ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ ከተማ መሪነቱን ሲያስጠብቅ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ወልዲያ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ዘጠነኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች እሁድ፤ አንድ ጨዋታ ደግሞ ዛሬ ተከናውነዋል። ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ በተጠናቀቁበት የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር ሰበታ ከተማ በመሪነቱ ሲቀጥል ለገጣፎ ለገዳዲ እና ወልድያ ከተማም አሸንፈዋል። ገላን ከፍተኛውን ድል ያስመዘገበ ቡድንም ሆኗል።

ዛሬ በተካሄደ ብቸኛ መርሐ ግብር ዱከም ላይ በ4:00 አውስኮድን የገጠመው ገላን ከተማ 5-0 አሸንፏል። ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ተጭነው መጫወት የቻሉት ገላኖች ግብ ማስቆጠር የቻሉት ገና በጊዜ ነበር። በ6ኛው ደቂቃ ጅብሪል አህመድ ከመሐል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ፊት በመግፋት የገላንን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት ገፍተው ለመጫዋት ሙከራ ያደረጉት አውስኮዶች ስኬታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። ኳስ እግራቸው ስር ስትገባ ወደፊት የሚሳቡት አውስኮዶች የተከላካይ ክፍላቸው በቁጥር አንሶ ሲስተዋልም ነበር። ይህን የየረዱት ገላኖች ወደፊት በሚጣሉ ኳሶች በጅብሪል አህመድ፣ አንተነህ ደርቤ እንዲሁም ሚካኤል ደምሴ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። በ32ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደምሴ ለገላን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ሲችል እንግዳው ቡድን  በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ይህን ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያሰተናግዱ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


በ47ኛው ደቂቃ ላይ ለራሱ ሁለተኛ ጎል ለቡድኑ ሶስተኛ ጎል ጅብሪል አህመድ አስቆጥሮ መሪነቱን ሲያሰፋ ከግቡ መቆጠር በኋላ በእንቅስቃሴ ተሽለው የታዩት አውስኮዶች ጫና መፍጠር ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም ሐቁምንይሁን ገዛኸኝ፣ ኤርሚያስ ኃይሌ እና ሙክታር ሀሰን ያደረጉት የግብ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። በ62ኛው ደቂቃ በሚካኤል ደምሴ አማካኝነት አራተኛውን ጎል ያስቆጠሩት ገላኖች ወደ ኋላ አፈግፍገው ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት የተሳካ ሲሆን አልፎ አልፎ የሚፈጥሩት የግብ እድል ተጨማሪ ጎል አስገኝቶላቸዋል። በ87ኛው ደቂቃ ጅብሪልን ተክቶ የገባው እሸቱ ጌታሁን የቡድኑን አምሰተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨውታውም ገላን ከተማ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 


የእሁድ ጨዋታዎች

ወደ ደሴ ያቀናው ሰበታ ከተማ መሪነቱን ያስጠበቀበትን ድል ደሴ ከተማን 1-0 በማሸነፍ አስመዝግቧል። በ28ኛው ደቂቃ ናትናኤል ጋንቹላ ሰበታን ቀዳሚ ሲያደርግ በ43ኛው ደቂቃ ጫላ ዲሪባ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል። በ82ኛው ደቂቃ አላዛር ዝናቡ ለደሴ ግብ ቢያስቆጥርም ቡድኑን ከሽንፈት ሳይታደግ ጨዋታው በሰበታ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ለገጣፎ ላይ የምድቡ ተጠባቂ የነበረው የለገጣፎ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በለገጣፎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 10:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ፍቃደ ያስቆጠራት ግብ ለለገጣፎ ወሳኟን ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች። በነጥብ ከሰበታ ከተማ እኩል በመሆን በግብ ልዩነት ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ለገጣፎዎች በቀጣይ መርሐ ግብር ከሰበታ የሚደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል።

ወልዲያ ላይ ፌዴራል ፖሊስን የገጠመው ወልዲያ 3-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል። ከአንደኛ ሊግ መርሐ ግብር በኋላ 10:00 በጀመረው ጨዋታ  የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቂቂያ ላይ ተስፋዬ ነጋሽ ቀዳሚውን ግብ ሲያስቆጥር ከዕረፍት መልስ በ48ኛው እና በ58ኛው ደቂቃ ላይ ዐቢይ ቡልቲ አከታትሎ ማስቆጠር ችሏል።

ኮምበልቻ ላይ ወሎ ኮምበልቻ ከ አክሱም ያደረጉት ጨዋታ በወሎ ኮምበልቻ 1-0 በሆነ ውጤት ሲጠናቀቅ ቡራዩ ላይ አቃቂ ቃሊቲ አብዱልቃድር ናስር በ11ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ ከሜዳው ውጪ ቡራዩን ማሸነፍ ችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *