ለአንድ ዓመት ቅጣት ተጥሎበት የቆየው ተጫዋች ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመለሰ


በ2010 የውድድር ዘመን ወልዲያ ከፋሲል ከነማ ባደረጉት የሊግ ጨዋታ ለተፈጠረው ሁከት መነሻ ነህ በማለት ፌዴሬሽኑ ለአንድ ዓመት ቅጣት ተጥሎበት የቆየው እና ቅጣቱን ሊያጠናቅቅ የአንድ ወር ጊዜ የቀረው ብሩክ ቀልቦሬ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል።

በወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ እና ወልዲያ የተጫወቀተው ብሩክ ቀልቦሬ የተጣለበት ቅጣት እንዲነሳለት ተደጋጋሚ ይግባኝ እና ይቅርታ ደብዳቤ ቢያስገባም በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ወደ ሜዳ ሳይመለስ ቆይቷል። ብሩክ ይህን ዓመት ከአዳማ ከተማ ጋር አብሮ ልምምድ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሊያገለግል ፊርማውን አኑሯል። የዝውውር መስኮቱ ሲከፈትም ፊርማው በፌዴሬሽን እንደሚፀድቅ ይጠበቃል። ተጫዋቹ በትናትናው ዕለት ከአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አስቀድሞ ከደጋፊዎች ጋር በይፋ ትውውቅ አድርጓል።

ብሩክ ዝውውሩን ካጠናቀቀ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ሲናገር “በጣም በቃላት የማይገለፅ አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፌያለው። ሁሉንም ነገር ምንም አንዳልተፈጠረ አድርጎ ፈጣሪ አሳልፎልኛል። ወደፊት በእግርኳስ ብቃቴም ሆነ በሌሎች ነገሮች የተሻለ ሆኜ እቀርባለሁ።” ብሏል።

ከአንድ ወር በኋላ ቅጣቱን የሚፈፅመው ብሩክ በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ አዳማ ከተማን የሚያገለግል ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *