ከፍተኛ ሊግ ሀ | የመሪዎቹ ፍልሚያ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ኤሌክትሪክ ልዩነቱን አጥብቧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ አስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ተከናውነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ደሴ ከተማ፣ አክሱም ከተማ እና ገላን ከተማ አሸንፈዋል።

በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ረፋድ 04:00 ላይ አክሱም ከተማን ያስተናገደው አውስኮድ 2-0 ተሸንፏል።ከዋና አሰልጣኙ ጋር የተለያየው እና በጊዜያዊነት በምክትል አሰልጣኙ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባው አውስኮድ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ከመሄዱ ባሻገር በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ተዳክሞ ነበር የቀረበው። በጨዋታው ጅማሬ 2ኛው ደቂቃ ነበር አክሱሞች በፍጥነት ወደ ጎል በመሄድ በሙልጌታ ረገሳ አማካኝነት ግሩም ጎል አስቆጥረው ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ከሦስት ደቂቃ በኋላ አክሱሞች በፈጣን አንቅስቃሴ ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል ኳስ ወደ ፊት ሄደው ሙሉጌታ ረጋሳ ብቻውን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አገባው ሲባል ኳሱ ረዝሞበት ግብጠባቂው ደረጄ ቀድሞ የያዘበት ጎል መሆን የሚችል ዕድል ነበር።

ብልጫ የተወሰደባቸው ባለ ሜዳዎቹ አውስኮዶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም በእንቅስቃሴ የወረደ በመሆኑ በመጀመርያው አጋማሽ ተጠቃሽ የሚሆን የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። እንግዶቹ አክሱሞች 18ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ያገኙትን ኳስ ክፍሎም መቶት ግብጠባቂው ደረጄ እንደምንም አውቶባቸዋል። አውስኮዶች የግብ ዕድል አይፍጠሩ እንጂ ከጨዋታው 30 ደቂቃ በኋላ በተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ በአንፃሩ አክሱሞች በጥንቃቄ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ሲፈጥሩ 40ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን አጥቂው ቴዎድሮስ መንገሻ በግንባሩ የገጨው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ከእረፍት መልስ አውስኮዶች ተጭነው ጎል ፍለጋ ቢጫወቱም ኳስ እና መረብን ማገናኘት የሚችል ሁነኛ አጥቂ ባለመኖሩ የማይታመኑ ኳሶችን አምክነዋል። በውጤት ቀውስ ውስጥ መገኘታቸውና ጫና ውስጥ መሆናቸው ቡድኑ በስነ ልቦናው ወርዶ እንዲታይ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። 71ኛው ደቂቃ የአውስኮዱ አጥቂ ተቀይሮ በመግባት ግልፅ የግብ አጋጣሚ ያልተጠቀመበት የሚያስቆጭ ነበር። 85ኛው ደቂቃ በዕለቱ በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአክሱሙ አጥቂ ሙሉጌታ ረጋሳ ከቀኝ መስመር ለአጥቂው ስለሺ ዘሪሁን አቀብሎት ስለሺ ላይ በሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ትዕዛዙ ፍቃዱ ወደ ጎልነት ቀይሮ የእንግዶቹን አክሱሞች የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። ተመሳሳይ አጨዋወት መከተላቸው አውስኮዶች ዋጋ አስከፍሏቸው በቀጠለው ጨዋታ 88ኛው ደቂቃ ማስተዛዘኛ የሚሆን ለጎሉ አንድ ሜትር የቀረበ ኳስ ተቀይሮ የገባው ኤርምያስ ኃይሌ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ አስገራሚ ሆኖ አልፋል። ጨዋታውም በአክሱም 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሌሎች ጨዋታዎች

ሰበታ ላይ የምድቡ መሪዎችን ያገናኘ የሰበታ ከተማ እና ለገጣፎ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። በ14ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ተማም ለገጣፎን ቀዳሚ አድርጎ በእንግዳው ቡድን መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ በ67ኛው ደቂቃ ናትናኤል ጋንቹላ የአችነቱን ጎል አስቆጥሮ ሰበታ ነጥብ እንዲጋራ አስችሏል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎም ሁለቱ ቡድኖች በግብ ልዩነት ተበላልጠው በሰንጠረዡ አናት ላይ መጓዛቸውን ቀጥለዋል።

በምድቡ ሌላው የሳምንቱ ተጠባቂ እና ሁለት አምና ከፕሪምየር ሊጉ የወረዱ ቡድኖችን ባገናኘው ጨዋታ ኤሌክትሪክ በሜዳው ወልዲያን ገጥሞ 2-0 በማሸነፍ ከመሪዎቹ የነበረውን ልዩነት አጥብቧል።

ዱከም ላይ አዲስ አዳጊው ገላን ከተማ ቡራዩን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። የገላንን ብቸኛ ጎል በ88ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጅብሪል አህመድ ነው።

ኒያላ ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲን የገጠመው ደሴ ከተማ አብደላ እሸቱ ገና በ3ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል 1-0 ሲያሸንፍ ኦሜድላ ሜዳ ላይ ፌዴራል ፖሊስ ከወሎ ኮምቦልቻ 1-1 ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *