ደቡብ ፖሊስ ከሁለት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል

ደቡብ ፖሊስ ከግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ እና አማካዩ ቴዎድሮስ ሁሴን ጋር በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጅማ አባጅፋርን በመልቀቅ በአንድ ዓመት የውል ስምምነት ቢጫ ለባሾቹን የተቀላቀለው የቀድሞ ሐረር ቢራ፣ ንግድ ባንክ እና መከላከያ ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የክለቡ የመጀመርያ ተመራጭ ግብ ጠባቂ በመሆን የተጫወተ ሲሆን በተለይ ደቡብ ፖሊስ በሜዳቸው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በቀላሉ ግቦች ማስተናገዱ ተቃውሞዎች ከተመልካች እንዲያስተናግድ ሲያደርገው ቆይቷል። ይህንን ተከትሎም ከክለቡ ጋር በስምምነት ሊለያይ ችሏል። በመጀመሪያው ዙር ከክለቡ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቱ ቴሴራ ያልነበረው መክብብ ደገፉ በምትኩ በግብ ጠባቂነት ያገለግላልም ተብሏል፡፡

ሌላኛው ከክለቡ ጋር የተለያየው አማካዩ ቴዎድሮስ ሁሴን ነው። የቀድሞው ሐረር ቢራ፣ ሲዳማ ቡና እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ተጫዋች በተመሳሳይ የአንድ ዓመት የውል ኮንትራት በክለቡ ቢኖረውም ቀሪ ስድስት ወራት እያለው ተለያይቷል፡፡ ተጫዋቹ ጅማ አባጅፋርን ክለቡ በረታበት ጨዋታ ላይ ብቻ ተቀይሮ ከገባበት ጨዋታ ውጪ ለክለቡ ግልጋሎት መስጠት አልቻለም።

ላኪ ሰኒንና ኪዳኔ አሰፋን በዝውውር መስኮቱ ቀዳሚ ፈራሚ ያደረገው ክለቡ በቀጣዩ ቀናትም አንድ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ለማምጣት ያሰበ ሲሆን በተመሳሳይ ሊሰናበቱ የሚችሉ ተጫዋቾች እንዳሉም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *