ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አስመዝግቧል

14ኛው ሳምንት ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ አንድ ጨዋታ ሲደረግ ሲዳማ ቡና ደደቢትን 3-0 በሆነ ውጤት ረቷል።

ሲዳማ ቡናዎች በ12ኛው ሳምንት መከላከያን በሜዳቸው ከረቱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪን ሲያደርጉ ዮሴፍ ዮሃንስ እና ግሩም አሰፋን በማስገባት ዮናታን ፍሰሀ እና ዳግም ንጉሴን ያሳረፉ ሲሆን ደደቢቶች ደግሞ በስሑል ሽረ ባሳለፍነው ሳምንት ሽንፈትን ከገጠመው ስብስብ ውስጥ ኩማ ደምሴ ፣ አክዌር ቻሞ እና ዓለምንአንተ ካሳን በአንዶህ ኩዌኩ ፣ አብርሀም ታምራት እና አሌክሳንደር ዐወት ተክተዋል።

የሲዳማ ዞን ስፖርት ቢሮ ውስጥ ረጅም ዓመታትን ሰርተው በቅርቡ በጡረታ ከተገለሉ በኃላ በሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው ትናንት በድንገት ላረፉት አቶ ቢራራ ገቢሶ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኃላ ነበር ጨዋታው ጅማሮን ያደረገው፡፡


አጀማመራቸው ጥሩ የነበረው እና ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ የነበራቸው የበላይነት ቀዝቅዞ የታየባቸው ደደቢቶች መሀል ሜዳ ላይ የዓብስራ ተስፋዬ ከሚያደርገው የጎላ እንቅስቃሴ ውጪ ወደ ግብ የሚደረግ አጋጣሚን ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች በአንፃሩ አጀማመራቸው በቅብብሎች ስህተት የተሞላ ቢሆንም በሂደት ግን ወደ ጨዋታው ምት ሲገቡ በእንቅስቃሴ ውጤታማ ባይሆኑም በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል በመድረሱ የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡ ከሌላው ጊዜ አንፃር በአጨዋወታቸው በአብዛኛው ወደ ግራ መስመር አድልተው ስኬታማ በነበረው የግራ ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ተደጋጋሚ የማግባት ዕድሎችን ሲፈጥሩም ተስተውሏል፡፡

3ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን በግራ በኩል ወደ ግብ ክልል እየገፋ ገብቶ ለአዲስ ግደይ ሰጥቶት አዲስ ከግብ ጠባቂው ማቲውሲ ጋር ተገናኝቶ ማታውሲ ያስጣለው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ መረጋጋት የተሳነውን የደደቢት የተከላካይ ክፍልን ሲረብሹ የታዩት ሲዳማዎች በአራት ደቂቃዎች ውስጥ የተገኙትን የማዕዘን ምቶች ወንድሜነህ ዓይናለም ሲያሻማቸው ሚሊዮን በግንባር ገጭቶ ወደ ውጪ የወጡበት አጋጣሚዎችም የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

ገና በ6ኛው ደቂቃ ላይ በደደቢት በኩል በግሉ የተለየ ነገር ለመፍጠር ሲሞክር የነበረው የዓብስራ ከጉዳት ህክምና አድርጎ ዳግም ወደ ሜዳ ከገባ በኃላ ደደቢቶች የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ማግኘት ችለው ነበር። የቅብብል ስህተት ሲሰሩ ከነበሩት ሲዳማ ቡናዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ከግርማ በተቋረጠ ኳስ ደደቢቶች ያደረጉት ሙከራ በተሻለ ለግብ የቀረቡበት ነበር፡፡ ሆኖም ሚሊዮን ሰለሞን ከግራ በኩል ሲያደርግ የነበረው ጥረት 26ኛው ደቂቃ ላይ ሰምሮለታል፡፡ ተጫጫቹ ወደ ሳጥን ጠርዝ ደርሶ ለመሀመድ ናስር ሰጥቶት መሀመድ አጋጣሚውን ወደ ግብነት መለወጥ ችሎ ሲዳማን ቀዳሚ አድርጓል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ የነበራቸውን የእንቅስቃሴ የበላይነት ያጡት ደደቢቶች ቶሎ ቶሎ ለጥቃት ሲጋለጡ ውለዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ከግሩም አሰፋ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ አንድ ሁለት ቅብብል የተገኘችውን ኳስ ሀብታሙ ሞክሮ ማታውሲ መልሶበታል፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ በተቃራቡበት ጊዜም ግርማ ከሚሊዮን የተቀበለውን ኳስ በግብ ክልሉ ጠርዝ ሲልካት ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ የሲዳማን የግብ መጠን ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ በጭማሪው ደቂቃ አብስራ ተስፋዬ ምላሽ የሰጠች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን ቢያገኝም በሲዳማ ተከላካዮች ሊነጠቅ ችሏል፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው የተቀዛቀዘ ሆኖ እና ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ፉክክሩ ወርዶ የታየበት ነበር፡፡ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ገና በጊዜ ቅያሪ ያደረጉት ደደቢቶች ቅያሪያቸው እምብዛም ውጤታማ አልነበረም። አልፎ አልፎ ዕድሎችን ቢያገኙም ጨራሽ የሚባል አግቢ ተጫዋች ያለመኖሩ ቡድኑ በቀላሉ ለጥቃት ለመጋለጡ ምክንያት ሊሆነው ችሏል፡፡ እንዳለ ከበደ እና ኤፍሬም ጌታቸው አከታትለው በማስወጣት አብዱላዚዝ ዳውድ እና ተመስገን በጅሮንድን ቢያስገቡም ባሰቡት ልክ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በጨዋታው የአዲስ ግደይ መቀዛቀዝ ቢታይም በሚሊዮን እንቅስቃሴ የመስመር አስፈሪነታቸውን ማሳየት የቀጠሉት ሲዳማዎች ጉዳት በገጠመው ዳዊት ተፈራ ምትክ በገባው ትርታዬ ደመቀ ተሻጋሪ ኳሶች የማጥቃት አማራጭን መውሰዳቸው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥቅሟቸዋል።

55ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ወንድሜነህ አክርሮ መትቶ ማታውሲ እንደምንም ካወጣበት በኃላ 61ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ወደ ግብ እየነዳ ገብቶ ከመሀመድ ጋር ግሩም ቅብብሎችን ካደረገ በኃላ መሀመድ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ለቡድኑ ደግሞ ሶስተኛ ጎል ሆናለች፡፡ ከግቧ በኃላ በመልሶ ማጥቃት ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ደደቢቶች በፈጠሩት የመስመር ጥቃት ኳስ የዓብስራ እግር ስር ደርሳ ለዳግማዊ አባይ ሰጥቶት ከግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ጋር ተገናኝቶ ማግባት የሚችላትን ግልፅ አጋጣሚ ፍቅሩ አስጥሎታል፡፡ ሙከራዋ ደደቢቶች በሙሉ የጨዋታው ሂደት የፈጠሯት የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ በሲዳማ በኩል 70ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን ያሻገራትን ኳስ ትርታዬ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወጥታበታለች፡፡ 75ኛው ላይም መሀመድ ናስር ሌላ አጋጣሚን ከአዲስ አግኝቶ ሳይጠቀም ሲቀር አዲስ እና ሀብታሙ በመጨረሻው ሰዓት ከርቀት አክረው መትተው ማታውሲ ያወጣባቸው ኳሶችም የቡድኑ የመጨረሻ ሙከራዎች ሆነዋል ፤ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና 3-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *