ከፍተኛ ሊግ | አውስኮድ ሊፈርስ ይሆን?

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ ተደልድሎ እየተወዳደረ የሚገኘው አውስኮድ (አማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት) ዘንድሮ በውጤት ማጣት የምድቡ ግርጌ ላይ ሲገኝ የክለቡ የበላይ አመራሮች ክለቡን ለማፍረስ እንቅስቃሴ መጀመራቸው እየተሰማ ይገኛል።

ክለቡ በምድቡ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በ7ቱ ተሸንፎ 3 አቻ በመውጣት 1 ጨዋታ አሸንፎ የውጤት ቀውስ ውስጥ ሲገኝ በአጠቃላይ ከተጫወታቸው ጨዋታዎች 5 ግቦችን ብቻ ተጋጣሚ መረብ ላይ አስቆጥሮ 17 ተቆጥሮበት በ6 ነጥብ እና በ12 የግብ እዳ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት አዲስ አሰልጣኝ በማምጣት እና 17 አዳዲስ ተጨዋቾችን በማስፈረም የዓመቱን ስራ የጀመረው ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ ተፎካካሪ ሆኖ ለቅረብ ቢሞክርም በከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ በመገኘት የሚወዳደርበትን የመጀመሪያ ዙር ውድድሩን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ከተጠናቀቀ ጀምሮ ክለቡ ሊፈርስ እንደሚችል ሲነገር የቆየ ሲሆን ትላንት እና ከትላንት በስትያ በተሰማ ዜና የክለቡ ስራ አስኪያጅ ፋጡማ ነጋስ ክለቡ ሊፈርስ እንደሆነ የሚገልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሊልኩ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ይህን ተከትሎ የክለቡ የቀድሞ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ክለቡ እንዳይፈርስ ትላንት እና ዛሬ ጫና ለመፍጠር እንደሞከሩ የሰማን ሲሆን ከክለቡ ግን ምንም አይነት አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ነግረውናል።

በባህር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ የክለቡ ተጨዋቾች ዛሬ ወደ ክለቡ ጽህፈት ቤት አቅንተው ጥያቄ እንደጠየቁ፤ ነገር ግን ክለቡ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልሰጣቸው የገለፁልን የቡድኑ ተጨዋቾች በሁለት ሳምንት ውስጥ ደሞዛቸው ገቢ እንደሚደረግላቸው ብቻ ተነግሯቸው እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል።

ዛሬ ረፋድ ጉዳዩን አስመልክቶ ክለቡ መግለጫ እንደሚሰጥ ሲጠበቅ ቢቆይም መግለጫው ሳይሰጥ ቀርቷል። ነገር ግን ከተለያዩ ወገኖች ውሳኔው እንዲቀየር ጫናዎች መበርከታቸውን ተከትሎ ነገ አስቸኳይ ስብሰባ ተደርጎ የክለቡ ቀጣይ እጣ ፋንታ ይፋ ሊሆን እንደሚችል ተሰምቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *