ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በክልል ስታዲየሞች ሲደረጉ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም አዳማ ከተማን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ 0-0 ተለያይቷል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ከሶስት ቀናት በፊት ስሑል ሽረን አስተናግደው ካሸነፉበት የተጨዋቾች ስብስብ አሌክስ አሙዙ እና ጃኮ አራፋትን በአስናቀ ሞገስ እና ፍቃዱ ወርቁ ተክተው ገብተዋል። ተጋባዦቹ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ተስፋዬ በቀለ፣ ሱሌይማን መሐመድ እና በረከት ደስታን አሳርፈው በቴዎድሮስ በቀለ፣ ሱሌማን ሰሚድ እና ሙሉቀን ታሪኩ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል። 

የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር አምና በክለባቸው ሲጫወት ለነበረው ሙሉቀን ታሪኩ ምስጋና ለማቅረብ እና እንኳን ደህና መጣህ ለማለት የዋንጫ ሽልማት ለተጨዋቹ ያበረከቱ ሲሆን ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉትም ለእንግዳው ክለብ አዳማ ከተማ የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል። 

አካላዊ ጉሽሚያዎች በበዙበት የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ለጎልነት የቀረቡ ሙከራዎችን ያልተስተናገዱበት ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት በተለይ በመሐለኛው የሜዳ ክፍል ላይ አዘንብለው ተንቀሳቅሰዋል። በ4-1-4-1 የተጨዋች አደራደር የቀረቡት እንግዳዎቹ የባህር ዳር ተከላካይ እና አማካይ ተጨዋቾች ኳስ መስርተው እንዳይጫወቱ በማድረግ የተጋጣሚን አጨዋወት ማጥፋት ችለዋል። በአንፃሩ በሚታወቁበት 4-3-3 አሰላለፍ የገቡት የአሰልጣኝ ጳውሎስ ተጨዋቾች ኳስ መስርተው ለመጫወት ባለመቻላቸው የመስመር ላይ እና ቀጥተኛ አጨዋወትን ሲከተሉ ተስተውሏል። 

የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በ14ኛው ደቂቃ ሲደረግ ፍቃዱ ወርቁ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ከመስመር ላይ አጨዋወት የግብ ማግባት ሙከራ ያደረጉት ባህር ዳሮች በወሰኑ ዓሊ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ወደ ባህር ዳሮች ግብ ቀስ በቀስ መድረስ የጀመሩት አዳማዎች በ28ኛው ደቂቃ ጥሩ እድል አግኝተው መክኖባቸዋል። በዚህኛው ደቂቃ ከቅጣት የተሻማውን ኳስ ተጨራርፎ ያገኘው አዲስ ህንፃ ግብ ለማስቆጠር የሞከረ ሲሆን አዲስ የሞከረው ኳስ መጨረሻውን የግቡ አግዳሚ በማድረግ ወደ ውጪ ወጥቷል። 

የመስመር ላይ አጨዋወታቸውን የቀጠሉበት ባህር ዳሮች ከሶስት ደቂቃ በኋላ በወሰኑ ዓሊ አማካኝነት ጥሩ እድል አግኝተው መክኖባቸዋል። የባህር ዳር ተጨዋቾች ለማጥቃት ትተውት የሚወጡትን ቦታ በመጠቀም አዳማዎች በሱሌማን ሰሚድ አማካኝነት ጥሩ እድል አግኝተው ቀዳሚ ለመሆን ቢጥሩም ግብ ጠባቂው ሃሪስተን ሄሱ አድኖባቸዋል። ከሚያገኙት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ውጪ ከቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ያሰቡት አዳማዎች በ40ኛው ደቂቃ የተሻማውን የመዓዘን ምት ኢስማኤል ሳንጋሪ በግምባሩ ወደ ግብ ሞክሮት ወደ ውጪ ወቶባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለግብ ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ መልኩ ሙከራዎች ያልታዩበት የሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ በመድረስ በኩል ተዳክመው ታይተዋል። በተለይ አዳማ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በመምረጥ ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ በተቃራኒው ባህር ዳር ከተማዎች በመጠኑ ጫና ለማሳደር ሲጥሩ ታይቷል። በአዳማ በኩል ለግብ የቀረበ ሙከራ የተደረገው በ64ኛው ደቂቃ ሲሆን ዳዋ ሁጤሳ እራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ሃሪስተን እንደምንም አውጥቶበታል። 

የአዳማ ተጨዋቾች በራሳቸው ሜዳ በመገደባቸው እና ክፍተቶችን በመዝጋታቸው ይበልጥ የተቸገሩት ባህር ዳሮች የአማካይ መስመር ተጨዋቾቻቸውን ቀይረው በማስወጣት የአጥቂ ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾችን አስገብተዋል። ሆኖም የአዳማን የግብ ክልል መድፈር ያልቻሉት ባለሜዳዎቹ ግብ ለማስቆጠር ረጃጅም ኳሶችን በፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ዳንኤል ኃይሉ አማካኝነት እየሞከሩ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ75ኛው እና በ84ኛው ደቂቃ የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል ከርቀት ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ግብ የሞከረ ሲሆን ኳሶቹ ኢላማቸውን በመሳታቸው ወደ ውጪ ወተዋል። 

ግብ ሳይስተናግድ የቀጠለው ጨዋታው ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት የቀይ ካርድ አስመልክቷል። በ21ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው ሱሌማን ሰሚድ በ93ኛው ደቂቃም ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በማየቱ ከጨዋታው ተሰናብቷል። ጨዋታውም ግብ ሳይስተናግድ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *