ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ነጥቡን ከመሪው ጋር አስተካክሏል

2ኛ ሳምንት ላይ መካሄድ ሲገባው ሲዳማ ቡና ለፌዴሬሽኑ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስቴዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን 2-1 በመርታት በአሸናፊነት ጉዞው ቀጥሏል።

በባዬ ገዛኸኝ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ከተመለሰው የመጀመርያ አሰላለፉ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረገው ወላይታ ድቻ በረከት ወልዴን (ጉዳት) በሐብታለም ታፈሰ፣ ዘላለም ኢያሱን ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጎል በማስቆጠር እና ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ባዬ ገዛኸኝን በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ  በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ደደቢትን 3-0 ከረታበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። ግብጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳን መሳይ አያኖ፣ ግሩም አሰፋን በዮናታ ፍስሃ፣ ዳዊት ተፈራን በዳግም ንጉሴ በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል።

በጥሩ ፉክክር ኳስን መሰረት ባደረገ አጨዋወት ተጋግሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሲዳማ ቡና በመሐል ሜዳ ክፍል ብልጫ በመውሰደ ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው ወደ ፊት የሚሄዱበት መንገድ መልካም የሚባል ቢሆንም ግልፅ የሆነ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ። ወላይታ ድቻ በጥንቃቄ በመከላከል ከራሳቸው ሜዳ ክፍል ማለፍ ሳይችሉ ኳሱን አደራጅተው ከመሄድ ይልቅ ሲዳማዎች የሚሰሩትን ስህተት በመጠቀም የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ታይቷል።

12ኛው ደቂቃ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ በመውሰድ የተጫኑት ሲዳማዎች የመጀመርያ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት በ14ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ ከመሀል ሜዳ ኳሱን እየገፋ በመሄድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን የድቻው ግብጠባቂው መኮንን በጥሩ ሁኔታ ያዳነበት የሲዳማዎች የመጀመርያ ጠንካራ ሙከራ ነበር። በተደጋጋሚ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከቀኝም መስመር ወደ ፊት የሚሄድባቸው መንገዶች እና የሚያሻግራቸው ኳሶች በሲዳማ ቡና አጥቂዎች በኩል የሚቀበል ጠፍቶ ኳሶቹ ሲባክኑ ተስተውሏል።

20ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር ወደ ድቻ ሳጥን ውስጥ በመግባት የሚያሻግረው ኳስ ተቀባይ አግኝቶ ወንድሜነህ ዓይናለም አግኝቶ አገባው ሲባል ውብሸት በፍጥነት ደርሶ እንደምንም ተደርቦ ያወጣበት ሌላ ጎል መሆን የሚችል ግልፅ  አጋጣሚ ነበር። ወላይታ ድቻዎች ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ከሚደረጉ ጥረቶች ውጭ ወጥነት የሌላቸው የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት እና አልፎ አልፎ  በመልሶ ማጥቃት በፍጥነት አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም የሚጣሉት ኳሶች ያልተመጠኑ በመሆናቸው በቀላሉ ይባክኑ ነበር። በ28ኛው ደቂቃ ፈቱዲን ጀማል ኳሱን በመሸፈን በመልስምት ጨዋታውን ለማስጀመር ሲሞክር ቸርነት ጉጉሳ ከጀርባው ደርሶ የነጠቀውን ኳስ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ቢሰጠውም በማይታመን መልኩ የሲዳማው ግብጠባቂው መሰይ አያኖ ያደናበት በድቻ በኩል በመጀመርያው አጋማሽ ያገኙት ግልፅ የሚያስቆጭ የጎል አጋጣሚ ነበር።

ሲዳማዎች በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት በነበረው በድቻ ቀኝ መስመር 35ኛው ደቂቃ ዮናታን ፍስሃ ወደፊት የተጣለለትን ኳስ ሰብሮ በመግባት ያሻገረውን አዲስ ግደይ በግንባሩ ኳሱን ከመሬት ጋር አጋጭቶ ቢመታውም ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወቶበታል። የግብ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማዎች ቢሆኑም በመልሶ ማጥቃት በድቻዎች የሚወሰድባቸው ጥቃቶች የተከላካይ ክፍላቸውን ሲረብሸው ታይቷል።

              

ውጥረት የተሞላበት ጠንካራ ፉክክር በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ ድቻዎች በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን 53ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ላይ መሳይ አያኖ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ቢሰራበትም የዕለቱ ዳኛ በዝምታ ማለፋቸው የድቻ ተጫዋቾች ተቃውሞ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። ከእረፍት መልስ ቀዝቃዛ አጀማመር ያደረጉ ቢመስሉም ሲዳማዎች በ57ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል አዲስ ግደይ ለመሐመድ ናስር ለማቀበል አስቦ በድቻ ተከላካዮች ተደርቦ ሲመለሰ ልማደኛው ወንድሜነህ ዓይናለም ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ሲዳማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። 

ከጎሉ መቆጠር ሁለት ደቂቃ በኋላ የጨዋታውን መልክ የቀየረ ክስተት ተፈፅሟል። መሐመድ ናስር ከኃይማኖት ወርቁ ጋር በፈጠሩት ሰጣ ገባ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው ድቻዎች ጫና ይፈጥራሉ ቢባልም እምብዛም ለሲዳማ ፈተና መሆን አልቻሉም። 64ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከተከላካዩ ተክሉ የነጠቀውን ኳስ  የሚቀበለው አጥቶ ወደ ጎል ሞክሮ ግብጠባቂው መኳንንት በቀላሉ የያዘበትም በሲዳማ በኩል የሚጠቀስ ነበር። 

ድቻዎች በረጃም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 75ኛው ደቂቃ ግብጠባቂው መሳይ አያኖ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ባዬ ገዛኸኝ ወደ ጎልነት ቀይሮ ድቻዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።

ጨዋታው በአስገራሚ እና እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ79ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ራቅ ብሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ወንድሜነህ ዓይናለም የመታውን አዲስ ግደይ ከተከላካዮች መሐል በመውጣት በግንባሩ ጨርፎ ጎል በማስቆጠር ሲዳማዎችን በድጋሚ መሪ መድረግ ችሏል።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ሲዳማዎች ተከላካይ በማስገባት እና አጥቂ በመቀነስ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲካላከሉ ድቻዎች ተከላካይ በመቀነስ እና የአጥቂ ቁጥራቸውን በመጨመር ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። በተለይ 87ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ቸርነት ጉግሳ መቶት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡት እና 89ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢያሱ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ኳሱን ሳያጠብቀው መትቶ መሳይ በቀላሉ የያዘበት እቻዎችን አቻ መድረግ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *