ሪፖርት | መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ዛሬ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የተካሄደው የ13ኛው ሳምንት የመከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በ12ኛው ሳምንት በሲዳማ የ2-0 ሽንፈት የደረሰባቸው መከላከያዎች በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ላይ የአምስት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ታፈሰ ሰረካ ፣ ዓለምነህ ግርማ ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ፍፁም ገብረማርያምን በሙሉቀን ደሳለኝ ፣ ሠመረ አረጋዊ ፣ አዲሱ ተስፋዬ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ተመስገን ገብረኪዳን ተክተዋል። ደቡብ ፖሊስን አሸንፈው የመጡት ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው ከቢጫ ካርድ ቅጣት የተመለሱት አዲስዓለም ተስፋዬ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በአክሊሉ ተፈራ እና ምንተስኖት አበራ ምትክ ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች ጨዋታውን ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ መጀመር ችለው ነበር። 2ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት አጋጣሚም ተመስገን ገብረኪዳን በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሳልፍ ሶሆሆ ሜንሳህ አውጥቶበታል ፤ ግብ ጠባቂው በዚህ እንቅስቃሴ መጠነኛ ጉዳትም አስተናግዶ ነበር። በቀጣይ ደቂቃዎች ግን መከላከያዎች በማጥቃት ሂደቱ ይታይባቸው የነበረው መነቃቃት እየቀነሰ ሲሄድ እና ሀዋሳዎች ወደ ፊት ገፍተው መጫወት ሲጀምሩ ታይቷል።11ኛው ደቂቃ ላይም በሚገርሙ ቅብብሎች ወደ መከላከያ ሳጥን የገቡት ሀዋሳዎች ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን  ከታፈሰ ሰለሞን በደረሰው ኳስ ለአዳነ ግርማ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም አዳነ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሆኖም ከደቂቃ በኋላ በከፈቱት ሌላ ጥቃት ፍቅረየሱስ ላይ ጥፋት በመሰራቱ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብነት ቀይሮት በድኑን መሪ አድርጓል።

ኳስ መስርተው ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ የሚሞክሩት መከላከያዎች ቀድመው የመከላከል ቅርፃቸውን ይይዙ የነበሩት ተጋጣሚዎቻቸውን አልፈው ወደ ውስጥ ለመግባት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው ግብ ጠባቂያቸው ይድነቃቸው ኪዳኔ ይሰራቸው የነበሩ ስህተቶች የግብ ልዩነቱን ለማስፋት ተቃርበው ነበር። 18ኛው ደቂቃ ላይ አዲስዓለም ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ይድነቃቸው መቆጣጠር ተስኖት እስራኤል እሸቱ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ሲወጣ 27ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ጠባቂው ሌላ በረጅሙ የተላከ ኳስ በአግባቡ ሳያወጣ ቀርቶ ሀዋሳዎች ክፍት የግብ ዕድል ለማግኘት ተቃርበው ነበር። ወደ ኋላ ቀረት እያሉ በጥንቃቄ በመከላከል ኳስ ሲያገኙ በፍጥነት ወደ ፊት ለመሄድ ይሞክሩ የነበሩት ሀዋሳዎች በእስራኤል እሸቱ ፍጥነት ላይ ተመስርተው አልፎ አልፎ ረዘም ባሉ ኳሶች ወደ ጦሩ አጋማሽ  ሲያደርሱ ቢታዩም ሌላ ግልፅ የግብ ዕድል ማግኘት ግን አልቻሉም።

በእስራኤል የፊት መስመር እንቅስቃሴ ከኋላ ቅብብሎችን ለመጀመር ይቸገሩ የነበሩት መከላከያዎች አልፎ አልፎ ቀጥተኛ ኳሶችን እየጣሉ ለማጥቃት ሲሞክሩ 29ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን  በግራ በኩል ገብቶ  የሞከረው እና ወደ ውጪ የወጣበትን ሙከራ ማድረግ ችለዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፍሬው በዛው መስመር ወደ ሳጥን ሲገባ በአዲስዓለም ተስፋዬ ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ምንይሉ ወንድሙም አጋጣሚውን ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑ በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አስችሏል። ከምንይሉ ግብ በኋላ የነበረው እንቅስቃሴ ግን እየተቀዛቀዘ የሄደ ነበር።

ከዕረፍት መልስ የነበረው እንቅስቃሴ የመጀመሪያው በተገባደደበት መንገድ ተተዛቅዞ የቀጠለ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ኃይላቸውን ለመጨመር ያደረጓቸው ቅያሪዎችም በፈለጉት መጠን የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሳይፈጥሩላቸው ነበር ጨዋታው ያለውጤት ለውጥ የተጠናቀቀው። ገብረመስቀል ዱባለን በአስጨናቂ ሉቃስ ቀይረው ያስገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በመስመር ለሚፈጥሩት ጫና ጉልበት የሚሆን ቅያሪን ቢያደርጉም ወደ ፊት የሚያሳልፏቸው ኳሶች የተመጠኑ ባለመሆናቸው ምክንያት በተደጋጋሚ በይድነቃቸው በቀላሉ እንዲከሽፍባቸው ሆኗል።  በሂደትም ወደ ጥንቃቄው በማድላት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከሳጥናቸው ብዙም ሳይርቁ በመከላከል ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።

በመከላከያዎች በከል 60ኛው ደቂቃ ላይ የአሰላለፍ ለውጥንም ጭምር ያስከተለ ቅያሪ ተደርጓል። ፍፁም ገብረማርያም ሳሙኤል ታዬን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ጦሩ ከፊት የሦስት አጥቂዎችን ጥምረት በመጠቀም እስከጨዋታው መጨረሻ ዘልቋል።

61ኛው ደቂቃ ላይ  ፍፁም እና ፍሬው ከፈጠሩት ቅብብል ምንይሉ ግራ የሀዋሳ ሳጥን ውስጥ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረበት እንዲሁም 83ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው የቴክኒክ ብቃቱን በመጠቀም ከመሀል ጀምሮ በፈጠረው ክፍተት ምንይሉ ለፍፁም አቀብሎት ፍፁምም በተመሳሳይ አክርሮ ሲመታ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራ ቡድኑ ወደ ፊት ዘልቆ በገባባቸው ሁለት ቅፅበቶች የታዩ ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም ጦሩ የሀዋሳዎችን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ገብቶ ያለቀለት የሚባል የግብ ዕድል ሳይፈጥር ጨዋታው በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱም ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በነበረበት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ ዛሬ ድል የቀናው ስሑል ሽረን ተክቶ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቀመጥ ተገዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *