የአሰጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 5-2 መከላከያ

መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታድየም መከላከያን አስተናግዶ 5-2 የረታበት ጨዋታን አስመልክቶ የሁለቱ ቡድኖች አልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ለመቐለ ደጋፊዎች ይሄ አዲስም ብርቅም አይደለም ” ገብረመድኅን ኃይሌ

ስለ ጨዋታው 

በእንደዚህ የማሸነፍ መንገድ ላይ ስትሆን ጨዋታውን ነጥለህ መለካት አትችልም። ማለትም የመጀመርያው አጋማሽ እንዲ ነበር ሁለተኛ አጋማሽም እንዲህ ነበር ማለት አትችልም። ወሳኙ ነገር ማሸነፍ እና የማሸነፍ መንፈሱን መጠበቅ ነው። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ጥሩ ነበር።

ሰለ ቀጣይ

ተስተካካይ ጨዋታ ሊኖረን ይችላል። ግን እሱን ከግምት እያስገባን አንጫወትም። ያሉብንን ጨዋታዎች እግር በእግር ማሸነፍ እና ከፊታችን ያሉትን ክለቦች መቅደም ነው። የማሸነፍ መንፈሳችን እያደገ ነው።  ይህን ጠብቀህ መሄድ ነው ዋናው ነገር።

ስለ ደጋፊው እና ስለ ስቴድየም ድባብ

ለመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ይሄ አዲስም ብርቅም አየረደለም። አምናም ቡድኑን እንዲ አድርጎ እየደገፈ ነበር። አሁንም እየደገፈን ነው፤ ከዚህ በላይም እንጠብቃለን። ዛሬ ደጋፊው ከዚ በላይ ስቴድየሙን ይሞላዋል ብዬ ገምቼ ነበር። ሆኖም ድጋፉ ልዩ የሆነ አቅም እየሰጠን ነው፤ ይቀጥል።

“ያሰብነው አልተተገበረም፤ ይህንን ለቀጣይ እናርማለን” – ሥዩም ከበደ – መከላከያ (በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ)

ስለ ጨዋታው

አጀማመራችን ጥሩ ነበር፤ እስከሆነ ደቂቃ ድረስም እንዳሰብነው እየሄድን ነበር። በጎልም የቀደምነው እኛ ነበርን። ነገር ግን ግብ ካስቆጠርን በኃላ ወድያው ነው የገባብን። በዛሬው ጨዋታ የመከላከል አደረጃጀታችን ጥሩ አልነበረም። የጎሉ ቁጥርም እሱን ነው የሚነግረን። በሳጥን ውስጥ መጠንቀቅ አለብህ አደጋ የማይፈጥር ቦታ ላይ ያልሆነ ውሳኔ መወሰን፣ መጠንቀቅ ሲገባህ መግፋት ዋጋ አስከፍለውናል። ይህም በመጀመርያ ደቂቃዎች በአማካይ እና አጥቂ  መስመር የነበረውን መልካም አጀማመር ይዞብን ነው የጠፋው። ቡድናችን በተወሰነ ቦታ ላይ ማስተካከል ይኖርብናል። በተለይም መከላከል ላይ የተደራጀ አልነበረም።

ቡድኑ ጫና በፈጠረባቸው ደቂቃዎች ንፁህ የግብ ዕድል አለመፍጠሩ አጨዋወቱን እንዲቀይር አያስገድድም?

በዛሬው ጨዋታ ከተለመደው ቀይረን ነው የገባነው። 4-2-3-1 ይዘን ገብተን ተመስገንን ከሶስቱ አማካዮች በአንዱ ጠርዝ አሰልፈን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ይህ ያደረግንበት ምክንያትም አንደኛ ሜዳው ትልቅ ነው። ከዛ በተጨማሪ የነሱ ተጫዋቾች በተለይም ፊት ላይ ፈጣኖች ናቸው። ቦታዎች በአግባቡ ይጠቀማሉ። ቡድኑ መከላከል ላይም ጥሩ ስለሆነ እኛም በመሃል ሜዳ ላይ ብልጫ ወስደን ፍሬውንም ተመስገንንም ወደ ሳጥን ተጠግተው የማጥቃት አማራጭ እንዲፈጥሩ ነበር አጨዋወታችን የቀየርነው። ግቡ እስከገባበት ደቂቃ ድረስ መልካም ነበር.። በዛሬው ጨዋታ ድክመታችን ደግሞ 4-4-2 ስትጫወት ሁለቱም የመስመር ተከላካዮች ቡድንህን ካልረዱ ክፍተት አለው የማጥቃት አጨዋወትህ ያበላሻል። እንዲህም ሆኖ የነሱን ፈጣን አጥቂዎች ለመከላከል ሞክረናል። ግን የሚደረጉት ነገሮች በስህተት የታጀቡ ነበሩ፤ እነዛ ነገሮች ዋጋ አስከፍለውናል።

ቡድኑ በድፍረት የተከላካይ ክፍሉን እጅግ ወደ መሃል ሜዳ አስጠግቶ ስለ መጫወቱ

ጎሎች ከተቆጠረብህ ተከላካይ ክፍልህ አርቀህ ጨዋታው በቀላሉ መቆጣጠር አትችልም። ለአጨዋወታችን የሚሆን ተፈጥሯዊ የመስመር ተከላካይ የሉንም፤ ማለት እንደጠበቅነው አይደሉም። የመሃል ተከላካዮቻችን አስቀርተን የመስመር ተከላካዮቹ በማጥቃቱ እንዲሳተፉ እንፈልጋለን። ግን ይህ ራሱ የሆነ ብቃት ያስፈልገዋል። በዚህም የማጥቃት አጨዋወታችን መጠናከር አልቻለም። ለዚህም በአጥቂዎቹ እና አማካዮቹ ያለው ክፍተት እንዳይሰፋ የግድ ተከላካዮቹ ገፍተው መግባት አለባቸው። በሁለተኛው አጋማሽ ቀድሞ የምንጠቀምበትን 4-4-2 ዳይመንድ ይዘን ገብተናል። ከዛ በኃላ የተሻሉ ነገሮች ፈጥረናል። ነገር ግን አማኑኤል የኛን ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች የአቋቋም ስህተት ለሱ ዕድል ሰጥቶታል ግብ እንዲያገባ።

ሁለት ከተከላካይ ጀርባ ያለው ቦታ መጠቀም የሚችሉ አጥቂዎች ከያዘ ቡድን ጋር እንደመጫወቱ የተከላካይ ክፍሉን ወደ መሃል ሜዳ ማስጠጋት ስለመምረጣቸው

እንደዛ ስንወስን ተከላካዮቻችን ሌላ ሃላፊነትም ሰጥተናቸው ነበር፤ አማኑኤል ከዕይታቸው እንዳይርቅ። ምክንያቱም የቡድኑ ትልቁ የማጥቅያ መሳርያ እሱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቹ በግሉ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ ቦታ አመራረጡ፣ ኳስ አገፋፉ በጣም ጥሩ ነው። ጠዋት ከጨዋታ በፊት በጥቁር ሰሌዳ ሳስረዳቸው የነበረውም ይሄንኑ ነው። የመጫወቻ ቦታ እንዳይሰጡት። ታክቲካሊ ፉርሽ አድርጎብናል፤ አልተተገበረም። ይህም ለቀጣይ እናርማለን ትልቅ ትምህርት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *