ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ፋሲል ከነማን በማሸነፍ ስድስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ

በ3ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ትግራይ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማን ያስተናገደው መቐለ 70 እንደርታ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ምዓም አናብስት ባለፈው ሳምንት መከላከያን ካሸነፈው ስብስብ ሓይደር ሸረፋን በኦሴይ ማውሊ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ ዐፄዎቹ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስባቸው ሚካኤል ሳማኬ እና ሱራፍኤል ዳኛቸውን በማሳረፍ በጀማል ጣሰው እና በዛብህ መለዮ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በሁሉም ረገድ ፋሲሎች ብልጫ ወስደው የታዩበት የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ያስመለከተ ነበር። በተለይም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ፋሲሎች ከተጋጣምያቸው በተሻለ በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ኤፍሬም ዓለሙ በጥሩ ሁኔታ ይዞ ገብቶ ለኢዙ ኢዙካ አቀብሎት አጥቂው መትቶ ለጥቂት በወጣችው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ዐፄዎቹ ብዙም ሳይቆዩም ኤፍሬም ዓለሙ ከርቀት ባደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ቢያደርጉም ፍሊፕ ኦቮኖ በጥሩ ሁኔታ ሊያድናት ችሏል።

ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ክልል በመድረስ ይሁን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የተሻሉ የነበሩት ዐፄዎቹ ምንም እንኳ የተጋጣሚን የመስመር መከላከል ሰብረው ከመስመር ብዙ ዕድሎች ቢፈጥሩም በቁጥር አንሰው እና ዘግይተው ወደ ሳጥን የሚገቡት የአጥቂ አማካዮች ዕድሎቹን መጠቀም አልቻሉም። ሆኖም ኢዙ ኢዙካ እና አብዱልራህማን ሙባረክ በተጠቀሰው የመስመር አጨዋወት ዕድሎች ፈጥረዋል። አብዱልራህማን ሙባረክ ያመከናት ኳስም ለግብ የቀረበች ነበረች። ከዚ ውጭ አምሳሉ ጥላሁን ከርቀት ያደረጋት ሙከራም አፄዎቹን መሪ ለማድረግ ከተቃረቡት ሙከራዎች አንዷ ነበረች። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ለሁለት ንፁህ የግብ ዕድሎች መፈጠር ምክንያት የነበረው ኤፍሬም ዓለሙ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ያደረጋት ሙከራም በዐፄዎቹን በኩል አስቆጪ ሙከራ ነበረች።

በመጀመርያው አጋማሽ ለአጥቂዎች በረጅሙ ከሚሻገሩ ኳሶች ባሻገር ለወትሮ የሚታወቁበት የኳስ ቁጥጥር ብልጫም ሆነ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ማሳካት ያልቻሉት መቐለዎች ምንም እንኳ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መመለስ ችለው የነበረ ቢሆንም ንፁህ የግብ ዕድል የፈጠሩባቸው እንቅስቃሴዎች ጥቂት ነበሩ። ከነዚህም መካከል ኦሶይ ማውሊ ከጠበበ አቅጣጫ አክርሮ መቶ መረቡን ታካ የወጣችው እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ከዮናስ ገረመው የተላከችለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ጀማል ጣሰው ያዳናት ይጠቃሳሉ። በመጀመርያው አጋማሽ የፋሲልን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ለማለፍ ሲቸገሩ የታዩት ባለሜዳዎቹ ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጪ በኦሴይ ማውሊ ዒላማውን ያልጠበቅ ሙከራ አድርገው ነበር።

ብዙም ሳቢ ያልነበረው ግን ደሞ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ እስኪያልቅ አብዛኛው ደቂቃዎች በተጫዋቾች ጉሽምያ እና ተደጋግሞ በሚሰማው የዳኛ ፊሽካ እንዲሁም እሱን ተከትለው በሚመጡ ቅጣት ምቶች እና አታካራዎች የታጀበ ነበር።

በቁጥር እጅግ ጥቂት ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ የቀረቡበት እና እንደ ቡድን የተጫወቱበት ሲሆን በአንፃሩ በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው ፋሲሎች በሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር።

ኦሴይ ማውሊ በመስመር በጥሩ ሁኔታ ገብቶ መቶ ለጥቂት በወጣችው ሙከራ የጀመሩው መቐለዎች በ54ኛው ደቂቃም ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሚካኤል ደስታ ያሻማትን የማዕዝን ምት ኦሴይ ማውሊ ከፋሲል ተጫዋቾች በላይ ዘሎ ሲገጫት በግርግር መሃል የመጣችው ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በማስቆጠር መቐለዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላ ፋሲሎች በግቧ አቆጣጠር ላይ በግብ ጠባቂው ጥፋት ተሰርቷል በሚል ከመስመር ዳኛው ጋር ቡዙ ደቂቃዎች የፈጀ ክርክር አድርገዋል።

ሜዳ ውስጥ ከዳኛ ጋር በተደጋግሚ በሚፈጠሩ ክርክሮች አንዴ ሲፈጥን አንዴ ደሞ ሲቀዘቅዝ የታየው ጨዋታው ከግቡ መቆጠር በኃላ ይህ ነው የሚባል ማራኪ እንቅስቃሴ አልታየበትም። ሆኖም በፋሲሎች በኩል ሠለሞን ሐብቴ ከርቀት ያደረጋት፤ በመቐለዎች በኩልም እንዳለ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

የመጠናቀቅያ ፊሽካ ከተሰማ በኃላም ግርግር ያልተለየው ጨዋታው የፋሲል ተጫዋቾች ከመስመር ዳኛው ጋር ብዙ ደቂቃዎች የፈጀ ክርክር ሲያደርጉ ረዳት ዳኛው አበራ አብርደው ላይም ጥቃት ደርሶበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *