ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ደቡብ ፖሊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ነገ ዘግየት ብሎ የሚጀምረው የቡና እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታ የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን የመጨረሻው ትኩረት ነው።

10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም መካሄድ በሚጀምረው ጨዋታ ከአምና ጀምሮ በሜዳው ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገው ደቡብ ፖሊስ ይገናኛል። በጅማ መሸነፉን ተከትሎ ወደ ሁለተኝነት ዝቅ ያለው ቡና ይህን ጨዋታው አሸንፎ ቢያንስ እስከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ድረስ ወደ አንደኝነት የመመለስ ዕድል ይኖረዋል። ቡድኑ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከደረሱበት ትከታታይ የ 1-0 ሽንፈቶች እና እየተዳከመ ከመጣው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ለማገገም በውጤት ማጣት ውስጥ ከሚገኘው ደቡብ ፖሊስ ጋር መገናኘቱ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥርለት ይመስላል። ደቡብ ፖሊስ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር ተለያይቶ በመቆየት ትናንት የቀድሞው ተጫዋቹን አሰልጣኝ አላዛር መለሰን በቦታው ሾሟል። ቡድኑ ከሽረ ጋር ነጥብ ከተጋራበት የአስረኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ወደ ተከታታይ ሽንፈቱ ከተመለሰበት ውጤት ለማገገም እና በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ነፍስ ለመዝራት ከነገው ጨዋታ የሚገኘው ነጥብ በእጅጉ ያስፈልገዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በጅማው ጨዋታ ከባድ ጉዳት ያስተናገደው ተመስገን ካስትሮን እና ሚኪያስ መኮንን በነገው ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን ከነበረባቸው ጉዳት አገግመው ልምምድ የጀመሩት ቶማስ ስምረቱ እና አስራት ቱንጆ መግባትም አጠራጣሪ ሲሆን ሱለይማን ሎክዋ ግን ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በደቡብ ፖሊስ በኩል ደግሞ አበባው ቡታቆ እና ብርሀኑ በቀለ በጉዳት ብሩክ ኤልያስ በሀዘን ምክንያት እንዲሁም ኤርሚያስ በላይ በአምስት ቢጫ ካርዶች ቅጣት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ አልመጡም።

ኢትዮጵያ ቡና የተመስገንን ጉዳት ተከትሎ ወደ ቀደመው የ4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፉ የሚመለስበት ዕድል የሰፋ ነው። በተታተይም ሱለይማን ሎክዋ ወደ ሜዳ ከተመለሰ ቡድኑ በተጋጣሚ የመከላከል ቀጠና ውስጥ ክፍተቶችን ለመፍጠር የሚረዳውን ከአቡበከር ናስር ጋር የነበረውን ጥምረት መልሶ ሊያገኝ ይችላል። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ማፈግፈግን ምርጫቸው ሊያደርጉ የሚችሉት ደቡብ ፖሊሶች ጥሩ አቋም ላይ ወደሚገኘው የመስመር አጥቂያቸው ኄኖክ አየለ በአጠቃላይ ወደ ፊት መስመር ከሚልኳቸው ኳሶች አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– በአምስት የሊግ ጨዋታዎች የመገናኘት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በአቻ ውጤት ተለያይተው ያማያውቁ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና አራቱን በድል ሲያጠናቅቅ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አንድ ጊዜ አሸንፏል።

– በ2002 የውድድር ዓመት 5-0 ያሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ ኢትዮጵያዊ ቡና በአምስቱ ጨዋታዎች 13 ግቦች ሲያስቆጥር ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አራት ግቦች አሉት።

– ዘንድሮ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና በቀሪዎቹ ጨዋታዎች አምስት ጊዜ አሸንፎ አንዴ ነጥብ ተጋርቷል።

– ከሀዋሳ ውጪ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንዴም ሦስት ነጥብ ይዞ መመለስ ያልቻለው ደቡብ ፖሊስ ሁለት የ 1-1 ውጤቶች እና ሦስት የ1-0 ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– በዘንድሮው የሊጉ ውድድር አራት ጨዋታዎችን የዳኘው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ ይመራዋል። ኢትዮጵያ ቡናን ለሁለተኛ ጊዜ የሚዳኘው አርቢትሩ እስካሁን በአራት ጨዋታዎች 17 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ወንድይፍራው ጌታሁን– እያሱ ታምሩ

አማኑኤል ዮሃንስ

ዳንኤል ደምሴ– ሳምሶን ጥላሁን

ካሉሻ አልሀሰን

አቡበከር ናስር – ሱለያን ሎክዋ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ዳዊት አሰፋ

ዘሪሀን አንሼቦ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አናጋው ባደግ

ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ሙሉዓለም ረጋሳ

መስፍን ኪዳኔ – በኃይሉ ወገኔ – ኄኖክ አየለ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *