ምንይሉ ወንድሙ ስለ እግርኳስ ህይወቱ እና የዘንድሮ አቋሙ ይናገራል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት በቻለባቸው ያለፉት ዓመታት እንደ ዘንድሮ በርከት ያሉ ጎሎችን አስቆጥሮ አያውቅም። በአንድ ክለብ ብቻ የቆየው የእግርኳስ ህይወቱ ከመከላከያ ተስፋ ቡድን በመነሳት በአሁኑ ወቅት በዋናው ቡድን እያገለገለ ይገኛል። በጉዳት ምክንያት ፈታኝ የሆኑ ጊዜያትን በማሳለፍ ከሜዳም ዕርቆ ቆይቶ ያውቃል። ከዓመት ዓመት የእግርኳስ እድገቱ እየተሻሻለ የሚገኘው እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ አጥቂ እየሆነ የመጣው ምንይሉ ወንድሙ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ሰፊ ቆይታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ እንዲህ አቅርበነዋል።

ትውልድ እና እድገትህ የት ነው?

ተወልጄ ያደኩት ጅማ ከተማ ሠራተኛ ሰፈር በሚባል መንደር ውስጥ ነው። እግርኳስን መጫወት የጀመርኩበት በሰፈሬ የበሚገኘው አባቡና በሚባል ሜዳ ነው።

ለወላጆችህ ስንተኛ ልጅ ነህ ከቤተሰቦችህ መካከል እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ አለ ?

ለእናቴ የመጀመርያ ልጅ ነኝ፤ አንድ ታናሽ ወንድም አለኝ። ያደግኩት አያቴ ጋር በመሆኑ እንደ ወንድም እህት የማያቸው አጎቶች እና አክስቶች አሉኝ። ከቤተሰቦቼ መካከል ኳስ ተጫውቶ ያለፈ አይደለም የኳስ ፍላጎት ያለው እንኳን ቤተሰብ የለኝም። አሁን እንኳን እኔ ያለሁበትን ደረጃ አይተው እንኳ የእግርኳስ አድናቂ አይደሉም። አሁን ነው ታናሽ ወንድሜ እኔን አርአያ አድርጎ መጫወት የጀመረው እንጂ ብዙም የእግርኳስ ስሜቱ የላቸውም። ታናሽ ወድሜ ዳንኤል ይባላል፤ ገና 15 ዓመቱ ነው የ። ጅማ የሚገኝ ፕሮጀክት ውስጥ እየሰራ ይገኛል።

ቤተሰብህ የእግርኳስ ስሜት ከሌላቸው አንተ በምን መነሻነት ነው እግርኳሰኛ የሆንከው?

ከልጅነቴ ጀምሮ የሰፈር ውድድር ውስጥ እጫወት ነበር። አንድ ሰው በግሉ በመነሳት በየዓመቱ የታዳጊ ውድድሮችን ያዘጋጅ ነበር። በዚህ ውድድር ላይ በጣም ጥሩ ነገር አሳይ ስለነበረ አንዳንድ ሰዎች ይህ ልጅ ወደፊት ትልቅ ደረጃ ይደርሳል እያሉ ያወሩ ነበር። ከዚህም ባሻገር ስጫወት ያዩኝ ሁሉ እኔን ለማበረታታት ብዙ ሽልማቶችን ይሸልሙኝ ነበር። ይህ ነው እኔን ወደ ፕሮጀክት እንድገባ እና አሁን ላለሁበት ደረጃ መነሻ የሆነኝ።

ከፕሮጀክት ስለነበረህ ቆይታ ግለፅልኝ። ቀጣይ የእግርኳስ ህይወትህ ወዴት አመራ?

አብርሃም የሚባል አሰልጣኝ አለ። መጀመርያ ዳኛ ነበር፤ በኋላ አሰልጣኝ ሲሆን እርሱ ጋር ገብተን እንድንሰራ አደረገኝ። በመቀጠል ከ13 ዓመት በታች ፕሮጀክት ሄድኩኝ። እዛም እየሰራው ብዙ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ዕድሉን ለማግኘት ብሞክርም አቅም የለህም እየተባልኩ እቀነስ ነበር። ሰውነቴ በጣም ደቃቃ ስለነበረ ይቀንሱኛል። በዚህ በጣም እበሳጭ ነበር። በቃ አቅም እያለኝ እየቻልኩ የማያጫውቱኝ ከሆነ ከዚህ በኋላ ኳስ አልጫወትም ብዬ ለመወሰን የተገደድኩበት ጊዜ ነበር። ሆኖም እንደ አጋጣሚ ቦንጋ ከተማ ለአንድ ውድድር ተጠርቼ በመሄድ እዛ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ በመቻሌ በዚህ መነሻነት ለቦንጋ ምርጥ ተመርጬ ሆሳዕና ከተማ ለሚካሄድ ውድድር በመሄድ ጥሩ ነገር አሳይቼ መመለስ ቻልኩ። በመቀጠል ጅማ የትምህርት ቤትን በመወከል አዳማ ከተማ ላይ ለሚካሄድ የትምህርት ቤቶች ውድድር አመራው። እዛም ጥሩ ነገር አድርጌ ተመለስኩ። በመጨረሻም አሁን ላለው የእግርኳስ ህይወቴ መነሻ የሆነ ዕድል ተፈጠረልኝ። ሻሸመኔ ከተማ ለሚካሄደው የኦሮሚያ ቡድን ተመርጬ 2005 ወደ ሻሸመኔ ሄድኩኝ። የሚገርምህ ወደ ሻሸመኔ ከመሄዴ በፊት በኦሮሚያ የክለቦች ሻምፒዮና ወደ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት የሚካሄድ የ15 ቀን ውድድር ላይ ለነቀምት ተጫወትኩ። ማንም ስለማያቅ በወቅቱ (እየሳቀ)… ለደቡቦቹ ክለቦች ከፋ ቡና እና ለሃዲያ ሊሞ መጫወት ችያለው።

በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስት ክለቦች መጫወት እንዴት ነው ትንሽ ግራ ያጋባል። አብራራልኝ…

አዎ ፊርማ የለውም፤ ደሞዝም የለም። ውድድሩ ለ15 ቀን የሚካሄድ ስለሆነ አበል ብቻ ነው የሚሰጥህ። ውድድሩ ታች የሚደረግ ስለሆነ ብዙ ቁጥጥርም ስሌለ ማንም አያውቅም። በዛ ምክንያት ያው እየቀያየርክ ትጫወታለህ። እኔ ደግሞ የማስበው የተሻለ ደረጃ ለመድረስ አቅሜን የማሳይበትን አጋጣሚ ማግኘት ስለሆነ እየዞርኩ ለጠሩኝ ክለቦች ሁሉ እጫወት ነበር። አንዱ ስጫወት ያየኝ ይጠራኛል። ቡድኑ ሲወድቅ ሌላኛው ይጠራኛል። እንደዛ እያደረኩ ነበር የምጫወተው። የሚገርምህ ሀዲያ ሆሳዕና ለመጫወት ተስማምቼ ቤተሰቦቼን ለማግኘት ሄጄ እመለሳለሁ ብያቸው ነው ለኦሮሚያ ምርጥ ተመርጬ ወደ ሻሸመኔ የሄድኩት እንጂ ሀድያ ሆሳዕና ፈርሜ የምጫወትበት የመጀመርያው ክለቤ ይሆን ነበር።

የሻሸመኔው ውድድር የምንይሉን የወደ ፊት የእግርኳስ ህይወት የወሰነ ውድድር ነበር። እስቲ የሻሸመኔው ውድድር እንዴት ነበር ?

የአሁን የጅማ አባ ቡና ምክትል አሰልጣኝ (ለማ ይባላል) እሱ ነው ኦሮሚያን ወክዬ እንድጫወት የላከኝ። እዛም በነበረው ውድድር ላይ ጥሩ ነገር ማሳየት ቻልኩ። በውድድሩም አጠቃላይ አራት ጎል አስቆጠርኩኝ። እስከ መጨረሻው የዋንጫ ጨዋታ ደርስ ደርሰን የነበረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ተሸንፈን ነው ዋንጫ ያጣነው። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች በመሆን መልካም እንቅስቃሴ በማድረጌ የብዙ ክለቦች እይታ ውስጥ መግባት ቻልኩ። በዚህ የሻሸመኔ ውድድር ላይ በየክልላቸው ጥሩ የሚጫወቱ እንደ ቢንያም በላይ፣ ዳዊት ተፈራ እና አህመድ ረሺድ የመሳሰሉ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ነበሩ። የሚገርምህ በዚህ ሁሉ ውድድር ውስጥ የተጫወትኩት በአንድ ዓመት ውስጥ 2005 ላይ ነበር።

ባደረግኩት ጥሩ እንቅስቃሴ የብዙ ክለቦች ዓይን ውስጥ ገባሁ ብለኸኛል። ከዛ በመቀጠል ወዴት ነው ያመራኸው?

ወደ ቤተሰቦቼ ጅማ ሄድኩ። እዛ እያለው የአሁኑ የፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ (ለእኔ እንደ አባቴ ነው የማየው።) ሻሸመኔ በነበረው ውድድር ላይ የኦሮሚያ ቡድን መሪ ነበር። በኋላ ነው የሰበታ ከተማ ስራ አስኪያጅ የሆነው። አቶ ኢሳይያስ ለሰበታ ከተማ መጫወት አለብህ ብሎኝ እሺ ብዬ ለሰበታ ለመጫወት ውል ላይ በሁለት ሺህ ብር ደሞዝ ተስማምቼ ፈርሜ ፎቶ አምጣ ሲሉኝ ወደ ቤተሰብ ሄጄ ላማክር ብዬ አዲስ አበባ ወደ ወዳለችው እህቴ ጋር መጣሁ። ከእርሷ ጋር እየተማከርኩኝ ባለበት ሰዓት አቶ ኢሳይያስ ደውሎ እኔ ሰበታን ልለቅ ስለሆነ ለመከላከያ ፈርም ብሎኝ 2006 የመጀመርያ ክለቤ ሆኖ ለመከላከያ መጫወት ጀመርኩ።

አጋጣሚው ይገርማል። በአንድ ዓመት ውስጥ ያለ ፊርማ ለኦሮሚያ ምርጥ፣ ለነቀምት ከተማ ፣ ለቦንጋ ፣ ለከፋ ቡና ፣ ለሀዲያ ሊሞ ተጫውተህ መጨረሻህ ለመከላከያ ተስፋ ሆነ። የመከላከያ ተስፋ ቡድን ውስጥም ብዙ የቆየህ አይመስለኝም…

አዎ ለእኔም ይገርመኛል። ቅድም እንዳልኩህ ለመጫወት ካለኝ ፈላጎት የመነጨ ነው። በመከላከያ የተስፋ ቡድን ውስጥ እኔ እንደገባው አሁን በክለባቸው ጥሩ የሚንቀሳቀሱ እነ አሜ መሐመድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ (መከላከያ)፣ ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና) እና ሌሎች ተጫዋቾች ነበሩበት። በተስፋ ቡድን ውስጥ ሦስት ጨዋታ ብቻ ተጫውቼ ሦስት ጎል አስቆጠርኩኝ። ከዛ በኋላ ነው አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ወዲያውኑ ግማሽ ዓመት ላይ ወደ ዋናው ቡድን አድጌ እንድጫወት ያደረገኝ። የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዬ ከሙገር ጋር ነበር ያደረግኩት። በመቀጠል የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ውድድር ላይ ወደ ሱዳን ይዞኝ ሄዶ ከጅቡቲ ክለብ ጋር በነበረ ጨዋታ 75ኛው ደቂቃ ተቀይሬ ገብቼ 2-1 ስናሸንፍ የማሸነፊያዋን አንድ ጎል አስቆጥሬ ወጣሁ። ይህም በመከላከያ ማሊያ የመጀመርያ ጎሌ ነው። በዋናው ቡድን በ2006 በቀሩት 13 ጨዋታዎች በመጫወት ሦስት ጎሎች አስቆጥሬ የውድድር ዓመቱን ጨርሻለሁ።

እድገትህ ፈጣን ነው በግማሽ ዓመት የተስፋ ቡድን ቆይታ ነው ወደ ዋናው ቡድን አድገህ መጫወት የቻልከው። ከ2007 ጀምሮ በመከላከያ የነበረህ ቆይታ እንዴት ነው?

አዲስ ፈራሚዎች ወደ ቡድኑ የመጡ ቢሆንም አሰልጣኝ ገብረመድኅን በእኔ እምነት ስለነበረው በቀጥተኛ አጥቂም፣ በመስመር አጥቂ በማድረግ በመጀመርያ አስላለፍ ውስጥ ያስገባኝ ነበር። ጥሩ የውድድር ዓመት ነው ያሳለፍኩት። ባልሳሳት በዓመት ውስጥ ሰባት ጎል አስቆጥሬ ጨርሻለው። በ2008 ደግሞ ጉዳት ቢያጋጥመኝም 6 ጎሎችን አስቆጥሬ ዓመቱን ውድድር መጨረስ ችያለው ።

ጉዳትህን ካነሳኸው አይቀር በጣም ከባድ ጊዜ አሳልፍሃል። ባጋጠመህ ከባድ የጉልበት ጉዳት ምክንያት ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እርቀሀል? እስቲ ያንን አስቸጋሪ ጊዜ እንዴት አሳለፍከው?

አዲስ አበባ ስታዲየም የኮፌዴሬሽን ካፕ ከግብፁ ምስር ኤል ማቃሳ ጋር እየተጫወትኩ ነው የጅማት መበጠስ ጉዳት ያጋጠመኝ። ከዚህ በኋላ ለዘጠኝ ወራት ከሜዳ ርቄ ቆይቻለው። በጣም ፈታኝ እና አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ያም ቢሆን ብቻዬን አልነበርኩም፤ እንደ ቤተሰብ ሆኖ ያሳከመኝ ያሳደገኝ ክለቤ መከላከያ ከጎኔ ነበር። ከኢትዮጵያ ውጭም ወጥቼ አልታከምኩም፤ እዚሁ ሀገር ውስጥ በዮርዳኖስ ሆስፒታል ነው የቀዶ ጥገና ያደረግኩት። የክለቤ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በተፈጥሮም ቢሆን አዕምሮዬ ጠንካራ በመሆኑ ለጉዳቱ እጄን አልሰጠሁም። ሁሌም ቢሆን ለማንኛውም ለምንም ነገር እጅ አልሰጥም። ወደ ሜዳ ለመመለስ ከነበረኝ ፍላጎት የተነሳ ተው አታድርግ የምባለው ነገር ሁሉ አደርግ ነበር። ፈጣሪም ረድቶኝ ክለቤ ባደረገልኝ ከፍተኛ ጥረት ከዘጠኝ ወር የጉዳት ቆይታ በኋላ በ2009 ወደ ሜዳ መመለስ ችያለው።

ከዛ አስቸጋሪ የጉዳት ቆይታ በኋላ በፍጥነት ወደ አቋምህ መመለስህ አስገራሚ ነው። ከጉዳት ከተመለስክ በኋላ የነበረህ ጊዜን አጫውተኝ ?

2009 አንደኛው ዙር ላይ ነው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ መጫወት የጀመርኩት። በወቅቱ ቡድናችን አደጋ ውስጥ ሆኖ በተከታታይ ጨዋታዎችን ይሸነፍ ነበር። እኔ ቡድኔን ለማገልገል ካለኝ ፍላጎት የተነሳ እረፍት አድርግ ይቅርብህ አትጫወት እየተባልኩ እንኳ ማንንም ሳልሰማ ነበር ወደ ሜዳ የገባሁት። በብዙ ችግር ውስጥ አብሮኝ የነበረ ክለብ እርሱ ሲቸገር እኔ አሞኛል ብዬ መቀመጥ አልቻልኩም። ተነስቼ ገብቻለው። ዘንድሮ ብዙ ክለቦች ከፍተኛ ብር አቅረበውልኝ እንድጫወትላቸው ጠይቀውኝ ያልተቀበልኩት የኋላውን ስለማስብ ነው። አሞኝ በተጎዳሁበት ወቅት ታግሶ ገንዘብ እያወጣ ያሳከመኝን ክለብ ዛሬ ጥሩ ሆኜ ማገልገል በሚገባኝ ጊዜ ገንዘብን አስቤ ብለቅ ለእኔም ጡር ነው የሚሆንብኝ። አዕምሮዬም አይቀበለውም። ክለቡ የገንዘብ አቅሜ ይህ ነው ሲለኝ ገፍቼ መሄድ ያልፈለኩት የክለቤን ውለታ ስለማስብ ነው። ከቡና ጋር ወደ ነበረው ጨዋታ ልመልስህ እስከ 88ኛው ደቂቃ ተጫወትኩ፤ ጎል ባላስቆጥርም 2 – 2 በአቻ ውጤት አጠናቀቅን። በሳምንቱ ግን በአዲስ አበባ ስቴየታዲየም ከወልዲያ ጋር ስንጫወት ወደ ጎል ማስቆጠር ተመልሻለው። በቀረው ጨዋታዎች ጉዳቴ ብዙም አስተማማኝ ስላልነበር እያረፍኩ እየተጫወትኩ በአጠቃላይ 6 ጎሎች በማስቆጠር የውድድር ዓመቱን መጨረስ ችያለው።

በየ ዓመቱ ጎሎችን ታስቆጥራለህ ሆኖም ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጥሪ ካልሆነ በቀር ብዙም በመጀመርያ አስላለፍ አልያም በተጠባባቂ ወንበር ላይ ስትቀመጥ አልተመለከትኩም። አሁን በቅርብ ነው በጋና ጨዋታ በብሔራዊ ቡድኑ በመጀመርያ ተሰላፊ መሆን የቻልከው። ከዚህ ቀደም ከመጠራት በዘለለ ለመጫወት እድል ያላገኘህበት ምክንያት ምንድነው ትላለህ?

የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በክለብ ጨዋታ ይመለከቱህና ለብሔራዊ ቡድን ይጠሩሀል። ሆኖም የመጫወት እድል ሳይሰጡሁ ይቀንሱሀል። እኔ ብዙ ጊዜ ተጠርቻለው፤ በልምምድ ብቻ እያዩ ይቀንሳሉ። አንድን ተጫዋች ደግሞ በልምምድ ብቻ አትለካውም። ልምምድ ላይ ጥሩ ሆኖ ጨዋታ ላይ የሚወርድ ይኖራል። እኔ ደግሞ በአብዛኛው የልምምድ ሳይሆን የጨዋታ ሰው ነኝ። በልምምድ ላይ እንዳንዴ መጨናነቅ ስለማልወድ ልምምድ ላይ ቸልተኛ ነኝ። ይህ ደግሞ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በጣም ጎድቶኛል። በብሔራዊ ቡድን መጫወት ባለብኝ እና አቅሜን ማሳየት በሚገባኝ ሰዓት እንዳልጫወት ያደረገኝ ልምምድ ላይ ያለኝ ቸልተኛ በመሆኔ ነው። አሁን ግን የመጫወት ልምድ እያገኘሁ ስሄድ አዕምሮዬም እየበሰለ ሲመጣ ልምምድ ላይ ጠንክሬ ነው እየሰራው ያለሁት። በብሔራዊ ቡድንም የመጀመርያ ተሰላፊ ወደ መሆን መጥቻለው። ከዚህ በኋላ ቦታዬን ለማስከበር ጠንክሬ እሰራለው።

ምንይሉ ከመቼውም ዓመታት ዘንድሮ የተሻለ እየሆነ መጥቷል። ሊጉንም ከአማኑኤል ጋር በተመሳሳይ በ11 ጎል በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል። የዘንድሮ ወቅታዊ አቋምህን እንዴት አየኸው?

አዎ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። ከዚህ ቀደም ከጉዳት ጋር እየታገልኩ ነበር የምጫወተው። አሁን ጥሩ አቋም ላይ ነው የምገኘው፤ ከጉዳትም ነፃ ነኝ። ሜዳ ውስጥ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሁሉ አድርጌ እወጣለው። ጎል ከማስቆጠር ባሻገር ቡድኔ አሸናፊ እንዲሆን የምችለውን ነገር ለማድረግ እየሰራሁ ነው።

በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትም እየተፎካከርክ ነው…

ጎል ማስቆጠር ስራዬ ነው። ክለቡ አጥቂ አድርጎ ኃላፊነት የሰጠኝ ጎል እንዳስቆጥር ነው። ዋና አላማዬ ቡድኔን ማገልገል ነው። ለዚህም በተከታታይ ጎሎችን ማስቆጠር አለብኝ። አንዳንድ የአጨራረስ ክፍተቶች አሉብኝ። በቀጣይ ከአንደኛው ዙር በተሻለ ቡድኔን ለማገልገል ጎሎችን ለማስቆጠር ጠንክሬ እሰራለው።

በጨዋታ ጎል ከማስቆጠርህ ባሻገር የፍፁም ቅጣት ምት እና የቆሙ ኳሶች አጠቃቀምህ ጥሩ ነው። ይህ ከምን መጣ ?

አዎ የክለቤ የመጀመርያ ፍፁም ቅጣት ምት መቺ ነኝ። ይህ ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ ያዳበርኩት ነው። ፍፁም ቅጣት ምት በራስ መተማመን ይጠይቃል። ምንም የማይፈራ ተጫዋች መሆን ይገባሀል። ከልጅነቴ ጀምሮ ፍፁም ቅጣት ምት ስመታ ነው ያደኩት። እስካሁን ድረስ ተመልሶብኝ አያቅም። ቅጣት ምት ደግሞ ጉልበት ይጠይቃል፤ እሱንም በልምምድ ያመጣሁት ነው።

በግልህ ጥሩ የውድድር ጊዜ ብታሳልፍም እንደ ቡድን መከላከያ ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። የክለብህን አቋም እንዴት ታየዋለህ ?

መከላከያ በጣም ትልቅ ቡድን ነው። እኔንም ጎልቼ እንድወጣ ያደረገኝ ይህ ትልቅነቱ ነው። አሁን ላይ ግን ይህ ቡድን ወጥነት የማይታይበት ቡድን እየሆነ መቷል። ግርጌ ላይ ከሚገኘው ደደቢት ይሻላል የምልበትም ሁኔታ አይደለም አሁን ያለው። ልምድ ያለው ተጫዋቾች ያሉበት እንጂ አማተር ቡድን አይደለም፣ ጥሩ ስብስብ ያለው ቡድን ነው። ሆኖም ጎሎች በቀላሉ ሲቆጠርብን ታያለህ። ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። አለመረጋጋቶች ነበሩብን፤ ስሜት ውስጥ እንገባ ነበር። ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት የዘንድሮ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የአሸናፊዎች አሸናፊ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ማንሳታችን ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን ውስጥ ገብተን የነበረ በመሆኑ ብዬ ነው የማስበው።

በሁለተኛው ዙር የተሻለውን መከላከያ እንጠብቅ ?

አዎ ጠብቅ። ከዚህ በፊት የደረሰብንን ነገር ወደ ኋላ ማሰብ አንፈልግም። በእግርኳስ አንዳንዴ ይሄ ይከሰታል። በተከታታይ አምስት አምስት ጎሎች ገብተውብናል ይሄ አልፏል። በሁለተኛው ዙር የተሻለውን መከላከያ ጠብቁ። አሰልጣኙ ማስተካከል ያለበትን ነገር ያስተካክላል። እኛም ማሻሻል ያሉቡንን ድክመቶች አርመን ወደ አሸናፊነት እናመራለን።

እስካሁን አስራ አንድ ጎሎች አሉህ። በዙርያህ ጠንካራ ተፎካካሪዎች አሉ። በእግርኳስ ታሪክህ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ ምን ታስባለህ ?

ለእኔ ታሪክ ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥም ስሜን መፃፍ እፈልጋለው። ይህን ለማሳካት ደግሞ አሁን ካለኝ ነገር መጨመር ያለብኝ ነገር እንዳለ አስባለሁ። በየጨዋታው ጎሎችን ለማስቆጠር ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ልምምዶቼን በአግባቡ እየሰራሁ፣ ከአሰልጣኜ ጋር እየተማከርኩኝ የተሻለ ነገር አሳይቼ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን አሳካለሁ ብዬ አስባለው።

የብሔራዊ ቡድን ቀዳሚ ተመራጭ አጥቂ በመሆን በጋና ጨዋታ ላይ የመሰለፍ ዕድል አግኝተሀል። በቀጣይ ቦታህን አስከብረህ ብሔራዊ ቡድኑን ለማገልገል ምን ታቅዳለህ ?

አዎ በብሔራዊ ቡድን ታሪክ የሰሩ ተጫዋቾች አሉ። እኔም የራሴን ታሪክ መፃፍ እፈልጋለው። በፊት ቁጭ ብዬ ነበር የማየው፣.፤ አሁን የመጫወት እድል አግኝቻለው። ሁሌም በመጀመርያ አስተላለፍ ውስጥ ለመግባት ጠንክሬ እሰራለው።

ከጅማ እንደመገኘትህ አሁን በኢትዮጵያ እግርኳስ ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀሱ ሁለት የጅማ ክለቦች አሉ። ብዙ ባለ ታሪክ ተጫዋቾች ከጅማ ወጥተው ተጫውተዋል። አሁን ላይ ያሉት ሁለት ክለቦች ከፍተኛ ብር በማውጣት ተጫዋች በማዘዋወር ላይ ተጠመዱ እንጂ የተስፋ ቡድን ላይ እየሰሩ አይደሉም። ይህን እንዴት ታየዋለህ ?

በጣም ይቆጨኛል። ማለት እኔ ባለሁበት ሰዓት እንኳን ለታዳጊ ቦታ አልነበራቸውም። የሚገርምህ በዛን ጊዜ ጅማ ከተማ በሚባልበት ወቅት ከእኛ ፕሮጀክት ጋር ተጫውተን አሸንፈናቸው ነበር። ይህ የምነግርህ እኔ በነበርኩበት ጊዜ ያለውን እውነታ ነው። ይህን አይተው እንኳ በታዳጊ ያላቸው እምነት የወረደ ነበር። ጥሩ ነገር እያሳየን እንኳን ጥሩ ናቹሁ ብለው የሚያበረታቱ አመራሮች እንኳን አልነበሩም። እኛም እንድንጫወት እድሉን የሚያመቻች ሰው አልነበረም። አሁንም ድረስ ታዳጊን ለማየት የሚያስብ አመራር ጠፍቷል። ለአንድ ተጫዋች ከፍተኛ ብር ማውጣቱ አያስከፋም፤ ግን ከሚያመጡት ተጫዋች ጋር ታዳጊ ቀላቅለህ እያጫወትክ ልምድ እየሰጠህ እንዲጫወቱ ማድረግ ወደፊት ገንዘብህን ትቀንሳለህ። የከተማውን ተጫዋች ማውጣት ትችላለህ። ከእኔ ጋር በፕሮጀክት ሲጫወቱ የነበሩ ከሃያ በላይ ታዳጊዎች ነበሩ። አሁን አራት አንሞላም ኳስ የምንጫወተው። የተቀሩት ኳስ አይጫወቱም። ለምን ዕድል ባለማግኘታቸው ምክንያት። ስለዚህ የከተማው የስፖርት አመራሮች ለታዳጊዎች ትኩረት ሊሰጡ ያስፈልጋል።

ከኢትዮጵያ ተጫዋች ለእኔ አርአያዬ ነው የምትለው ተጫዋች ማነው ?

ለእኔ መነሻዬ መሐመድ ናስር ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ እርሱን ነው እያየሁ ያደኩት። ጅማ ላይ የእግርኳስ ተጫዋቾች ስም ሲነሳ ቀድሞ ስማቸው ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል ስሙ ጎልቶ ይነሳል። ከእርሱ ጋር አብሬ የመጫወት እድል አግኝቻለው። በጣም የእኔ ቢሆኑ ብዬ የምመኝለት አቅም አለው። ለእግርኳስ መነሻዬ የማደንቀው እርሱን ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *