ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | ሀዋሳ ከተማ እና ጥረት ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 15ኛ ሳምንት ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ በክልል እና በአዲስ አበባ ተካሂደዋል።

08:00 በአዲስ አበባ ስቴዲየም በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በእንግዶቹ ሀዋሳዎች 5 – 2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ለማሸነፍ በከፍተኛ ፍላጎት ወደ ሜዳ እንደገቡ በጥሩ እንቅስቃሴ ጨዋታውን ተቆጣጥረው መጫወት የጀመሩት አዲስ አበባዎች በ4ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት አስካለ ገብረፃድቅ የመታችውን የሀዋሳዋ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ ኳሱን አርቃለው ብላ በራሷ ላይ ጎል አስቆጥራ መምራት ችለው ነበር። ሆኖም ከጎሉ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባዎች በክፍት ሜዳ የጎል ዕድል ከመፍጠር ይልቅ በረጃጅም እና ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ብዙም ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ለተደጋጋሚ ጫና እራሳቸውን እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል።

እንግዶቹ ሀዋሳዎች የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ወደ መረጋጋት ገብተው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ጀምረዋል። 19ኛው ደቂቃ አጥቂዋ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ተከላካይ በማለፍ ያሻገረችውን ኳስ ነፃነት መና በግንባሯ ገጭታ ወደ ውጭ የወጣበት የመጀመርያ ሙከራቸው ሲሆን በ23ኛው ደቂቃ ምርቃት ፈለቀ ከቅጣት ምት ግሩም ጎል አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል።

ሀዋሳዎች ተጨማሪ ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ ነፃነት መና ሌላ የግብ መሆን የሚችል ዕድል ከማምከኗ በላይ 36ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን ከግራ መስመር ተጫዋቾችን በማለፍ ከርሷ ይልቅ ለጎሉ የተሻለ አቋቋም ለሚገኙት አጥቂዎች ማቀበል ስትችል ራሷ በመጠቀም ወደ ውጭ የወጣው እንዲሁም 45ኛው ደቂቃ በማይታመን መልኩ እራሷ መሳይ ጎል መሆን የሚችል ሳትጠቀም የቀረችው የሚያስቆጭ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት የሚችሉት ቅድስት ቦጋለ እና ህይወት ረጉን በመቀየር የገቡ ሲሆን በ48ኛው ደቂቃ ሜላት ደመቀ ለጎሉ ሁለት ሜትር በሚርቅ ቦታ ላይ የሳተችው ጨዋታውን ለመቀየር የነበራቸውን እድል አሳጥቷል። የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሀዋሳዎች በአንፃሩ በአጥቂዎቻቸው መሳይ በምርቃት አማካኝነት ጎሎችን ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ሰምሮላቸው 70ኛ ምርቃት ፈለቀ የግል ብቃቷን ተጠቅማ ተከላካዮችን በማለፍ የግቡን አግዳዊ ነክቶ ግሩም ሁለተኛ ጎል ለሀዋሳ አስቆጥራለች።

ከአምስት ደቂቃ በኃላ ከሀዋሳ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ ከተከላካዮች ጀርባ በፍጥነት በመውጣት በተደጋጋሚ ጎል ለማግባት ያገኘችውን አጋጣሚ ሳትጠቀም የቀረችው መሳይ ተመስገን የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎሏን አስቆጥራ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርገዋለች። ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን መጠቀም ያልቻሉት ሀዋሳዎች 81ኛው ደቂቃ በነፃነት መና አማካኝነት ጎል አስቆጥረው የጎል መጠናቸውን ወደ አራት ከፍ አድርገዋል።

የተወሰደባቸውን ብልጫ እንዲሁም የጨዋታውን ውጤት መቀየር ባይችልም 84ኛው ከደደቢት ጋር በተከታታይ ሦስት ዋንጫ በአምበልነት አጣጥማ ዘንድሮ አዲስ አበባን የተቀላቀለችው ኤደን ሽፈራው ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሯ በመግጨት ለአዲስ አበባ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችላለች። በመጨረሻም ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ 89ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው የቀኝ መስመር ተከላካይዋ ፍሬህይወት በድሉ አምስተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በእንግዶቹ ሀዋሳዎች 5-2 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

በክልል ስታድየሞች በተደረጉ ጨዋታዎች ዲላ ላይ ጌዴኦ ዲላን የገጠመው ጥረት ኮርፖሬት 2-1 አሸንፏል። ትመር ጠንክር እና ምስር ኢብራሂም ለጥረት ሲያስቆጥሩ መሠረት ወርቅነህ ለጌዴኦ ዲላ አስቆጥረዋል። አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ ሔለን ሰይፉ ለመከላከያ፤ መሠረት ማቲዎስ ለአርባምንጭ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *