ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አዳማ እና ንግድ ባንክ ከሜዳቸው ውጪ ሲያሸንፉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የ15ኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተካሂደዋል። መሪው ንግድ ባንክ እና ተከታዩ አዳማ ከሜዳቸው ውጪ ሲያሸንፉ ቅዱስ ጊዮርጊስም በሰፊ ልዩነት ድል አስመዝግቧል።

08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 3-0 አሸንፈዋል። አምበሏ ሶፋኒት ተፈራ ባስቆጠረችው ጎል ቅዱስ ጊዮርጊሶች 1-0 በመምራት ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ በሁለተኛው አጋማሽ ብርሀን ኃይለሥላሴ ከቅጣት ምት እና ከክፍት ጨዋታ አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ጎሎች 3-0 ተጠናቋል። ባሳለፍነው ሳምንት በንግድ ባንክ 7-0 የተሸነፉት እንስቶቹ ፈረሰኞች ከከባዱ ሽንፈት ያገገሙበትን ድል ማስመዝገባቸውን ተከትሎ በ10 ነጥቦች ግርጌውን ለጥሩነሽ ዲባባ አስረክበው አንድ ደረጃ ማሻሻል ችለዋል።

10:00 በቀጠለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ አዳማ ከተማ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ባለሜዳው ኤሌክትሪክን 4-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ሎዛ አበራ በአዲሱ ቡድኗ መለያ ጎልታ ባለችበት በዚህ ጨዋታ እንግዶቹ አዳማዎች በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ በሴናፍ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም ግብጠባቂዋ እስራኤል ከተማ አውጥታባታለች። ከሲዳማ ቡና አዳማ ከነማን ዘንድሮ በመቀላቀል መጀመርያ አሰላለፍ መግባት ከጀመረች ጊዜ አንስቶ በአዳማ የግራ መስመር ላይ በመከላከል ሆነ በማጥቃት ሽግግር ውስጥ ልዩነት እየፈጠረች ያለችው የግራ ተከላካይዋ ነፃነት ፀጋዬ ቆርጣ በመግባት ተከላካላካዮችን በማለፍ ያሻገረችውን ሎዛ አበራ በግንባራ ገጭታ መትታ ግብጠባቂዋ እስራኤል የያዘችው ኳስ አዳማዎች ብልጫ ወስደው ለመጫወታቸው ማሳያ ነው።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት እና በይበልጥ የሜዳውን ሁለቱን መስመሮች ለመጠቀም ቢጥሩም ወርቅነሽ መልመላ ፍጥነቷን ተጠቅማ የፈጠረችው የግብ አጋጣሚ እንዲሁም 23ኛው ደቂቃ መሳይ ከቅጣት ምት የሞከረችው ኳስ ካልሆነ በቀር ሌላ የግብ እድል መመልከት አልቻልንም።

የአዳማ የበላይነት ይበልጡኑ ጎልቶ መታየት የጀመረው በ26ኛው እፀገነት ብዙነህ ከግራ መስመር ያሻገረችውን በቅርቡ አዳምን የተቀላቀለችው ሎዛ አበራ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎሏን በግንባሯ ገጭታ ካስቆጠረች በኋላ ነበር። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የቆዩት አዳማዎች 40ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል በመድረስ ሎዛ አበራ አመቻችታ የሰጠቻትን ከጎል ርቃ የቆየችው የዓምና የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሰናይት ቦጋለ ከሳጥን ውጭ ጥሩ ጎል አስቆጥራ የአዳማን ጎል ሁለት ማድረስ ችላለች። እረፍት መውጫ መዳረሻ ላይ እፀገነት ብዙነህ ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል እድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት በግቡ ቋሚ ታኮ ሊወጣባት ችሏል።

ከእረፍት መልስ ገና በ47ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ከግብ ጠባቂዋ እስራኤል ጋር ተገናኝታ ኳሱ ከፍ ብሎ በመርዘሙ የወጣባት ጠንካራ የግብ ዕድል ነበር። የጨዋታው ሚዛን ሙሉ ለሙሉ ወደ አዳማ ባጋደለበት በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 52ኛው ደቂቃ ሴናፍ ከቀኝ መስመር ይዛ በመግባት ያሻገረችውን ሎዛ አበራ ሁለተኛ ጎሏን ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል በግንባሯ በመምታት አስቆጥራለች።

በዛሬው ጨዋታ ጎል አታስቆጥር እንጂ ጥሩ በመንቀሳቀስ ለጎሎች መቆጠር ትልቁን አስተዋፆኦ ያደረገችው ሴናፍ ዋቁማ 56ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሌላ የጎል እድል ለሎዛ አበራ አመቻችታ በመስጠት ሎዛ አበራ ሦስታ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል አስቆጥራለች። ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ሜዳ የተመለሰችው ሎዛ አበራ በዛሬ አቋሟ በቀሩት የሊጉ ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠሯን የምትቀጥል ከሆነ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆና ለመጨረስ ሰፊ እድል ያላት ይመስላል።

በተወሰደባቸው ብልጫ መረጋጋት ያቃታቸው ኢትዮ ኤሌትሪኮች በቆሙ ኳሶች እና በግል ጥረቷ መሳይ ተመስገን ከምታደርገው ጥረት በቀር ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን የጎል እድሎች መፍጠር ተስኗቸው ውሏል። ኳስን ተቆጣጥሮ ከመጫወት ባለፈ እንምብዛም ወደ ፊት መሄድ አቁመው የነበሩት አዳማዎች ከ72ኛው ደቂቃ በኃላ ሎዛ አበራ ከሳጥን ውጭ በጠንካራ ምቷ ወደ ጎል የላከችውን ግብጠባቂዋ በሚገርም ብቃት ወደ ውጭ ካወጣችባት በኋላ ሴናፍ ሦስት ጎል መሆን የሚችሉ እድሎችን አምክናለች።

በመጨረሻም ሌሎች በርከት ያሉ ጎል መሆን የሚችሉ ኳሶችን ሎዛ ተቀይረው የገቡት ሳራ ነብሶ፣ ሰርካዲስ ጉታ እና ጤናዬ ወመሴ ሳይጠቀሙ ቀርተው ጨዋታው በአዳማ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወደ ድሬዳዋ ያመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 በማሸነፍ መሪነቱን አስቀጥሏል። ብዙነሽ ሲሳይ በመጀመርያው አጋማሽ የንግድ ባንክን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረች ተጫዋች ናት።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *