ሪፖርት | ድሬዳዋ ወደ ድል ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና በውጤት ማጣት ጉዞው ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን ጨምሮ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በድሬዳዋ ስታዲየም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ተመልካች በታደመበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ ከተከታታይ ውጤት ማጣት በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

በፈጣን እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት በመሄድ የመጀመርያ ጨዋታውን ባደረገው ቡሩዲያዊው አጥቂ ሐሰን ሻባኒ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ቢመታውም በረከት ሳሙኤል በአስገራሚ ሁኔታ ተደርቦ የወጣበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። በዚህ ሙከራቸው መነሻነት በኢትዮጵያ ቡና በኩል የተለየ ነገር የምንመለከት ቢመስልም፤ ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የሆነ የጨዋታ አቀራረብ መሐል ሜዳ ላይ በሚደረጉ የኳስ ንክኪዎች ብልጫ ለመውሰድ የሚደረገው ጥረት ለተመልካቹ አዝናኝ የነበረ ቢሆንም ወደ ፊት በመሄድ በጎል ሙከራ ያልታጀበ በመሆኑ ሌሎች ክፍት የጎል እድሎችን መመልከት ሳንችል ቆይቷል። ያም ቢሆን በድሬደዋ በኩል አዲስ ፈራሚው ምንያህል ተሾመ እና ረመዳን ናስር በፈጠሩት ጥምረት የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት ዘነበ ከበደ ሲመታው የግቡ አግዳሚ የመለሰውን ራምኬል ሎክ በድጋሚ ኳሱን አግኝቶ ወደ ጎልነት በመቀየር ድሬዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በድሬደዋ እንቅስቃሴ ውስጥ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንዲሆን እና ተረጋግቶ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የምንያህል ተሾመ እና የረመዳን ናስር ጥምረት መልካም የሚባል ሲሆን ረመዳን ናስር 33ኛው ደቂቃ ለማዕዘን ምቱ የቀረበ ቦታ ላይ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ወንድወሠን አሸናፊ በጥሩ ሁኔታ ወደ ውጭ ያወጣበት ኳስ ሌላኛው ግልፅ የግብ ሙከራ ነው።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሱን አደራጅቶ በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት መልካም የሚባል ነበር። ሆኖም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በሚፈጥሩት ትርምስ በቀላሉ በተከላካዮቹ እጅ ኳሱ እየገባ ያርቁባቸው የነበረ በመሆኑ የተሻለ የሚባል የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ድሬዎች በአንፃሩ ተረጋግቶ በመጫወት እና የፊት አጥቂዎቹ ሐብታሙ ወልዴ እና ኢታሙኒ ኬሙኒ ወደ መሐል ሜዳ በመምጣት ኳስ በመቀበል በመስመር በኩል አስፍተው ለሚጠብቁት ራምኬል ሎክ እንዲሁም ለረመዳን ናስር በማቀበል ተመልሰው ራሳቸው በመግባት የሚፈጥሩት አደጋ ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ፈተና ነበር። ወደ እረፍት መዳረሻ ረመዳን ያሻገረለትን ነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘው ራምኬል ኳሱን አጠንክሮ በግንባሩ ባለመምታቱ በቀላሉ ግብጠባቂው ወንድወሠን አሸናፊ የያዘበት ሌላ በድሬ በኩል ለጎል የቀረበ የተሻለ አጋጣሚ ነበር።

ከእረፍት መልስ እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ ሙሉ ለሙሉ በተሻለ ሁኔታ እንግዶቹ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በጠንካራ መከላከል የግብ ክልላቸውን ሲጠብቁ የዋሉት የድሬ ተከላካዮችን በማለፍ ጎል ማስቆጠርም ሆነ የጎል ሙከራም ማድረግ ሲሳናቸው መመልከት ችለናል። አሰልጣኝ ስምዖን በኢትዮጵያ ቡና በኩል የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቆጣጠር ምንያህል ተሾመን ወደ ግራ መስመር እያጋደለ እንዲጫወት እና ራምኬል ሎክ ወደ ቀጥተኛ አጥቂ በመሆን እንዲጫወት በማድረግ ሐብታሙ ወልዴን ቀይረው ኤልያስ ማሞን በማስገባት በመሐል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቆጣጠር ያደረጉት ቅያሪ በአንፃራዊነት ተሳክቶላቸዋል።

በአንድ አጋጣሚ 61ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ በፍጥነት በመግባት ወደ ጎል የሞከረው ኳስ ድሬዎች ወደ ፊት መሄድ የቻሉበት ሲሆን በ65ኛው ደቂቃ በተጨማሪ ከሳጥን ውጭ ራምኬል ወደ ጎል አክሮ የመታውን የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ቶማስ ስምረቱ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዘነበ ከበደ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከሳጥን ውጭ ጥቃት ለመፈፀም በተደጋጋሚ ይሞክር የነበረው ረመዳን ናስር 70ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ የመታውን የግቡ አግዳሚ የመለሰበትም በድሬዎች በኩል ጨዋታውን አስቀድሞ ለመጨረስ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ የሚያደርጉት ጥረት በጎል ሙከራ ያልታጀበ በመሆኑና የድሬዎች ተከላካዮች በንቃት የግብ ክልላቸውን መጠበቅ የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በድሬደዋ ከተማ 1 – 0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *