ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ | ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታ አሰላ ላይ የተገናኙት ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።

አሰላ ከተማ በሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቅጥር ግቢ ውስጥ 09:00 በተደረገው ጨዋታ እንግዶቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ወደ ፊት በመሄድ ሲጀምሩ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚዎች ባልተደራጀ አጨዋወት ተዳክመው የታዩ ሲሆን የጎል ሙከራ በማድረግም ቀዳሚ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነበሩ። በዚህም 11ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል በግራ ጠርዝ ከሳጥን ውጪ ዳግማዊ አርአያ ተረጋግቶ የመታው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ጥሩ የማግባት አጋጣሚ ነበር። የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የቀጠለው ፈረሰኞቹ በ17 ኛው ደቂቃ በሐረር ሲቲ ፣ በደደቢት ከ17 ዓመት በታች ክለቦች በአጥቂ መስመር ሲጫወት የምናቀው ታዲዮስ አዱኛ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ግብጠባቂው መኮንን መርዶክዩስ አድኖበታል። አልፎ አልፎ ካልሆን በቀር በተቆራረጠ አጨዋወት ከርቀት ኳሶችን ከየትኛውም አቅጣጫ አክርሮ በመምታት የግብ እድል ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ ጥሩነሽ ዲባባዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ብልጫ ተወስዶባቸዋል።


የመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ከነበራቸው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ እያሉ መምጣታቸውን ተከትሎ ጥሩነሽ ዲባባዎች በረጃጅም ኳሶች ወደፊት በመሄድ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ እና በዋናው ቡድን እየተመላለሰ የሚጫወተው ተከላካዩ ያዓብስራ ሙሉጌታ የመከላከል አቅም ግልፅ የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ማምሪያ ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል በገቡት ፈረሰኞቹ በኩል የመጨረሻውን ኳስ በደረቱ ያበረደው ታዲዮስ አዱኛ ወደ ጎል ቢሞክርም ግብጠባቂው መኮንን በጥሩ ሁኔታ አድኖበታል።


ከእረፍት መልስ የነበረው እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ ፉክክር የተካሄደበት ቢሆንም የሜዳው ነፋሻማ አየር እንደልብ አላጫውት ማለቱ ለሁለቱም ቡድኖች ስራቸውን ፈታኝ አድርጎታል። ወደፊት የሚያሳልፏቸው ኳሶች በንፋስ ግፊት በፍጥነት ወደ ውጪ ሲወጥጡባቸው እና አቅጣጫ ሲቀይሩባቸውም ተስተውሏል። ጥሩነሽ ዲባባዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በመልሶ ማጥቃት 67ኛው ደቂቃ አትርሳው ተዘራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ የወጣበት አጋጣሚ የቡድኑ የመጀመርያ የግብ ሙከራ ነበር።

በፈረሰኞቹ በኩል ወደ ፊት የሚያሳልፏቸው ኳሶች የተመጠኑ ባለመሆናቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ለግብ ጠባቂው መኮንን ሲሳይ ይሆኑ የነበረ በመሆኑ በርካታ ሙከራዎች ባያደርጉም 78ኛው ደቂቃ ላይ ሉክ ፖውሊኒሆ ከዳግማዊ በጥሩ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ ግብ ጠባቂው መኮንን በሚገርም ሁኔታ ተወርውሮ ያዳነበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ለግብ ጠባቂ የሚሆን ቁመና ያለው የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚው ግብጠባቂ መኮንን በጨዋታው ተሰፋ ሰጪ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። ወደ ጨዋታው መገባደጃ ላይ በታየው የመጨረሻ ሙከራም ተቀይሮ የገባው የአካዳሚው አጥቂ 14 ቁጥር ግልፅ የማግባት አጋጣሚን ሳይጠቀም ቀርቶ ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም ቡድኖቹ የደረጃ መሻሻልን ሲያደርጉ ጥሩነሽ ዲባባዎች ወደ ስድስተኝነት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ወደ ሁለተኝነት ከፍ ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *