ሪፖርት | ጅማ አባጅፍር ከ አዳማ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጅማ ላይ ጅማ አባጅፋርን ከ አዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው ጨዋታ ገና በ4ኛው ደቂቃ አዳማ ከተማዎች የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች ቁጥርን በተመለከተ ጅማ ላይ የክስ ቻርጅ በማስመስዝገብ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጨዋታው ተቋርጦ ነበር።

በመጀመሪያ አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር እና እድሎችን በመፍጠር ከጅማ አባጅፍር አንፃር ተሽለው ታይተዋል። በተደጋጋሚ በሁለቱ ፈጣን አጥቂዎቻቸው በዳዋ ሁቴሳና በብዙዓየሁ እንደሻው አማካኝነት የጅማን የተከላካይ ክፍል ሲረብሹ እና ኳስን አደራጅተው እንዳይጀምሩ በማድረግ በአግባቡ ለአማካይ ክፍሉ የሚላኩ ኳሶች እንዳኖሩ ማድረግ ችለዋል። በጅማ በኩል በተከላካይ አማካይ ስፍራ የሚጫወተው ንጋቱ ገብረሥላሴ ወደ ኋላ በመሳቡ እንዲሁም ይሁን እንደሻው እና መስዑድ መሐመድ በአዳማ አማካይ ተጫዋቾች በመዋጣቸው ባለሜዳዎቹ እድሎችን እንዳይፈጥሩና ብልጫም እንዲወሰድባቸው አድርጓል። የማጥቃት አማራጫቸውን ከተከላካይ ክፍሉ በሚለጉ ተሻጋሪ ኳሶች ማድረጋቸውም በቀላሉ ለአዳማ ተከላካዮች ሲሳይ ሲሆኑ ታይቷል።


በ10ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻረውን ኤፍሬም ዘካርያስ በደረቱ አብርዶ ሞክሮ ዳንኤል አጄ የመለሰበት አስደንጋጭ የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበር። በ30ኛው ደቂቃ ዳዋ ሁቴሳ በቀኝ መስመር ኳስ እየገፋ ወደሳጥን በመግባት ፊት ለፊቱ የነበረውን አዳም ሲሶኮን አታሎ በማለፍ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ዳንኤል አጄ ያዳነበትም ሌላ ጠንካራ ሙከራ ነበር። በጅማዎች በኩል በ18ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ጃኮ ፔንዜ እንደምንም ካወጣበት ሙከራ ውጭ በመጀመሪያው አጋማሽ ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አላደረጉም።
በጨዋታው 40ኛ ደቂቃ ላይ በእለቱ ጥሩ ሲቀሳቀስ የነበረውና በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በመጀመርያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ የገባው ብዙዓየሁ እንደሻው አስቻለው ግርማን በክርኑ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የመጀመርያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማዎች አጨዋወታቸውን ወደ 4-4-1 በመቀየር ኳስን ለጅማዎች በመተው በመልሶ ማጥቃት ተጫውተዋል። አብዛኛዎቹ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ኳስ ጀርባ በመሆናቸው የኳስን የማንሸራሸር እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲወስዱ ለጅማዎች እድል ቢፈጠርላቸውም ወደ ጎል በመቅረብ አዳማዎች ተሽለው ታይተዋል። በተለይ በመልሶ ማጥቃት በረጅሙ ለዳዋ የሚጣሉ ኳሶች ለጅማ ተከላካዮች ፈታኝ ነበሩ።

ጅማዎች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥቦች ይዘው የመውጣት ወርቃማ አጋጣሚ በ57ኛው ደቂቃ አግኝተው ነበር። ሆኖም ወደ አዳማ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ ሱራፌል ዳንኤል በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ግርማ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው ጉልበት ላይ ያመዘነ እና በተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካ የሚቆራረጥ ነበር። ባለሜዳዎቹ ጅማ አባ ጅፋሮች በሜዳቸው እንደመጫወታቸው እንዲሁም የሰው ቁጥር ብልጫ ከመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ጀምሮ እንደመውሰዳቸው በ69ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች አክሊሉ ዋለልኝ እና ሄኖክ ገምቴሳን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት አማራጮችን እየፈጠረ የነበረው መስዑድን ማስወጣታው አግራሞትን የሚጭር ነበር።

በ83ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡን አግዳሚ የውስጥ ክፍል ለትሞ የወጣበት አጋጣሚ ጅማዎችን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አሸናፊ ሊሆኑ የተቃረቡበት አስደንጋጭ ሙከራ ነበር። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ጎል ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *