የኮከቦች የገንዘብ ሽልማት እስካሁን አለመፈፀሙ ቅሬታ እያስነሳ ነው

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2010 የውድድር ዘመን የኮከቦችን የገንዘብ ክፍያ በአምስት ወራት ውስጥ ከፍሎ አለመጠናቀቁ በተሸላሚዎች ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ ነው።

የ2010 የውድድር ዓመት ሊጎቹ ኮከብ አሰልጣኝ ፣ ተጫዋቾች ፣ ጎል አስቆጣሪዎች እና የምስጉን ዳኞች ሽልማት መርሀ ግብርን ኅዳር 6 ቀን 2011 ላይ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል። ሆኖም በወቅቱ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ለተሸላሚዎች እንደሚሰጥ የተገለፀው ገንዘብ ከአምስት ወራት ቢያስቆጥርም ፌዴሬሽኑ እስካሁን ገቢ ሊያደርግ አልቻለም።

ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ኮከብ ተሸላሚዎች ለሶከር ኢትዮዽያ እንደተናገሩት “እስካሁን የሽልማታቸው ገንዘቡ ዛሬ ነገ ይሰጣችኋል እየተባለ አምስት ወር ሆኖታል። ይህ በጣም ያሳዝናል ከ2011 የውድድር ዘመን ኮከቦች ጋር አብረው ሊሸልሙን ነው ወይ?” በማለት ቅሬታቸውን እየገለፁ ፌዴሬሽኑ ሽልማታቸውን እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ባለፈው ዓመት በተለየ መልኩ በአንድ መድረክ ላይ መከናወን የጀመረው ኮከቦች ሽልማት ዓምናም በተመሳሳይ የሽልማት ገንዘቡ ሊከፈለን አልቻለም በማለት ተሸላሚዎች ቅሬታቸውን አሰምተው ከወራት መዘግየት በኋላ ፌዴሬሽኑ ክፍያውን የፈፀመ ሲሆን ዘንድሮም ክፍያውን በፍጥነት አለመፈፀሙ አስገራሚ ሆኗል።

ሶከር ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙርያ የፌዴሬሽኑ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አቶ ነቢዩን ጠይቃ ባገኘችው ምላሽ በቀጣዩ ሳምንት የገንዘብ ሽልማቱ ለተሸላሚዎች መድረስ ይጀምራል ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *