአንፃሩ በ19 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *