ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በጊዜያዊ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ድል ተመልሷል

ከ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእሁድ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሶዶ ላይ ተካሂዶ በባለሜዳው 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻዎች በሲዳማ ቡና ከተሸነፈው ስብስብ የሶስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ኃይማኖት ወርቁ፣ ሳምሶን ቆልቻ እና ሐብታለም ታፈሰን አሳርፈው በረከት ወልዴ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ፀጋዬ አበራ ተክተዋቸው ሲገቡ ጊዮርጊሶች ከአዳማው ጨዋታ አንድም ተጫዋች ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል። ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ጋር በመለያየት በምክትሉ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻታ እየመራ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ በሶዶ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታውን ተከታትለውታል፡፡

ማራኪ ያልሆነ የሜዳ እንቅስቃሴን የተመለከትንበት ጨዋታው በረጃጅሙ ከተከላካይ እና ከግብ ጠባቂ በሚላኩ ኳሶች ማጥቃትን መሠረት ቢያደርጉም ጨዋታውን አሰልቺ ከማድረጋቸው ውጪ ሊጠቀሱ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ አስተውለናል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች በተለይ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች በተሻለ መልኩ ፈጥነው ግብ ለማስቆጠር ያለሙ በሚመስል መልኩ ጫን ብለው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ 15ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ የሰጠውን ኳስ ፀጋዬ አበራ የፍሬዘር ካሳን ስህተት ተጠቅሞ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታትም ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ወታበታለች፡፡ 22ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ የፍሪምፖንግ ሜንሱን ስህተት ተጠቅሞ አልፎት ወደ ሳጥን በመግባት አክርሮ ወደ ግብ ሲመታው ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ ሲመልሰው ባዬ ገዛኸኝ አግኝቶ በድጋሚ ስትመለስ ቸርነት ጉግሳ እግር ስር ደርሳ ወደ ግብነት ለውጧት የጦና ንቦቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከጎሉ በኋላ ያሉት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጉሽሚያዎች እና ተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካዎች የበዙበት ሲሆን የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ድቻዎች ሰዓት እየገደሉ ነው በሚልም ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተመልክተናል። 41ኛው ደቂቃ ሄኖክ አርፊጮ በግራ የጊዮርጊስ የግብ ክልል ከቅጣት ምህ አሻምቶ ፀጋዬ አበራ ጋር ደርሳ ፀጋዬ ሲመታት ለጥቂት የወጣችበት ኳስ ሌላኛው የድቻ ሙከራ ነበረች፡፡ በኃይሉ አሰፋ ከቅጣት ምት አሻግሯት አቤል ያለው መጠቀም ያልቻላት ኳስ ደግሞ የፈረሰኞቹ ብቸኛ የመጀመሪያው አጋማሽ ሙከራ ነበረች፡፡

ለእረፍት ከሜዳ እየወጡ ባለበት ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በተለይ አሰልጣኙ ስትዋርት ሀል ከእለቱ ዳኛ ዮናስ ካሳሁን ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገቡ ቢሆንም ዳኛው በዝምታ ማለፋቸው አግራሞትን አጭሯል፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ ያልተቀየረ የአጨዋወት ሂደትን የተመለከትን ሲሆን ጊዮርጊሶች አቡበከር ሳኒን በአሜ መሐመድ ለውጠው አቤልን ከአጥቂ ስፍራ ወደ ቀኝ መስመር ወጥቶ እንዲጫወት በማድረግ አቻ ለመሆን ቢሞክሩም በወላይታ ድቻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ተበልጠው ታይተዋል፡፡ 47ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከማህዘን ምት አሻግሮ ሙሉአለም መስፍን አግኝት ቢመታትም ኢላማዋን ሳጠብቅ የወጣችበት ኳስ ቀዳሚዋ የጊዮርጊሶች ሙከራ ነበረች፡፡

ድቻዎች ወደ በሁለተኛው አጋማሽ ከተከላካዮቻቸው በረጅሙ በሚላኩ አልያም ከቸርነት የግል ጥረቶች ከሚመጡ ዕድሎች ወደ ፀጋዬ አድልተው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመን አካሄድ ተከትለዋል፡፡ 72ኛው ደቂቃም የጊዮርጊስን ያልተጠበቀ የተከላካይ ክፍልን ስህተት ተጠቅመው ሁለተኛ ግብን አስቆጥረዋል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ ሄኖክ አዱኛም በአስገራሚ መልኩ አልፎ ወደ ግብ ክልል ኳሷን እየነዳ በመግባት ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ፀጋዬ ያሻገረውን ኳስ ፀጋዬ አበራ በማታሲ መረብ ላይ አሳርፎ የድቻን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ አጋጣሚን ግን ለመፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይልቁንም በ81ኛው ደቂቃ አብዱልሰመድ ዓሊ የናትናኤል ዘለቀ እና የግብ ጠባቂውን ፓትሪክ ማታሲን ስህተት ተጠቅሞ ሶስተኛ የግብ ማግባት አጋጣሚን ቢያገም ሳይጠቀምባት ቀርቷል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑ ከአራተኛ ዳኛው ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደግሞ በአሰልጣኙ ላይ ተቃውሞንም ሲያሰሙ ታዝበናል፡፡

ድሉን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ከ9 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *