የ<ኳስሜዳ> የቀድሞ ስሙን ለመመለስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል

– ኳስሜዳ የቀድሞ ስሙን የሚመልስበት የፉትሳል ሜዳ ለመስራት ከከተማው አስተዳደር የማረጋገጫ ካርታ ሊሰጠው ነው::

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ አይረሴ ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀው መሳለሚያ አካባቢ የሚገኘው <ኳስሜዳ> ከ25 ዓመታት በፊት በልማት ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መቀየሩ ይታወሳል። ከዛ ወዲህም ኳስሜዳ ለአካባቢው ስያሜ ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

በ2001 ከትምህርት ቤቱ ጀርባ ምትክ ቦታ ተሰጥቶ ሜዳውን ለመስራት የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም ቦታው እንደታሰበው የእግርኳስ ሜዳ እንዳይሆን እና ሌላ የልማት ስራዎች እንዲሰራበት ለማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል። ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት በቅርቡ በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ መልካም ፍቃድ ቦታው ላይ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ እንዲሰራበት ፍቃድ ማግኘቱን፣ የካርታ ርክክብ በቅርቡ እንደሚፈፀም እና የፉትሳል ሜዳውን ለመጀመር ማሰባቸውን የኳስሜዳ ኮሚቴ አስተባባሪ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ (ከ1983 – 86) መጫወት የቻለውና በአሁኑ ወቅት አቢሲኒያ የተባለ የታዳጊዎች ፕሮጀክት በመክፈት እየሰራ የሚገኘው ሞገስ ታደሰ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።


ሞገስ ከድረ-ገጻችን ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

በቅድሚያ ኳስሜዳ በኢትዮጵያ እግርኳስ ያበረከተውን ውለታ እንዴት ትገልፀዋለህ?  

የዛሬን አያርገውና ኳስሜዳ በኢትዮጵያ እግርኳስ ስማቸው የማይረሳ ብርቅዬ ተጫዋቾችን ያፈራ ሜዳ ነው። ኃይሌ ካሴ፣ ወርቁ ማሞ፣ ሀሚቲ ካሳ፣ አስቻለው ተሰማ እና አቦነህ ማሞ ያደጉበት ከቅርቦቹ እነ ዓሊ ረዲ፣ ማሞዓለም ሻንቆ እና ሌሎችም ዝነኛ ተጫዋቾች የወጡበት ሜዳ ነበር።  ሆኖም የዛሬ 25 ዓመት “ለአቅም ግንባታ” በሚል የተወሰነው የሜዳ ክፍል ግንባታ ተከናወነበት። በቀረው የሜዳ ክፍል የአካባቢው ወጣቶች እና ታዳጊዎች እየተጫወቱበት ቆይቶ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአካባቢው ብዙ ትምህርት ቤቶች እያሉ ሜዳው ላይ ትምህርት ቤት በመስራታቸው ይህ ታሪካዊ ሜዳ በሚያሳዝን ሁኔታ ጠፍቷል። በወቅቱ አስታውሳለው ብዙ ህዝብ በዚህ ነገር በመበሳጨት ትምህርት ቤቱ እንዳይሰራ እና ሜዳው እንዲቆይ ጥረት አድርገናል። ቆፍረው ሲሄዱ መልሰን አፈር እያለበስን ሜዳውን ለማስቀረት ብንሞክርም ትታሰራላቹ የሚል ማስፈራርያ ይደርስብን ነበር።  ሆኖም ይህ ጥረታችን ሳይሳካ በመቅረቱ ነዋሪው በጣም አልቅሶ፣ አዝነን ሜዳውን ተነጥቀናል። አሁን ላይ ኳስ ሜዳ ደብዛው ጠፍቶ ስናይ ሁሌም ያሸማቅቀናል።

ይህ ታሪካዊ ሜዳ በልማት ምክንያት በመቅረቱ በትውልዱ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ጎን አለ ትላለህ?

ይህ ሜዳ በልማት ምክንያት ከቆመ በኋላ  አንዳንድ ወጣቶች በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። በተለያዩ ሱሶች እየተጠቁ ይገኛል። ከመጠን በላይ አላስፈላጊ ባህሪ ውስጥ የገቡ ወጣቶች አሉ። የሚያሳዝነው የአዕምሮ ህመምተኛ የሆኑም ጭምር መኖራቸው ነው። ታዲያ ይሄንን ሁሉ እያዩ መኖር ልብን ይሰብራል። ትውልድ ጠፍቷል፤ ለኢትዮጵያ እግርኳስም ሀዘን ነው ማለት ይቻላል።


አሁን ዘመናዊ የፉትሳል ሜዳ ለመስራት አቅዳችኋል። ታዲያ ይህን መሬት እንዴት ልታገኙ ቻላችሁ?

ይህ ቦታ የከብቶች ማደለብያ ቦታ ነበር። በተለያዩ መንገዶች ቤቱ ስራ አቁሞ ሲዘጋ እዚህ ቦታ ላይ ቢያንስ አስር ሰው የሚጫወቱበት የፉትሳል ሜዳ እንዲሰራ ለክፍለ ከተማው ጥያቄ አቀረብን። በወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት ኩማ ደመቅሳ ይህን ቦታ እንድንሰራበት ፈቅደው የመሰረት ድንጋይ 2001 ሰኔ 7 ላይ ተቀምጦበታል።

ታዲያ ላለፉት አስር ዓመታት ቦታው ላይ የታሰበው የፉትሳል ሜዳ ሳይሰራ ለምን ቀረ?

ብዙ ውስብስብ ነገሮች አሉበት። በወቅቱ የነበረውም ብልሹ አሰራር ይመስለኛል ግንባታው እንዳይካሄድ ያደረገው። በተለይ አንዳንድ ባለ-ሀብቶች ቦታው ግንባር ቦታ በመሆኑ ለልማት ለመውሰድ ብዙ ጥረት አድርገው ነበር። በከተማ አስተዳደር ያሉትም አመራሮች ቦታውን ለባለ-ሀብት ለማስተላለፍ ሞክረዋል። ሆኖም የአካባቢው ነዋሪ ይህ ቦታ እንዳይወሰድ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት እና ጫና ከብዙ ትግል በኋላ ተሳክቶ ቦታውን አስከብረን እንዳይወሰድ ማድረግ ችለናል። አመራሮቹም የነበረንን ቆራጥነት ተመልክተው ምንም ነገር ሳያደርጉት ቦታው ላይም ምንም ነገር ሳይሰራበት አስጠብቀን ለአስር ዓመት አቆይተናል።

ከሰሞኑን ቦታውን በተመለከተ አንድ ተስፋ ሰጪ ነገር እንዳገኛችሁ ሰምተናል። ይህ ነገር ምንድነው?

በመጀመርያ የኳስ ሜዳ ህዝብ ብዙም ፖለቲካ ውስጥ አይገባም፤ አይሳተፍም ይሄም ይመስለኛል ያለፉትን ዓመታት ቦታው እንዲወሰድ እና ኳስ መጫወቻ እንዳይሰራበት የተፈለገው። ለመጀመርያ ጊዜ ነው የአካባቢው ነዋሪ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ታከለ ኡማን ያመሰገነው። እውነት ለመናገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ያቀረብነውን ጥያቄ ተቀብለው፣ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመፈፀም ቃል በመግባት ቦታው ላይ ዘመናዊ የፉትሳል ሜዳ እንድንሰራ በአስቸኳይ የማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጠን የተባበሩን በጣም እናመሰግናለን። ይህ ለእኛ እና ለታዳጊው ትልቅ ተስፋ ነው።


ከከተማው መስተዳድር የቦታውን ማረጋገጫ ካርታ በቅርቡ ትረከባላችሁ። ስለዚህ ወደ ግንባታው መቼ ትገባላችሁ?  በምን ያህል ጊዜ ለማጠናቀቅ አስባችኋል? ለግንባታው የሚሆን የፋይናንስ ምንጭ እንዴት ለማግኘት አስባችኋል?  

በዚህ ስራ ክፍለ ከተማውም ሆነ ወረዳው ለግንባታው ድጋፍ ለማድረግ በጀት እንደሚመድቡ ቃል ገብተውልናል። ይህ ጥሩ ነገር ቢሆንም እንደሚታወቀው ከመንግስት የሚለቀቁ ገንዘቦች በፍጥነት ስለማይለቀቁ እና የሚቆራርጡ በመሆናቸው አስቸጋሪ ነው። ይህ ቦታ የሜዳ ግንባታ እንዲካሄድበት የለፉ የደከሙ በሀገር ውስጥም በውጭም አሉ ይህንን ቦታ ሜዳ ለማድረግ ሁሉም ጓጉቷል። የአካባቢው ነዋሪም ከፍተኛ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በተቀናጀ ሁኔታ ለመስራት ከማኅበረሰቡ የተወጣጡ ስምንት አባላት ያሉበት ኮሚቴ ተዋቅሯል። ከወረዳው ስፖርት ፅህፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን ሰፊ ውይይት አድርገን ካርታው እጃችን እንደገባ ወደ ስራ የምንገባ የሚሆነው። ሁሉም ሰው ተሰርቶ እንዲያልቅ ካለው ጉጉት የተነሳ ይረባረባል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። በቀጣይም ዝርዝር ነገሮች እናቀርባለን።

በመጨረሻም የምታስተላልፈው መልክት ካለ?

የኳስ ሜዳ መጥፋት የብዙ ሰው ቁጭት፣ ሀዘን ነው። ሁሉም ሰው ይህ የፉት-ሳል ሜዳ ተሰርቶ ማየትን ይፈልጋሉ። ኳስ ሜዳ የድሮ ስሙን ይዞ ጤናማ አዕምሮና ሙሉ አካል ያላቸው ወጣቶች የሚፈሩበት ቦታ እንደሚሆን እተማመናለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

error: Content is protected !!