ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ድሬዳዋ ከተማ

አባ ጅፋር እና ድሬዳዋ የሚገናኙበት ሌላኛው የነገ ተስተካካይ መርሐግብር ቀጣዩ የቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት ነው።

በአምናው ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ምክንያት ተላልፈው ከቆዩ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የ4ኛ ሳምንት የአባ ጅፋር እና ድሬዳዋ ጨዋታ ነገ 09፡00 ሰዓት በጅማ ስታድየም ይደረጋል። ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋል በሜዳቸው ከባህር ዳር ጋር ነጥብ የተጋሩት ቻምፒዮኖቹ 10ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጡም በሂሳብ ስሌት መሪ የመሆን ተስፋቸው እንዳለ ነው። ነገር ግን ከሚኖርባቸው ተከታታይ ጨዋታዎች አንፃር የነገውን ጨዋታ በማሸነፍ የደረጃ መሻሻልን ባያሳኩ እንኳን ከበላያቸው ካሉት ክለቦች ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ይጠበቅባቸዋል። ወደ ሀዋሳ ካደረጉት ጉዞ ሦስት ነጥቦችን ይዘው የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ከነገ ተጋጣሚያቸው ጋር በነጥብ ተስተካክለው 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።  በሁለት ነጥብ ብቻ ከራቁት የወራጅ ቀጠና በሚገባ ከፍ ለማለትም እንደ ሀዋሳ ሁሉ ጅማ ላይም ድል የማስመዝገብ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል። 

ጅማ አባ ጆፋር ከጉዳት ያላገገመው ከድር ኸይረዲንን እና መጠነኛ ልምምድ የጀመረው ዐወት ገብረሚካኤልን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ዳንኤል አጄዬ ባለመመለሱም እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ከእጅ ጉዳቱ ያላገገመው ዘሪሁን ታደለን እንደሚጠቀም ይጠበቃል። በድሬዳዋ በኩል የመሀል ተከላካዩ ፍቃዱ ድነቀ ከጉዳቱ ያላገገመ ሲሆን በቅርቡ ጋብቻውን የፈፀመው ረመዳን ናስርም ከቡድኑ ጋር አብሮ አልተጓዘም።

ከአህጉራዊ ውድድሮች መልስ ተስተካካይ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የተጨዋቾች አጠቃቀሙ ላይ ለውጦችን ሊያደርግ ይችላል። አማካይ ክፍል ላይ በተከታታይ ጨዋታዎች የተጠቀመው የይሁን ፣ አክሊሉ እና መስዑድ ጥምረት ግን የአምናውን የቡድኑን ምርጥ አስራ አንድ ወጥነት የሚያስታውስ ነው። በሌላ በኩል የቡድኑ ጥቃት በመስመር አጥቂዎቹ ላይ የተመሰረተ መሆኑ በነገው ጨዋታ ከአማካዮቹ ጥሩ ሽፋን የሚያገኘው ድሬዳዋን ሰብሮ ለመግባት ቀላል ባለመሆኑ ከአማካዮቹ የሚነሱ ኳሶች የተሻለ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። ድሬዎች በጨዋታው ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ እንደሚኖራቸው ሲገመት ወደ ፊት አጥቂዎቻቸው ከሚያሻግሯቸው ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይጠበቃል። በዚህም ቡድኑ በሀዋሳው ጨዋታ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ገናናው ረጋሳን ብቃት መደገም የሚሻ ይመስላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋሮች በመጡበት የ2010 የውድድር ዓመት ከድሬደዋ ከተማ የተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ሲሆን ሁለቱም በየሜዳቸው የ1-0 ድልን ማሳካት ችለው ነበር፡፡

– ባሳለፍነው ሳምንት ሦስተኛ የሜዳው ላይ ጨዋታን ያደረገው አባ ጅፋር ጅማ ላይ የአንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን አሳክቷል፡፡

–  በ14ኛው ሳምንት ሀዋሳን በመርተት ከሜዳ ውጪ የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ድሬዳዋ ከተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ አንድ ነጥብ ይዞ ሲመለስ አንድ ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል፡፡

ዳኛ

– ጨዋታው በ14ኛው ሳምንት አዳማ እና ድቻን ጨዋታ በዳኘው ኢንተርናሽል ዳኛ  አማኑኤል ኃይለሥላሴ የመሀል ዳኝነት ይመራል። ከሁለቱ ተጋጣሚዎች መካከል በመጀመሪያው ሳምንት በድሬዳዋ ጨዋታ ላይ የመዳኘት አጋጣሚ የነበረው አርቢትሩ በአምስት ጨዋታዎች 19 የቢጫ ካርዶች እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)                       

ዘሪሁን ታደለ

ተስፋዬ መላኩ – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ                                                     

                               
ይሁን እንዳሻው – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ምንያህል ይመር – ሬምኬል ሎክ

ሐብታሙ ወልዴ – ገናናው ረጋሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *