ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በውጤታማ ቅያሬዎች ታግዞ ስሑል ሽረን አሸንፏል

በሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር መደረግ የነበረበት ነገር ግን በትግራይ እና በአማራ ክልል ክለቦች መካከል በነበረው አለመግባበት ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የባህር ዳር ከተማ እና የስሑል ሽረ ጨዋታ ዛሬ በባህር ዳር አለማቀፍ ስታዲየም ተከናውኖ በባለሜዳዎቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ዐወል (ኮሎኔል)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እንዲሁም የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራሮች በክብር እንግድነት በተገኙበት ይህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የጣናው ሞገዶቹ ሙሉ ብልጫ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ተጋባዦቹ ሽረዎች ደግሞ ተዳክመው ተይተዋል።

ከዚህ ቀደም ባህር ዳር ከተማዎች በሜዳቸው ጨዋታቸውን ሲያከናውኑ እንደሚያደርጉት ከጨዋታው በፊት ለተጋባዡ ክለብ ስሑል ሽረ በአምበላቸው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ አማካኝነት ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን ስጦታውን ክለቡን ወክሎ አምበል ሐፍቶም ቢሰጠኝ ተረክቧል።

ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ጅማ አቅንተው ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ደረጄ መንግስቱን እንዲሁም አምስት ቢጫ ካርዶች የነበሩበት አስናቀ ሞገስን በዳግማዊ ሙሉጌታ እና አሌክስ አሙዙ ተክተው ሲገቡ ስሑል ሽረዎች ደግሞ ልደቱ ለማን በሰዒድ ሁሴን ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ገና በጅማሮ ግብ ለማስቆጠር ጫና ማድረግ የጀመሩት የአሰልጣኝ ጳውሎስ ተጨዋቾች በ2ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ለሳላምላክ ተገኝ አሻምቶ ሳላምላክ ወደ ግብ በሞከረው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የሽረ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ተከላካዮቹ ወደ ውጪ ያወጡትን ኳስ በመጠቀም ግርማ ከመዓዘን ምት ጥሩ ኳስ ያሻገረውን ለመጀመሪያው ሙከራ ምንጭ የነበረው ወሰኑ በግምባሩ ሞክሮ ወቶበታል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ወሰኑ በ6ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ መሃል ሰንጥቆ በመግባት ለግርማ ዲሳሳ ያመቻቸለትን ኳስ ግርማ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ቢቃረብም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።

እነዚህ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ያስደነገጣቸው የሚመስሉት ሽረዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ ተጠግተው ክፍተቶችን ለመድፈን ሞክረዋል። መሃል ለመሃል የሚያደርጉት የማጥቂያ መንገድ ሲዘጋባቸው ወደሚታወቁበት የመስመር አጨዋወት የተመለሱት ባህር ዳሮችም በ16ኛው እና በ17ኛው ደቂቃ በጃኮ አራፋት አማካኝነት ሁለት ሙከራዎችን አድርገው መክኖባቸዋል። የአስናቀን ቦታ ሸፍኖ ሲጫወት የነበረው ወንድሜነህ ደረጄ ኳስ የባህር ዳር ተጨዋቾች እግር ስር ሲሆን ወደ ኋላ በመቅረት የቡድኑን የመከላከል ሚዛን ለመጠበቅ የሞከረ ሲሆን በተቃራኒ በግራ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ሳላምላክ ተገኝ ወደ ፊት የመሄድ ነፃነት ተሰቶት ለብዙ ሙከራዎች ምንጭ ሲሆን ተስተውሏል። በዚህም መንገድ ቡድኑ በ16፣ 19 እና በ33ኛው ደቂቃ ላደረጋቸው ሙከራዎች ኳሶችን ሲያመቻች የነበረው ሳላምላክ በተለይ የሽረ የመስመር ተከላካይ እና አማካዮች በራሳቸው ሜዳ ተገድበው እንዲቆዩ በማድረግ ተንቀሳቅሷል። በ29ኛው ደቂቃ ወሰኑ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ ወደ ፊት በመጣል ጃኮን ከግብ ጠባቂው ሃፍቶም ጋር ያገናኘው ቢሆንም ጃኮ ኳሱን እግሩ ላይ በማዘግየቱ የሽረ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ተረባርበው አውጥተውታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ደቂቃ ምንም አይነት ሙከራ ያላደረጉት ሽረዎች በጭማሪው ሰዓት ፍቅረሚካኤል ኳስ በእጁ በመንካቱ ምክንያት የተሰጣቸውን የቅጣት ምት በሸዊት ዩሃንስ አማካኝነት ሞክረው አግዳሚ መልሶባቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በውጥረት የተሞላው ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሽለው የገቡት ሽረዎች ተጋጣሚያቸው ግብ ለማስቆጠር ትቶት የሚሄደውን ሜዳ በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይቷል። በተቃራኒው ግብ ለማስቆጠር ፈልገው የነበሩት ባህር ዳሮች በ50ኛው ደቂቃ ወንድሜነህ ባሻገረውን እና ዳግማዊ ተቀልብሶ በሞከረው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ተከታታይ ቅያሪዎችን ያደረጉት አሰልጣኝ ጻውሎስ ጨዋታው ሲጀምር 4 የነበረውን የተከላካይ መስመር ወደ 3 በመለወጥ እና የአጥቂ ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች በማስገባት ይበልጥ ሽረዎች ላይ ጫና አድርገው ተጫውተዋል። ነገር ግን ሽረዎች ከርቀት የሚያገኙትን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ እየመቱ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በ70ኛው ደቂቃም ሸዊት ዮሐንስ ከርቀት ያገኘውን ኳስ በቀጥታ መቶ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ኳሷ ኢላማዋን በመሳቷ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በረጅሙ የተመታውን ኳስ አቤል ውዱ በሚቆጣጠርበት ወቅት ስህተት ፈፅሞ ያገኙትን ኳስ በጅላሎ ሻፊ አማካኝነት ወደ ግብ ሞክረው ሃሪስተን ሄሱ አድኖባቸዋል።

በ78ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ወሰኑ ያሻገረውን የመዓዘን ምት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ወርቁ በግምባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ አድርጓል። ጎል ሲያስተናግዱ የተፍረከረኩት ስሑል ሽረዎች በራሳቸው ሜዳ የተጨዋች የቁጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተሰንዝሮባቸዋል። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም ዜናው ፈረደ ከወንድሜነህ የተቀበለውን ኳስ ግብ ላስቆጠረው ፍቃዱ አመቻችቶለት ፍቃዱ በግብ ጠባቂው አናት ላይ መትቼ አስቆጥራለሁ ብሎ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ የወጣው ሐፍቶምን ተክቶ የገባው ሰንደይ ሮቲሚ አምክኖበታል።

ከደቂቃ በኋላ በፈጣን ሽግግር ወደ ባህር ዳሮች የግብ ክልል የደረሱት ሽረዎች ከግራ መስመር ኳስ አሻምተው የነበረ ሲሆን የተሻገረችውን ኳስ ያገኘው ዲሜጥሮስ ወ/ስላሴ ቡድኑን አቻ ለማድረግ በግምባሩ ቢሞክርም ኳሷ የውጪውን መረብ በመንኳት ወታለች። ግብ እንዳስቆጠረው ፍቃዱ ሁሉ ተቀይሮ የገባው እንዳለ ደባልቄ በ88ኛው ደቂቃ ከወሰኑ ዓሊ የተሻገረውን ኳስ በግምባሩ ገጭቶ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የባህር ዳሮችን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ሁለተኛው ጎል እንደተቆጠረ በነበረ ግርግር ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ለአንድ ደቂቃ ጨዋታውን ያቋረጡት ሲሆን ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ጨዋታውን አስቀጥለዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *