የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-1 ሀዋሳ ከተማ

ከሰዓታት በፊት መከላከያ ሀዋሳ ከተማን በአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናገደበት የ13ኛው ሳምንት የሊግ ጨዋታ 1-1 ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች በጨዋታው ዙሪያ ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

“በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ጨዋታ ነበር ያየነው” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

“ጨዋታውን ይሄ ነው ማለት ይከብዳል። አንድ አይነት እንቅስቃሴ ነው ያደረግነው ፤ እነሱም ላለመሸነፍ እኛም ከመሪው ላለመራቅ ታግለናል። የመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ ላይ የሳትናቸው ኳሶች ነበሩ ፤ እነሱን ያገኘናቸው አጋጣሚዎች ብንጠቀም ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር። በተረፈ ግን በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ኳስ ጨዋታ ነበር ያየነው።”

” ቢያንስ ከምንም ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ለቡድኑ ስነ ልቡና ጥሩ ነው ብዬ አስባለው” ሥዩም ከበደ – መከላከያ

“ነጥቦች እየጣልን በመምጣታችን በራስ መተማመናችን እየወረደ የመጣ ይመስላል ፤ ያንን ለማስተካከል እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ላይ ማሸነፍን እንጠብቅ ነበር ፤ ያው ነገሮችን እያስተካከልን ለመሄድ እንሞክራለን። ዛሬ ስንጀምር በ 4-4-2 ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ ፍፁምንም አስገብተን ጫናውን ለመጨመር ሞክረን ነበር። ሆኖም ነገሮች እንዳቀድናቸው ባይሄዱም ቢያንስ ከምንም ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ለቡድኑ ስነ ልቡና ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።”

ከሲዳማው ጨዋታ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ስለመደረጉ

“ለውጦቹ በህመም እና በዲስፕሊን የተደረጉ ነበሩ። ለምሳሌ እንደ ዳዊት እና ተመስገን ዓይነቶቹ ከጉዳት የተመለሱ በመሆናቸው እና ወደፊትም ብዙ ስለሚጠቅሙን በፊትም ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ የነበሩ እና ዋንጫ ስናገኝም ጥሩ የነበሩ በመሆኑ እነሱን ወደ ሜዳ መመለሱ ተገቢ ነበር።”

መስመር ተከላካዮች ላይ የሚታየው ተደጋጋሚ ለውጥን በተመለከተ

“ከመጀመሪያም ጀምሮ ቡድኑ ላይ ያለ ትልቁ ክፍተት እና ወደፊትም የምናስብበት ጉዳይ ነው። የትኛውንም አሰላለፍ ብንጠቀምም የመስመር ተከላካዮች ወሳኝ ካልሆኑ በቀር የማጥቃት ኃይሉ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የሚጣል ነው የሚሆነው። ቦታው ጥራትን ይፈልጋል ፤ እስከዛው ግን ባሉን ተጫዋቾች እየተጠቀምን የምናስብበት ይሆናል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *