ደደቢት አምስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በርካታ ተጫዋቾች ያሰናበተው ደደቢት ምትክ ፍለጋ በሰፊው ወደ ገበያ በመውጣት አምስት ተጫዋቾች አስፈርሟል። መድሃኔ ታደሰ፣ ኃይሉ ገብረየሱስ፣ ሙሴ ዮሐንስ፣ ቢንያም ደበሳይ እና ኪሩቤል ኃይሉ የሰማያዊዎቹ አዲስ ፈራሚዎች ናቸው።

ላለፉት ስድስት ወራት ክለብ አልባ የነበረው አንጋፋው መድሀኔ ታደሰ ወደ ደደቢት ካመሩት ተጫዋቾች አንዱ ነው። በ1990ዎቹ አጋማሽ የእግርኳስ ህይወቱን በትራንስ ኢትዮጵያ የጀመረው መድሀኔ በ1997 የፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በ19 ጎሎች ሲያጠናቅቅ በ2003 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ደግሞ የሊግ ዋንጫን ማሳካት ችሏል። ከአራቱ ክለቦች በተጨማሪ ለዳሽን ቢራ እና ሀዋሳ ከተማ የተጫወተው መድሀኔ በውድድር ዓመቱ 3 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረው የደደቢት የአጥቂ ክፍልን በመቐለ አብሮት ከተጫወተው ፉሴይኒ ኑሁ በጋራ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ደደቢትን የተቀላቀለው ተጫዋች ኃይሉ ገብረየሱስ ነው። አብዛኛው የእግር ኳስ ህይወቱን በመቐለ 70 እንደርታ ያሳለፈው ተከላካዩ በዚህ ዓመት መጀመርያ ለበርካታ ዓመታት በአምበልነት ከመራበት ክለብ በመልቀቅ ወደ ከፍተኛ ሊጉ አክሱም ከተማ ቢያመራም ከወራት ቆይታ በኃላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሷል። ኃይሉ ጋናዊው ክዌክ አንዶህን ለመቐለ አሳልፈው ለሰጡት ደደቢቶች ጥሩ ተተኪ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ሶስተኛ የደደቢት ፈራሚ የሆነው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ቢንያም ደበሳይ ነው። ትራንስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለመቐለ 70 እንደርታ፣ አክሱም ከተማ፣ ወልዋሎ ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ገላን ከተማ የተጫወተው ይህ ተጫዋች ባሳለፍነው ክረምት ከመቐለ 70 እንደርታ ያልተሳካ የሙከራ ግዜ አሳልፎ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ክለብ ገላን ከተማ ቢያመራም ከበርካታ ዓመታት ቆይታ በኃላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመልሰው ዝውውር አድርጓል።

አራተኛው የደደቢት ፈራሚ ግብ ጠባቂው ሙሴ ዮሃንስ ነው። ባሳለፍነው ዓመት ስሑል ሽረ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ይህ የቀድሞ የመቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ስሑል ሽረ አንጋፋ ተጫዋች በመጀመርያ ዙር በወጣ ገባ ብቃት የደደቢትን ግብ ለጠበቀው ጋናዊው ዓብዱልረሺድ ማታውኪል ጥሩ ተፎፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሙሴ እና ቢኒያም

አምስተኛው የደደቢት ፈራሚ ወጣቱ ተከላካይ ኪሩቤል ኃይሉ ሲሆን እሱም እንደ ሦስቱ አዳዲስ ፈራሚዎች ሁሉ ከከፍተኛ ሊጉ የፈረመ ተጫዋች ነው። ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተመርቆ ከወጣ በኃላ ለደሴ ከተማ የተጫወተው ይህ ተከላካይ በርካታ ተጫዋች ላሰናበቱት ሰማያዊዋቹ ስምንተኛ ፈራሚ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *