ሀዋሳ ከተማ አይቮሪኮስታዊውን ተከላካይ አሰናብቷል

ሀዋሳ ከተማ ለክለቡ ብዙም ግልጋሎት መስጠት አልቻለም ያለው አይቮሪስታዊው የግራ መስመር ተከላካይ ያኦ ኦሊቨር ኩዋኩን ኮንትራት አቋርጧል፡፡

የ33 ዓመቱ ተከላካይ በአይቮሪኮስት ሊግ ለኤ ኤስ ታንዳ የተጫወተ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት ከመጣ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የሙከራ ዕድልን ለማግኘት ተቸግሮ በመቆየት የመጨረሻ ማረፊያውን በሀይቆቹ ቤት አድርጓል። በመስከረም ወር ላይ ለሀዋሳ ከተማ ለአንድ ዓመት ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው የግራ ተከላካዩ በሀዋሳ የስድስት ወራት ውል እየቀረው ክለቡ ተጫዋቹን አሰናብቶታል፡፡ በ2ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ በሜዳው ወላይታ ድቻን 2-1 በረታበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ለመጀመሪያ ጊዜ መሰለፍ የቻለ ቢሆንም በወላይታ ድቻ ተጫዋች ላይ ምራቅ በመትፋቱ ፌድሬሽኑ የአምስት ጨዋታ ቅጣት ተጥሎበት ቆይቶ ቅጣቱን ከጨረሰ ወዲህ በሦስት ጨዋታዎች ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ በመግባት ለክለቡ ያገለገለ ቢሆንም ክለቡ እና ደጋፊው በተጫዋቹ እንቅስቃሴ ደስተኛ ባለመሆናቸው ሊለቅ ችሏል፡፡

በቅርቡ በተመሳሳይ ከታዳጊ ቡድኑ ከተገኘው እና ቀሪ የሁለት ዓመት ውል ከነበረው ፀጋዓብ ዮሴፍ ጋር የተለያየው ሀዋሳ አምና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዕድል ተሰጥቶት ዘንድሮ በአንደኛው ዙር ተሴራ ያልነበረው ወጣቱ ተከላካይ ጌትነት ቶማስ የኦሊቨርን ቦታ ሲሸፍን ዳግም በሁለተኛው ዙር የምንመለከተው ሲሆን በእስራኤል እሸቱ እና ገብረመስቀል ዱባለ የሚመራው የአጥቂ ቦታን ለማጠናከር ደግሞ አንድ የውጪ ተጫዋች ከቀናት በኃላ ለማስፈረም በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *