አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ደቡብ ፖሊስ ተለያዩ

የ2010 የከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ ከአምስት ወራት በኃላ ከዋና አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራው ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ እየተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የተጠናቀቀው የውድድር ዓመትን በቻምፒዮንነት በማጠናቀቅ ለመጨረሻ ጊዜ ከስምንት ዓመታት በፊት ወደተሳተፈበት ውድድር የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ የቀድሞው አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራውን ዳግም በዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በሊጉ እስካሁን ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ደደቢትን ከረታበት ውጪ 10 ሽንፈት የገጠመው ሲሆን ሁለት የአቻ ውጤቶችን አስመዝቦግቦ በ10 የግብ ዕዳ እና 5 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት የሚታይበት ክለቡ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በውጤት የታጀበ ባለመሆኑ እና ደካማ የውድድር ዓመትን እያሳለፈ በመቀጠሉ ከአሰልጣኙ ጋር ለመለያየት ተገዷል፡፡ ዛሬ የክለቡ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ ከአሰልጣኙ ጋር ለመለያየት ከስምምነት መድረሱን ተከትሎ ውሳኔውን ማስተላለፉን የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ጠዋት በነበረው የልምምድ መርሐ ግብር ላይ ያልተገኙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት “በራሴ እንድለቅ ነበር የተፈለገው ፤ ያን ማድረግ እና ቡድኑን አደባባይ ጥዬ መልቀቅ ግን በፍፁም አልፈለኩም ነበር። እስከመጨረሻው ነገሮችን መጋፈጥ ነበር የፈለኩት። በእርግጥ ውጤታችን አልተሳካም ፤ ይህን ደግሞ ቁጥሮች ይናገራሉ። እናንተ ከተስማማቹ ግን እለቃለው አልኳቸው። በስተመጨረሻም ጉዳዩ ከነሱም ከኔም በተመሳሳይ የመጣ በመሆኑ በስምምነት ልንለያይ ችለናል” ብለዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ ከያዙት ደቡብ ፖሊስ ባለፈ የቀድሞው አዳማ ከተማ ፣ ደደቢት ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ወልዲያ እና የብሔራዊ ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ የነበሩት ዘላለም ሽፈራው የአንድ ዓመት የውል ስምምነታቸው ሳይጠናቀቅ ገና በአምስተኛው ወር ከክለቡ ጋር የተለያዩ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት በቅርቡ ሌላ የፕሪምየር ሊግ ክለብን ሊያሰለጥኑ እንደሚችሉ የተነገረ ሲሆን ደቡብ ፖሊስ አዲስ አሰልጣኝ እስከሚሾም ድረስ በረዳቶቹ ያለው ተመስገን እና አዲሱ ጡኔ እየተመራ ለቀጣይ ጥቂት ጨዋታዎች እንደሚዘለቅ ክለቡ ጨምሮ ገልጿል፡፡

*ሌላው በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ደደቢት በዛሬው ዕለት አሰልጣኞቹን ማሰናበቱ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *