የፌዴሬሽኑ መግለጫ ከአምብሮ ጋር ስለተደረሰው ስምምነት

ትናንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢንተርኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል መግለጫ ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለነበረው የአምብሮ ትጥቅ አቅራቢነት ስምምነት ዙሪያ የተነሱ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናቸዋል።

ኢሳይያስ ጂራ

ከኤሪያ ጋር የነበረው ስምምነት ስለተቋረጠበት ሂደት

ብሔራዊ ቡድኑ የሚጠቀምበት ትጥቅ የጥራት ችግር አለበት ከኤሪያ ጋር ተያይዞ። ይህ ጥያቄ ከጋዜጠኞችም ሲነሳ ቆይቷል። ከስራ አስፈፃሚው ጋርም ተነጋግረንበት ነበር ፤ እንደውም ሁለት ተጫዋቾች አንለብስም እስከማለት ደርሰው ነበር በፊት። በመሆኑም ካርሎን ከጣሊያን በማስጠራት በጥራት ጉዳይ እንደማንደራደር ገልፀንለት ማብራሪያ ጠይቀነዋል። በምላሹም ምርቱ ጥራት እንዳለው እና የዘንድሮው ከአምናው በተሻም ጥራቱ ከፍ ያለ መሆኑን ገልፅጿል። ጥራት የሚለካበት መንገድ የተለያየ በመሆኑም ሌላ ወደመፈለጉ ለመሄድ ወስነናል። በመቀጠል እዚህ መነሳታቸው አስፈላጊ የማይሆኑ አምስት ስድስት የሚሆኑ ድርጅቶችን አነጋገርን። ስናነጋግር አቅርቡ ብለናቸው አቀረቡ። ይሄ ሂደት ካለቀ በኋላ አምብሮ ያቀረባቸውን ሀሳቤች ለስራ አስፈፃሚው በማቅረብ ተወያይተን ከኤርያ ጋር ያለውን ነገር ይዘን መቀጠል የለብንም ብለን ወሰንን።

ስለ አምብሮው ስምምነት

ከአምብሮ ጋር ያለን ስምምነት ከሌላው ጊዜ የተለየ ነው። በጣም ብዙ ምርት ነው ያቀረበው ፤ ሁሉም በነፃ ነው። ነገር ግን በቁጥሩ ብቻ ተሯሩጠን አልገባንበትም። ምርቱን አስልከን ስራ አስፈፃሚውን እና የብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ በመጥራት ሀሳብ እንዲሰጠበት አድርገናል። ሁለት ነጥቦች ላይም የተሰጡትን ሀሳቦች አስተላልፈናል። በውላችን ውስጥም ካለፈው ስህተት ትምህርት በመውሰድ የጥራት ደረጃው ወርዷል ብለን ባሰብንበት ወቅት ስምምነቱን ማፍረስ እንደምንችል ተካቷል። በዚህም መሰረት የካምፓኒው ኅላፊ እዚህ መጥቶ ተፈራርመናል። ለሚዲያ ይፋ የሚሆንበትን ጊዜ አንድ ላይ ለማድረግ ተስማምተን ነበር ፤ እነሱ ቀድመው ይፋ አደረጉ እኛም ከተወሰነ ሰዓት በኋላ ለቀነዋል።

ከኤሪያ ጋር የሚኖረው ቀጣይ ሀኔታ

በኤርያ በኩል ካርሎ ወደ ህግ እንደሚሄድ ፅፎልናል። በኮንትራታችን መሰረትም ይህን ማድረግ ይችላል። ከዚያ በፊት የጣልያን ኢምባሲ ያስታርቀን የሚል ሀሳብ አንስቷል። ነገር ግን እኛ እንደ ተቋም ወደ ኤምባሲው መሄድ አይጠበቅብንም። ሀሳቡ ካላቸው ራሳቸው ቢሯችን መጥተው ሊያነጋግሩን ነው የሚገባው። በመሆኑም ጉዳዩን ህግ የሚፈታው ይሆናል። ከዚያ አልፎ መቶ ሺህ ዩሮ መከፈል አለበት ተብሎ ቢወሰንበት እንኳን ፌዴሬሽኑ አትራፊ ነው። ምክንያቱም በሁለት ዓመት መክፈል ይጠበቅብን ከነበረው 180 ሺህ ዩሮ አንፃር 80 ሺህ ዩሮ ያተርፍልናል።

የአምብሮ ፍላጎት ምንጭ እና ተጨማሪ ስምምነቶች

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት። አሁን ባለንበት ሁኔታ አምብሮ አይደለም የሀገራት መንግስታትም ኢትዮጵያን እያደነቁ ያሉበት ጊዜ ላይ ነን። ስለዚህ ከዚህ አንፃር እና ካለን የህዝብ ቁጥር አኳያም ትጥቅ አምራችቾች መጠቀም ይፈልጋሉ። እኛም ገንዘብ የለንም እያልን በነፃ ሊያውም በቁጥር እጅግ በርካታ ትጥቅ ማቅረብ የሚችል ተቋም እያለ ገንዘብ ማውጣት ስለሌለብን ተስማምተናል። ከዚህ ውጪ ሌላም ስምምነት አለን ፤ አምብሮ ለደጋፊ የሚሸጠው ማልያ አለ። ከዚህ ሽያጭ ላይ ተካፋይ ለመሆን ባደረግነው ድርድርም በ2019 በ3% ጀምሮ በየዓመቱ በ1% እጨመረ 2022 ላይ 6% የሚደርስ ድርሻ ኖሮናል። በዚህም መሰረት ማልያው የትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ሲሸጥ የድርጅቱን የኦዲት ሪፖርት መሰረት ባደረገ መልኩ ተካፋይ እንሆናለን።

ከጆሳምቢን ወኪል መሆን ጭምጭታ ጋር በተያያዘ

እኛ ማግኘት የሚገባንን ጥቅም በፐርሰንት ተደራደርን እንጂ ሀገር ውስጥ ትጥቆችን ለመሸጥ ማን ወኪል ይሁን የሚለው ነገር አይመለከተንም ፤ የተቋሙም ጉዳይ አይደለም። አቶ ዮሴፍ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ስለሆነ መደራደር የለበትም የሚል መተዳደሪያ ደንብ ስለሌለ ማን እንደወሰደ ብትጠይቁኝ በበኩሌ ምንም አላውቅም።

በመቀጠል ከጋዜጠኞች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ተከታዬቹ ምላሾች ተሰጥተዋል።

ኢሳይያስ  ጂራ

የኤርያ ትጥቆች ጥራት ማነስ በምን እንደተመዘነ

በክለብ አመራርነት ሳለሁም በመጀመሪያ ድራፍት ከኤሪያ ጋር ተስማምቼ ነበር ፤ ትጥቆቹን ሳያቸው ነው ሀሳቤን የቀየርኩት። ማንም ሰው ከሚያየው ነው ጥሩ ነው አይደለም ብሎ በጥራት የሚያወዳድረው። እርግጥ ነው የጥራት መለኪያ አልተጠቀምንም ነገር ግን የሚለብሰው ሰው ነው ምቾቱን የሚያውቀው ከዚህ አንፃር ነው ያየነው።

የውሉ መቋረጥ ለኤርያ ስለተገለፀበት መንገድ

ደብዳቤ ፅፈናል። ነገር ግን ቅጣቱን መቀነስ የሚቻልበት መንገድ ካለ እንደራደራለን ፤ አሁንም አልመሸም። በሌለን ገንዘብ መውጣት የለበትም። ገና አልተወሰነም። መደራደሩን እምቢ አላልንም የነሱም ፍላጎት ያ ነው። ነገር ግን የሚደራደረው ሰው ወደ ተቋማችን ይምጣ ነው ያልነው።


ዮሴፍ ተስፋዬ (የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል)

ግለሰቡ የሚመሩት የትጥቅ አከፋፋይ ጆሳምቢን ስፖርት ከአምብሮ ጋር ቢሰራ ሰለሚፈጠረው የጥቅም ግጭት

የትጥቁ ስምምነቱ በገንዘብም ሆነ በጥራት ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ነው። ድርጅቱን እኔ አምጥቼ ለአቶ ኢሳያስ እንደሰጠውት ተደርጎ የተነገረው ነገር ግን ከዕውነት የራቀ ነው። ይሄ አስተሳሰብ መስተካከል አለበት። ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚያውቀው ሰው አለ በሱ በኩል አራት ድርጅቶችን መርጦ ነው የመጣው። እስከዛ ሰዓት ድረስ ፌዴሬሽኑም ሆነ እኔ ድርጅቱ ስለመምጣቱ አናውቅም። ከዚህ ውጪ በራሱ መንገድ ከናንተ ጋር መስራት እንፈልጋለን የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርቧል። ያንንም እንደ ድርጅት ተመልክተን ልንወያይበት ተስማምተን ተለያይተናል። እስካሁኑ ሰዓት ድረስም ጄሳምቢን ስፖርት ከአምብሮ ጋር ምንም ስምምነት አልተፈራረመም። በመሆኑም የኔም ድርጅት ሆኑ ሌሎች ሊያሸንፉ ይችላሉ። ስለጥቅም ግጭት በተመለከተም ልላለፉት አስር ዓመታት የኔ ድርጅት ለተለያዩ ክለቦች ትጥቅ ሲያቀርብ ቆይቷል። ስለዚህ የፌዴሬሽኑ አመራር ስለሆንኩኝ መግዛት አቁሙ ማለት የለብኝም። እኔ ፌዴሬሽን ውስጥ የገባውት ዮሴፍ ተስፋዬን ወክዬ እንጂ ጆሳንቢን ወክዬ አይደለም። ብሔራዊ ቡድኑም በፊትም ከኛ ጋር ትጥቅ ይገዛ ነበር። ስለዚህም በኔ እይታ ጆሳምቢን ከካምፓኒው ጋር ቢሰራ በየትኛውም መንገድ የጥቅም ግጭት ይፈጥራል ብዬ አላምንም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *