ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሻለ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በዐፄዎቹ 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በደመናማ የአየር ፀባይ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ኃይል የበዛበት ፈጣን ጨዋታ ነበር። በፋሲል ከነማ በኩል ተደጋጋሚ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴም አስመልክቶናል።

ፋሲሎች በራሳቸው ሜዳ ኳስ በመመስረት የተሻለ ብልጫ ወስደው በመጫወት በ7ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ኢዙ አዙካ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝውን የቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን ወደ ግብ ቢያሻማውም በሲዳማ ቡና ተከላካዮች ተገጭቶ ወጥቷል። በመልሶ ማጥቃት ሲዳማ ቡናዎች ወደ ፋሲል የጎል ክልል አንድ ሁለት ተቀባብለው በመግባት 16ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ቢያረጉም ወደ ጎል ሊቀየር አልቻለም።

ፋሲሎች በፈጣን አጨዋወት እና በጥሩ የኳስ ፍሰት መጫወታቸውን ቀጥለው በ20ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ወደ ሳጥን ጨርሶ ይዟት የገባትን ኳስ ለሙጂብ ቃሲም አቀብሎት ሙጂብ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ሙከራው በግቡ ጠርዝ ወጥታለች። 23ኛው ደቂቃ ላይ ግን ከቅጣት ምት ሰለሞን ሀብቴ ወደ ግብ ያሻማው ኳስ በሲዳማ ተከላካዮች ወደ ውጪ በመውጣቱ ሰለሞን ሀብቴ በድጋሜ ከማዕዘን ምት አሻምቶ አማካዩ ኤፍሬም ዓለሙ የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሲዳማ ቡናዎች 25ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ዳዊት ተፈራ ላይ በተሰራው ጥፋት በተገኘው ቅጣት ምት ከመሃል ሜዳ ተከላካዩ ግርማ በቀለ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ሳማኬ ያዳነው የሚጠቀስ ሙከራቸው ነበር። በሌሎች ሙከራዎች 27ኛ እና 33ኛ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ግርማ በቀለ በኤፍሬም ዓለሙ እና ኢዙ አዙካ ላይ ተደጋጋሚ ጥፋት በመስራቱ ከተገኙት ቅጣት ምቶች ሙጂብ ቃሲም እና ያሬድ ባየህ በጭንቅላታቸው ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በሲዳማ ቡና በኩል በተመሳሳይ 38ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግዳይ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኙትን ቅጣት ምት ወደ ግብ ቢያሻሙም በፋሲል ተከላካዮች በቀላሉ ተመልሶባቸዋል። በዚህ መልኩም በብዙ ጥፋቶች የታጀበው የመጀመሪያው አጋማሽ በባለሜዳው ፋሲል ከነማ መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ይልቅ ተረጋግተው የገቡት ሲዳማዎች የፋሲልን ብላጫ ተቋቁመው ነበር የጀመሩት። ግጭቶቹም ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀነስ ብለው በሁለቱም በኩል ጥሩ የኳስ ፍሰት ታይቷል። በሙከራ ደረጃ ሙጂብ ቃሲም 57ኛው ደቂቃ ላይ ከኢዙ አዙካ በተሻማለት ኳስ ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አንድ ደቂቃ በኋላ ከአምሳሉ ጥላሁን የማዕዘን ምት በመቀስ የሞከረው ሌላ ኳስም ወደ ላይ ተነስቶበታል። በሲዳማ በኩል ደግሞ 60ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አዲሱ ተስፋዬ በጭንቅላቱ የሞከረው እና የ64ኛው ደቂቃ የጫላ ተሺታ የግራ መስመር በጣም ድንቅ ሙከራዎች ወደ ውጪ ወጥተዋል። በተጨማሪም ሲዳማዎች በ66ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥኑ ጥቂት ርቀት ባገኙት ቅጣት ምት ሌላ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን አዲስ ግዳይ 70ኛው ደቂቃ ላይ አክርሮ የመታትን ኳስም በሳማኬ ጥረት ድናለች።

ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች በመልሶ ማጥቃት 77ኛው ደቂቃ ግብ ሲቀናቸው ተቀይሮ የገባው አዲሱ ፈራሚ ፀጋአብ ዮሴፍ ለሙጂብ ቃሲም ያቀበለውን ኳስ ሙጂብ በድንቅ አጨራረስ ሁለተኛውን ጎል አድርጎታል። ከጎሉም በኋላ በ83 እና በ85ኛው እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃዎች ሙጂብ ቃሲም ፣ ሸመክት ጉግሳ ፣ ዓለምብርሃን ይግዛው እና አምሳሉ ጥላሁን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያረጉም ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ጨዋታው በፋሲል ከነማ የ2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ ማሸነፉን ተከትሎ በ28 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡናማዎች በ30 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *