ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ደደቢት

ከ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል ሲዳማ እና ደደቢት የሚያደርጉትን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

በ2002 የውድድር ዓመት ተያይዘው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉት እና ዘንድሮም በተመሳሳይ ጊዜ መቀመጫቸውን የቀየሩት ሲዳማ ቡና እና ደደቢት ነገ 09፡00 ላይ ለ19ኛ ጊዜ በሊጉ ይገናኛሉ። ራሳቸው ከረቱት ፋሲል ከነማ ጋር አንድ ሽንፈት ብቻ በማስተናገድ ዝቅተኛ የሽንፈት ቁጥር ያላቸው ሲዳማ ቡናዎች ሳምንት ከድሬዳዋ ጋር የነበራቸው ጨዋታ በፀጥታ ምክንያት መተላለፉ ይታወሳል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀራቸውም ከዋንጫ ፉክክሩ በነጥብ ባይርቁም ወደ አምስተኛ ደረጃ ዝቅ ብለው ይገኛሉ። ሲዳማዎች እንደመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቻቸው ሁሉ ነገም ድል ከቀናቸው መሪዎቹን እግር በእግር መከተላቸውን ይቀጥላሉ። ጨዋታው በ13 የግብ ዕዳዎች እና በአራት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ለሚገኙት ደደቢቶች ከአሰልጣኞቻቸው ኤልያስ ኢብራሂም እና ጌቱ ተሾመ ጋር ከተለያዩ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ይሆናል። ቡድኑ ከአዳማ ነጥብ ሲጋራ መጠነኛ ተስፋን ቢያሳይም ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች የገጠመው ሲሆን ከወዲሁ ከወራጅ ቀጠናው መግቢያ በስድስት ነጥብ ርቀት ላይ መቀመጡ ስጋቱን አባብሶበታል።

ከአስር ቀናት በኋላ ወደ ጨዋታ የሚመለሱት ሲዳማ ቡናዎች መሳይ አያኖን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ግሩም አሰፋም ወደሜዳ ይመለሳሉ። በመሆኑም ቡድኑ ያለምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና ጨዋታውን ያደርጋል። የልምድ ዕጦት የሚስተዋልበት ስብስብ የያዙት ደደቢቶች በአምናው ቡድን ውስጥ የተሻለ ተሳትፎ የነበራቸው አለምዓንተ ካሳን በጉዳት አቤል እንዳለን ደግሞ በስሑል ሽረው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ ያጣሉ። በተጨማሪም ኩማ ደምሴ በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት ወደ ሀዋሳ አልተጓዘም።

በታሪካቸው ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡናን መርታት ያልሆነላቸው ደደቢቶች በነገው የሀዋሳ ጨዋታም ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል። የተሻለ የጨዋታ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾቹን በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት ማጣቱ እንዳለ ሆኖ ሜዳ ላይ መረጋጋት ሲሳነው የሚታየው ደደቢት ከሲዳማ ቡና ፈጣን ጥቃት እና ደማቅ የደጋፊ ድባብ ጋር ሲገናኝ ሊቸገር እንደሚችል ይታመናል። በመሆኑም ወደ ኋላ ያፈገፈገ እና ኳስ ለመያዝ በመሞከር ከራሱ አጋማሽ ወደ ፊት በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት የሚሞክር ደደቢት ይጠበቃል። በሲዳማ በኩል ግን የቡድኑ ጠንካራ ጎን የሆኑት የመስመር አጥቂዎች በቀላሉ ክፍተቶችን የሚያገኙበት እና ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅትም ከደደቢት የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚፋለሙባቸውን ቅፅበቶች በአሸናፊነት የማለፍ ግምቱን ይወስዳሉ። የደደቢት መከላከል ከጠነከረ ግን የመሀል አጥቂው መሀመድ ናስርን መዳረሻ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች መታየታቸው የሚቀር አይመስልም።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 18 ጊዜ ተገናኝተዋል። በነዚህ ጊዜያት ሲዳማ ግማሹን በማሸነፍ የበላይ ሲሆን 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ደደቢት በ4 አጋጣሚዎች ድል ቃንቶታል።

– በ17 ጨዋታዎች 46 ግቦችን ባስተናገደው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ሲዳማ 24 ደደቢት ደግሞ 23 ግቦች አስቆጥረዋል። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበትም ነው።

– ደደቢት በሲዳማ ቡና ሜዳ አሸነፎ የማያውቅ ሲሆን ሲዳማ ቡና ከ9 ጨዋታዎች 7ቱን ድል አድርጓል።

– ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ላይ አምስት ድሎች እና ሦስት የአቻው ውጤቶች አስመዝግቦ ያለምንም ሽንፈት እስካሁን የዘለቀ ሲሆን ደደቢት በተቃራኒው ከሜዳው ውጪ ምንም ነጥብ አላሳካም።

ዳኛ

– እስካሁን በዳኘባቸው ሁለት ጨዋታዎች አምስት የማስጠንቀቂያ ካርዶች የመዘዘው አክሊሉ ድጋፌ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሃንስ – ግርማ በቀለ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – መሀመድ ናስር – አዲስ ግደይ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ዳዊት ወርቁ – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

አብርሀም ታምራት – የዓብስራ ተስፋዬ

ዳግማዊ ዓባይ – ሙሉጌታ ብርሀነ – እንዳለ ከበደ

አኩዌር ቻሞ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *