ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ድሬዳዋ ከተማ

መከላከያ እና ድሬዳዋ የሚገናኙበት የነገውን ተስተካካይ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦች እንሆ…

ከሦስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር መካከል የነበረው የመከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በተስተካካይነት ተይዞ ነገ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይከናወናል። ሰባት ጨዋታዎችን ያላድል የተጓዘው መከላከያ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡናን በተከታታይ በመርታት ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ፈቀቅ ብሎ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ከድሎቹ ባሻገር በሁለቱ ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣት የቻለው መከላከያ በውጤቶቹ በተደጋጋሚ የሜዳ ላይ ስህተቶች የራስ መተማመኑን ላጣው የኋላ መስመሩ እፎይታን ያስገኘበትን ሳምንትም ነበር ያሳለፈው። ጦሩ ተጨማሪ አንድ ደረጃን ከፍ ለማለት በሚያደርገው የነገው ጨዋታ ያለምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና ሙሉ ስብስቡን በመያዝ ወደ ሜዳ ይገባል።

እንደተጋጣሚው ሁሉ 13 ጨዋታዎችን ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ ወጣ ገባ በሆነ አቋሙ የቀጠለ ሲሆን ወደ ወራጅ ቀጠናው ላለመግባት ዋስትና የሆነው ከበታቹ ያሉት ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ማጠናቀቃቸው ነው። ቡድኑ ሀዋሳን ከረታበት የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ መሻሻልን ያሳያል ተብሎ ቢጠበቅም ሌላ ድል ሊስመዘግብ ተቃርቦበት ከነበረው የጅማ ጨዋታ ነጥብ ከመጋራቱ ባለፈ በመቐለ 70 እንደርታም ሽንፈት ገጥሞታል። በሁለቱም ጨዋታዎች ከመምራት ተነስቶ ነጥቦችን መጣሉም ሌላው ድክመቱ ሆኗል። ብርቱካናማዎቹ በነገው ጨዋታ መሀል ተከላካያቸው ፍቃዱ ደነቀ ከጉዳት የማይመለስ ሲሆን በመቐለው ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው ሳሙኤል ዮሀንስ እና ዘነበ ከበደ መድረስም አጠራጣሪ ነው። ከዚህ ውጪ በቅርቡ የጋብቻ ሥነስርዓታቸውን ያደረጉት ሚኪያስ ግርማ እና ረመዳን ናስር ሙሉ ለሙሉ ወደ ቡድኑ ተመልሰዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ድሬዳዋ ከተማ እና መከላከያ ከዚህ ቀደም 14 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን መከላከያ ከፍተኛ የበላይነት አለው። በዚህም ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ መከላከያ 9 ጊዜ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተለያዩባቸው ነበሩ። መከላከያ 25 ፣ ድሬዳዋ 11 ጎሎች አስመዝግበዋል።

– አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሰባት ጨዋታዎችን ያከናወኑት መከላከያዎች ሁለት ጊዜ አሸንፈው ሁለቴ አቻ ሲለያዩ በሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል።

– ከሜዳው ውጪ አንድ የድል እና አንድ የሽንፈት ውጤት ያስመዘገበው ድሬዳዋ ከተማ አራት ጊዜ ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ የሚመራ ይሆናል። የመጨረሻውን የጅማ ጨዋታ ጨምሮ በሁለት አጋጣሚዎች ድሬዳዋን የዳኘው አርቢትሩ በስድስት ጨዋታዎች 23 የቢጫ ካርዶች እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ዓለምነህ ግርማ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ዳዊት ማሞ – ፍሬው ሰለሞን

ዳዊት እስጢፋኖስ

ፍቃዱ ወርቁ – ምንይሉ ወንድሙ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ – ምንያህል ይመር – ሬምኬል ሎክ

ኃይሌ እሸቱ – ገናናው ረጋሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *