የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የመጀመርያው ዙር ተገባዷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ ዛሬ በተደረጉ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አስጠብቋል። መከላከያ እና አዳማ ከተማም ከሜዳቸው ውጪ በማሸነፍ ከመሪው እግር ስር መከተላቸውን ቀጥለዋል።

በአዲስ አበባ ስታድየም 08:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የመጀመሪያው ዙር በመሪነት ደምድሟል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች አዲስአበባ ከተማ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ8ኛው ደቂቃ ፎዚያ መሀመድ ከንግድ ባንክዋ ግብጠባቂ ጋር 1ለ1 ተገናኝታ ንግስቲ መዓዛ ያዳነችበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበረች፡፡

እምብዛም ሳቢ ባልነበረውና ተመጣጣኝ የሆነ የመሀል ሜዳ ላይ ፉክክር በታየበት በዚሁ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የግብ እይል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ከቀኝ መስመር አጥብባ ከገባች በኃላ ወደ ግብ የላከችው ኳስ የጥረቷ ግብ ጠባቂ ልታድንባት ችላለች፤ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች በ2 ደቂቃ ልዮነት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡ በ38ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ታሪኳ ደቢሶ ያሻማችውን ኳስ ተጠቅማ ረሂማ ዘርጋው በግንባርዋ በመግጨት የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ ከግቧ መቆጠር ሁለት ደቂቃዎች በኃላ በ40ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ ከረጅም ርቀት እጅግ ማራኪ የሆነች ግብን አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡ 

በ2ለ0 የንግድ ባንክ መሪነት ወደ እረፍት ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች ከእረፍት መልክ ከመጀመሪያው ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ሁለቱም ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ የንግድ ባንክዋ ትእግስት ያደታ ከርቀት በመምታት የቡድኗን መሪነት ወደ ሶስት ያሳደገችን ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ ከሶስተኛው ግብ መቆጠር በኃላ ፍፁም የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግቦችን ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወደ ዲላ ያመራው መከላከያ ጌዴኦ ዲላን 2-1 አሸንፏል። ብሩክታዊት ግርማ እና መዲና ዐወል የመከላከያን የድል ጎሎች ሲያስቆጥሩ ትንቢት ሳሙኤል የዲላን ብቸኛ ጎል አስቆጥራለች።

ወደ አሰላ ተጉዞ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን የገጠመው አዳማ ከተማ 3-1 አሸንፏል። ተከላካዮቹ ወይንሸት ጸጋዬ እና እጸገነት ብዙነህ እንዲሁም አማካይዋ አልፊያ ጃርሶ የአዳማ ጎሎች ባለቤት ናቸው።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል ወደ አርባምንጭ ተጉዞ አሳክቷል። በኤሌክትሪክ 4-2 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ መሣይ ተመስገን ሁለት፤ ዓለምነሽ ገረመው እና ዓይናለም ጸጋዬ የአሸናፊውን ቡድን ጎሎች ሲያስቆጥሩ መሠረት ማቴዎስ እና ድርሻዬ መንሳ የአርባምንጭ ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ድሬዳዋ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 2-1 አሸንፏል። የዘንድሮ ክስተት የሆችው አይዳ ዑስማን ሁለቱንም የድሬ ጎሎች በማስቆጠር ቡድኗን ለድል ስታበቃ በግሏም 11 ጎሎችን በማስቆጠር በግብ አግቢዎች ሰንጠረዥ መገስገሷን ቀጥላለች። 

ባህር ዳር ላይ ጥረት ኮርፖሬት በትዕግስት ወርቁ ብቸኛ ጎል ሀዋሳ ከተማን 1-0 ያሸነፈበት ጨዋታም የዕለቱ ሌላው መርሐ ግብር ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *