ሪፖርት | ድሬዳዋ ከሜዳው ውጪ በጊዜ በተቆጠረች ጎል ሀዋሳን አሸንፏል

ከ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች አንዱ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በገናናው ረጋሳ ብቸኛ ግብ በድሬዳዋ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳዎች ከመከላከያ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ያኦ ኦሊቨር እና አስጨናቂ ሉቃስን ከጉዳት በመጡት ደስታ ዮሀንስ እና ዳንኤል ደርቤ ሲለውጧቸው በ12ኛው ሳምንት ከሽረ ከሜዳው ውጪ ያለግብ ካጠናቀቀው ስብስባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች እንደ ሀዋሳ ሁሉ የሁለት ተጫዋች ለውጥን ሲያደርጉ ጉዳት የገጥመው ፍቃዱ ደነቀ እና ዛሬ የተሞሸረው ረመዳን ናስርን በበረከት ሳሙኤል እና ከጉዳት በመጣው ረምኬል ሎክ ተክተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም ብልጫን ወስደው በመጫወት ገና ከጅማሮው ለማጥቃት  የሞከሩት ሀዋሳዎች ቢሆኑም  የተከላካዮቻቸው ስህተት ታክሎበት በጊዜ በመልሶ ማጥቃት ሊቆጠርባቸው ችሏል፡፡ 3ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ ግርማ ያሳለፈለትን ኳስ በዕለቱ በቀኝ በኩል ከመሳይ ጻውሎስ ጋር እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ገናናው ረጋሳ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ከሀብታሙ ወልዴ ጋር በመቀባበል ድሬዳዋን አሸናፊ ያደረገችውን ብቸኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።  ከግቧ በኃላ ዘነበ ከበደ ከቆመ ኳስ ካደረጋት ሙከራ ውጪ ድሬዎች አሰላለፋቸውን ገና በጊዜ ከ4-4-2 ወደ 5-4-1 ቀይረው በመከላከሉ ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡ 

ያለፉትን ጨዋታዎች በጉዳት የነበሩት ዳንኤል እና ደስታን ለመጠቀም የሜዳውን የጎን ስፋት በመጠቀም ከተሻጋሪ ኳሶች ለማጥቃት ያለሙት ሀይቆቹ በርካታ ጊዜያቸውን በድሬዳዋ የግብ ክልል ቢያሳልፉም ያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎች በቀላሉ ሲያመክኑ አልያም በዕለቱ በጥብቅ ሲከላከሉ በነበሩት የድሬዳዋ ተጫዋቾች ጥረት ሲከሽፍባቸው ተስተውሏል፡፡ ሰብረው ለመግባት በተቸገሩት ሀዋሳዎች በኩል አልፎ አልፎ  አማካዩ ኄኖክ ድልቢ ከርቀት አክርሮ በመታት ግብ ለማስቆጠር ጥረት የሚያደርግበት ሂደት የነበረ ቢሆንም ሙከራዎቹ በሳምሶን አሰፋ ጥረት ግብ ከመሆን ሲተርፉ ይታይ ነበር። 11ኛው ደቂቃ በእስራኤል እሸቱ እና ታፈሰ ሰለሞን ቅብብል ወደ ግብ ክልል በመንደርደር ላይ የነበረው ደስታ ዮሀንስ ከታፈሰ በደረሰው ኳስ ከግብ ጠባቂው ሳምሶን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳምሶን አስጥሎታል፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን ምት ዳንኤል ደርቤ አሻምቶ አዳነ ግርማ ተገልብጦ የመታትን አስደናቂ ኳስ በረከት ሳሙኤል ከግቡ ጠርዝ ላይ ያወጣበት አጋጣሚም ሀዋሳዎች ላሳዩት ብልጫ ማሳያ የምትሆን ነበረች፡፡

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ አብዛኛው ተጫዋቾቻቸውን በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በመገደብ አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዎች ከሀዋሳ ተጫዋቾች እግር ስር በሚነጠቅ እና ከሳምሶን አሰፋ በረጅሙ የሚለጋ ኳስ ለግብ አስቆጣሪው ገናናው በማድረስ በቀኝ በኩል ለማጥቃት ሙከራን አድርገዋል፡፡ ገናናው ረጋሳ በዚሁ አጨዋወት የተገኘችዋን ዕድል ያመቻቸለትን ኳስ ሐብታሙ ወልዴ በግንባር ገጭቶ የወጣችበት እንዲሁም ገናናው ከሚኪያስ ያገኛትን አጋጣሚ በሀዋሳ ተከላካዮች የተነጠቀበት ሂደት ሌላው ሙከራቸው ነበሩ፡፡ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾቻቸው ፍሬድ እና ሚኪያስን ከማጥቃቱ ይልቅ ወደ መከላከሉ እንዲያመዝኑ ማድረጋቸውም ግቧን አስጠብቀው እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡ አቻ ለመሆን ቶሎ ቶሎ የሳምሶን አሰፋን መረብ ለመፈተሽ ጥረቶች ያልተለያቸው ሀዋሳዎች 34ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን በግራ በኩል ወደ ግብ የላካት ኳስ አዳነንና ሳምሶን ቢያፋጥም አዳነ መቷት ሳምሶን በቀላሉ ይዞበታል፡፡ ከዚህች አጋጣሚ በኃላ ራምኬል ሎክ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኛትን ኳስ ሳይጠቀምባት ለእረፍት ወተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በሜዳ ላይ ተቀዛቅዞ የነበረውን አዳነ ግርማን አስወጥተው ገብረመስቀል ዱባለን በማስገባት የግብ ፍለጋን አማራጫቸው ያደረጉት ሀዋሳዎች ቢሆኑም ድሬዳዋዎች የኋላ በራቸውን በጥብቅ አስጠብቀው ሊወጡ ችለዋል፡፡ በተለይ ድሬዳዎች ተጫዋቾቻቸው ሜዳ ላይ እየወደቁ ነጥብን ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ከሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ተቃውሞን ገጥሞታል፡፡ 

በግራ እና ቀኝ መስመራቸውን በደስታ ዮሀንስ እና ዳንኤል ለመጠቀም ያለሙት ባለሜዳዎቹ በዚህ አጨዋወታቸው ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡ ታፈሰ ሰለሞንን ከአማካይ ክፍል አስወጥተው ቸርነት አውሽንም ማስገባት ቢችሉም ሄኖክ ድልቢ ባገኛቸው ነፃ እና ክፍት የማግባት አጋጣሚ ከርቀት ከሚሞክራቸው ኳሶች እና እስራኤል እሸቱ ለማድረግ ከሚያደርገው የማጥቃት አማራጭ ውጪ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ውጤት መቀየር አልቻሉም። 

ድሬዳዋዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው ቢቀርቡም የኳስ ቅብብሎቻቸው የሚቆራረጡ ነበሩ። 68ኛው ደቂቃ ገናናው ረጋሳ የፈጠረለትን እድል ዮናታን ከበደ ያመከናት ኳስም ብቸኛ ሙከራቸው ሆናለች፡፡ ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድም ጨዋታው በድሬዳዋ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ 

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በክለቡ ተጫዋቾች እና በእለቱ ዋና ዳኛ ወልዴ ንዳው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን አሰምተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *