ካፍ የሀዋሳ ስታዲየምን ዛሬ ጎበኘ


በ2020 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የምታስናግደው ኢትዮጵያ ጨዋታዎቹን እንደሚያስተናግዱ ከሚጠበቁት አንዱ የሆነው የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ዛሬ የካፍ እና የፌዴሬሽኑፕሬዝዳንት በተገኙበት ጎብኝት አድርገዋል።

በሀገር ውስጥ ሊጎች በሚጫወቱ ተጫዋቾች የተዋቀሩ ቡድኖች የሚያደርጉትን ይህን ውድድር ኢትዮጵያ በሀዋሳ፣ መቐለ፣ ባህርዳር እና አዲሱ የአደይ አበባ ስታዲየሞች ለማካሄድ በፌዴሬሽኑ ለካፍ በተሰጠ ደብዳቤ የተገለፀ ሲሆን የካፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች ትላንት አዲስ አበባ በመግባት ዛሬ ረፋድ ሀዋሳ ከገቡ በኋላ የስታዲየሙን ውስጣዊ እና ውጫዊ የሜዳውን ክፍል እንዲሁም የድምፅ፣ የስክሪን እና ከሜዳው ውጭ ያሉ የልምምድ ሜዳዎችን ጎብኝተዋል። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ የሚገኘውና ለቡድኖች ልምምድ ያገለግላል የተባለው ዘመናዊ ስታዲየምም ተመልክተዋል፡፡

በጉብኙቱ ላይ በካፍ በኩል የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሊዮድጋር ቴንጋ እና ሞሰስ ማጎጎ በተጨማሪነትም የካፍ የክለቦች ፍቃድ ሰጪ ኃላፊ የሆኑት አህመድ ሀራዝ ከካፍ ሁለት የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተገኙ ሲሆን አቶ ኢሳይያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፣ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ እና የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ሞገስ ወንበሬ በጉብኝቱ ላይ በመገኘት ለግምገማ ከመጡት ጋር በመሆን ተመልክተዋል፡፡

የሀዋሳ ስታዲየም አብዛኛው የሜዳው ክፍል ቢጠናቀቅም የወንበር እና የጣራ ማልበስ ስራዎች የሚቀሩት ሲሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳበት የቆየውና አመቺ ያልነበረው የመጫወቻ ሳር ከውጪ ሀገር በመጣ ዘመናዊ ተፈጥሯዊ ሳር ለማልበስ በስራ ላይ መሆናቸውን መመልከት ተችሏል።

አቶ ኢሳይያስ ጂራ በሀዋሳ ስታዲየም እየተሰራ ባለው ስራ ደስተኛ መሆናቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ የገለፁ ሲሆን ገምጋሚዎቹ የተመለከቱትን ክፍተት በቀጣይ ስለሚገልፁ በሚገባ ተስተካክለው እንዲቀርቡ በተዋራድ ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ደመላሽ ይትባረክ (የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት) በቀጣይ በስታዲየሙ ዙሪያ የሚመጡት አስተያየቶች ተቀብሎ ለማረም እና ሜዳውን ለውድድሩ ብቁ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ ላይ በቁርጠኝነት በመስራት እንደሚዘጋጁም ጭምር ገልፀዋል፡፡ የካፍ ተወካይ የሆኑት በስታዲየሙ ስለተመለከቱት ነገር ሀሳብ ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን በቀጣይ ግን በሰነድ መልክ ለፌዴሬሽኑ እንደሚልኩ ተነግሯል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ስታዲየሞቹን እየተመለከተ ያለው ካፍ በነገው ዕለት ደግሞ የመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው የሚያመራ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *