U-20 ምድብ ለ | ፋሲል እና አዳማ ከተማ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ 7ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተካሂደው ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ተመሳሳይ የ3-1 ድል አስመዝግበዋል።

ፋሲል ከነማን ከወልቂጤ ከተማ በጎንደር ያገናኘው ጨዋታ ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በማጥቃቱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ፋሲሎች በ13ኛ ደቂቃ ላይ ቀዳሚ ሆነዋል። ዮናስ ደሳለኝ ከመሀል የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ግብ በማስቆጠር ነበር ባለሜዳዎችን መሪ ያደረገው። ሆኖም የፋሲሎች መሪነት የዘለቀዉ ለ3 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ 16ኛ ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘዉ አድኖም ፈይስን በድንቅ አጨራረስ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ወደ መሪነት ለመመለስ ተጭነዉ የተጫወቱት ፋሲሎች በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ ችለዉ ነበር፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እያዩ ድንቅ የቅጣት ምት ከሳጥን ዉጭ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታዉም የግቡን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣዉ ኳስ የሚጠቀስ ሲሆን 28ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እያዩ ከቅጣት ምት የተሻማ ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹ በድጋሚ መሪ አድርጎቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል 45ኛው ደቂቃ ላይ
ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ድንቅ ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን 3 ለ 1 በማድረግ ነበር ወደ እረፍት ያመሩት ።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለዉ የገቡት ወልቂጤዎች መሀል ሜዳ ላይ ቢንቀሳቀሱም ግብ ማግኝት አልቻሉም ነበር፡፡ በሙከራ ደረጃ 51ኛ ደቂቃ ላይ ቤቤ ታደሰ ከቅጣት ምት ያደረጋት፣ 54ኛ ደቂቃ ላይ አድኖም ፋይሰን በራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኝዉን የቅጣት ምት ቀጥታ ወደግብ መትቶ ግብ ጠባቂ ያወጣበት እንዲሁም 65ኛው ደቂቃ ላይ ኃይሌ ተክሉ ከመሐል የተሻገረለትን ኳስ ወደግብ መትቶ ኢላማዉን መጠበቅ ያልቻለዉ በወልቂጤ በኩል የሚጠቀሱ ነበሩ።

በፋሲል ከነማ በኩል በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ ቢችሉም በርካታ የግብ እድሎችን ሲያመክኑ ተስተዉሏል ። 47ኛ ደቂቃ ላይ ቢንያም አማረ  ከሳጥን ዉስጥ ያገኝዉን ኳስ ወደግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት 50ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ደሳለኝ በግራ መሰመር ወደ ግብ ይዞት የገባውን ኳስ ግብጠባቂው  ወጥቶ ቢያድንበትም ኳሱ ተጨርፎ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ጋር ደርሶ ግብ ጠባቂው ቦታው ላይ ባለመኖሩ ወደግብ ቢመታዉም ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል። በተደጋጋሚ ቦታዉን የሚለቀዉ የወልቂጤ ግብ ጠባቂ ከጎሉ ለቆ በመውጣቱ 57ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተስተዋለው ዮናስ ደሳለኝ በመቀስ ምት ቢመታም ግብጠባቂው ወደኋላ ተመልሶ አድኖበታል። ተቀይሮ የገባው ዓለማየሁ አየልኝ ከሳጥን ዉጭ ከሁለት ተከላካዮች መሀል ለመሀል  አክርሮ የመታውን ግብጠባቂው ያዳነበትም ሌላው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።

ዛሬ በተደረገ ሌላ ጨዋታ አዳማ ከተማ በሜዳው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ 3-1 በማሸነፍ መሪነቱን ከአፍሮ ፅዮን ተረክቧል።

ትላንት በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ አፍሮ ጽዮን እና አሰላ ኅብረት 1-1 ሲለያዩ የሀላባ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያ መድን ደግሞ የዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *