ሀ-20 ምድብ ሀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መሪነት ከፍ ብሏል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲደረጉ በምድብ ሀ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ አሸንፈዋል።

ቅዳሜ 08:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአአ ስታድየም ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፓርት አካዳሚን ገጥሞ 3ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የበላይ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሉክ ፓውሊን በጨዋታና በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 2ለ0 የበላይ የሆኑት ገና በጊዜ ነበር፡፡

ጊዮርጊሶች የበላይ በነበሩበት በዚሁ አጋማሽ በተለይ በግራ መስመር ተመላላሻቸው በሆነው በረከት ማተቤ በኩል በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ተስተውሏል፡፡ የሁለተኛ አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአንጻራዊነት ከመጀመሪያው በተሻለ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ታይቶበታል፡፡ የ2ለ0 ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚዎች በግብ ሙከራ ባይታጀብም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል፡፡

እምብዛም የግብ ሙከራዎች ባልታዮበት በሁለተኛው አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቀኝ መስመር ተመላላሽ አቡበከር ሙራድ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ጥሩ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ፤ በደቂቃዎች ልዩነት በተመሳሳይ ሂደት የተገኘውን ኳስ የቀኝ መስመር ተመላላሹ በረከት ማተብ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል ኳሱ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ዳግማዊ አርዓያ በድጋሚ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የአካዳሚው ግብጠባቂ አቤነዘር ጌሰሴ በግሩም ሁኔታ ሊይዝበት ችሏል፡፡

በ70ኛው ደቂቃ የአካዳሚው አማካይ ሰለሞን ያለው ከጊዮርጊስ ሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ በመምታት ማራኪ የሆነች ግብን አስቆጥሮ ልዩነቱን ወደ አንድ በማጥበብ የቡድኑን ተስፋ ያለመለመች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በዚህች ግብ የተነቃቁ የሚመስሉት አካዳሚዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል፡፡ ነገርግን በ76ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአካዳሚዎች ሳጥን የግራ ጠርዝ ያገኙትን የቅጣት ምት በረከት ማህተቤ ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ሜዳ የገባው አቤል አዱኛ የቡድኑን መሪነት ወደ ሶስት ማሳደግ ችሏል፡፡ በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ አካዳሚዎች ያገኙት የፍፁም ቅጣት ምት ሐቢብ ዛኪር አስቆጥሮ ጨዋታው በጊዮርጊሶች የበላይነት ተጠናቋል፡፡

ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ ከሜዳው ውጪ መከላከያን የገጠመው ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 2-1 ሲያሸንፍ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከ አምቦ ጎል ፕሮጀክት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *